የካቲት 23 1984 አ.ም.
በመጀመሪያ ባለፈው.....
ባለፈው ደብረዘይት አክስቴን ጥየቃ ሄጄ ነበርና በዚያ ሳለሁ ከምሽቱ ፩፪ ሰዓት ሲል ወደ መንገድ ዳር ወጣ ብዬ ነበር:: በዚያም
ሰዓት ሰማዩ ደማቅ ሰማያዊ መሆኑን ተመለከትኩና የጅማ ከተማ ሰማይ ትዝ አለኝ:: በተለይ በፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት! ከጤና
ሳይንሱ ደጃፍ ወደ ምዕራብ ከከተማው ባሻገር ካለው አድማስ ላይ የጅማ ፀሐይ ግዙፍ ሆና ትታያለች::
አጠላለቁዋ ፈጣን ነው:: በሚገርም ሁኔታ ለአይን ሳታጥበረብር ወርቅ ቢጫ ቀለም እንደተላበሰች ሰማዩን ታክካ
ዥ............ው ብላ ትጠልቃለች:: ከአባ ጅፋር ቤተመንግስት ዝቅ ብሎ በሰፈረው ጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲቱት ውስጥ ስኖር ላይኔ ምግብ ከሆኑኝ የተለያዩ ነገሮች ዋነኛ: ስርቅም ከሚናፍቁኝ ነገሮች አንዱ በበጋው ወራት በየቀኑ ከእራት ሰዓት
በሁዋላ የፀሐይን ጥልቀት መመልከት ነው::
የካቲት ዘጠኝ የቴሌቪዥን ዜና ስለ ንጉሰ ነገስት ሃይለስላሴ አፅም ትናገረ:: አፅሙ ለብዙ አመታት ተቀብሮ ከነበረበት
ቦታ በቁፋሮ መውጣቱን እንዲሁም በመጪው ሐምሌ 16 ቀን 1984 አ.ም. ከንጉሡ መቶኛ ዓመት ልደት ጋር የቀብር ስነስራታቸው
እንደሚፈፀም አዳመጥኩ:: እንደዜናው አባባል አፅሙ የመንግስቱ ሃይለማርያም ቢሮ ስር ሶስት ሜትር ዝቅ ብሎ ተቀብሮ ነበር::
ዋናው ታሪክ.....የፍረሽማን እውቀት
የካቲት 19 ቀን ከአንድ ስራው የደህነንት ፖሊስ ከሆነ ደረጄ የሚባል አብሮ አደግ ጉዋደኛዬ ጋ ሰበታ የሚገኘው ሜታ አቦ ብራ ፋብሪካ ሄጄ ነበር:: ወደሰበታ ለመሄድ በግብዣ መልክ ጥያቄ ያቀረበው ደረጄ ነበር:: “በቃ ዛሬ ቀኑን ሙሉ
እንከባከብሃለሁ” ብሎ:: ሜታ አቦ ብዙም አልቆየንም:: ሁለታችን ብቻ ስለነበርን እንደታሰበው ቆይታው አጉዋጊ ሊሆን አልቻለም::
ስለዚህም ምሳችንን በልተንና ቢራ ጠጥተን ወጣን:: ከዚያ በሁዋላ እዚያው ሰበታ የሚገኝ ስጋ ቤት ሂደን ጥሬ
ስጋ አስቆርጠን ከሰከስን:: የፈረንጅ አረቄና ወይን ጠጅ በመለኪያ አከልንበት........የሚገርም ውሎ ነበር :: መጨረሻ ላይ ከሰበታ ገበያ ብዙ ቲማቲም ገዝተን ወደ ወላጆቹ ቤት ሄድን:: እዚያም ከገዛነው ቲማቲም አስከትፈን በንጀራ ቀምሰን ተኛን :: በዚሁ ቀን ሌሊት ከዚህ በፊት አጋጥሞኝ ያማያውቅ ውጋት ግራ ሆዴ ላይ ቀስፎኝ ከእንቅልፌ ነቃሁ:: መቼም ኃይለኛ....ኃይለኛ ውጋት
ነበር:: ልክ ሆዴ ውስጥ የሆነ ነገር አንጀቴን ነክሶ ወደ ውስጥ እየሳበው የነበረ ነው የመሰለኝ:: መቆምም ሆነ መቀመጥ አቃተኝ:: ግራ ክንዴና እጄ
ዛለ:: ደረጄን ከእንቅልፉ ቀሰቀስኩት:: ህመሙ ብሶብኝ ድምፅ አውጥቼ አለቀስኩ:: የበላሁት እንዲወጣ ጣቴን ላንቃዬ ውስጥ
ሰነቀርኩ:: ከዚያም አስታወከኝ:: ነገር ግን ጥቅም አልነበረውም:: ውጋቱ ቀጠለ:: በግራ ሆዴ በኩል ከእምብርቴ ዝቅ ብሎ ነክሶ ይስበኝ ቀጠለ:: ደረጄ ባጋጣሚ ተቀምጦ የነበረ: ዳግም አረቄ ከጉዋዳ አምጥቶ ሰጠኝ:: አንድ መለኪያ ጠጣሁና በተከታታይ አስታወከኝ:: ጨጉዋራዬ ና አንጀቴ ውስጥ
ያለው በፍጭት ሂደት ላይ ያለ ምግብ በሙሉ በትውከቱ ውስጥ መካተቱን እርግጠኛ ነበርኩ:: በዚህ ሁኔታ ነጋ:: ከጠዋቱ አስራ ሁለት
ሰዓት ላይ ደረጄ አንድ የሰፈር ሀኪም ዘንድ ይዞኝ ሄደ:: ሰውዬው ሀኪም ቤት እንደሚሰራ እንጂ ትክክለኛ ሙያውም ሆነ የትምህርት ደረጃው አይታውቅም: ግን የሰፈር
ሰዎች ሲታመሙ በአነስተኛ ክፍያ ያማክራል: መድኃኒትም ይሰጣል:: መድሃኒቱን ከየት እንደሚያመጣው አይታወቅም:: የሚጠይቅም
የለም:: ብዙም ጥያቄ ሳይጠይቀኝ ሁኔታዬን በማየት ብቻ በፍጥነት አንድ መርፌ ወጋኝ:: ከዚያም አራት ነጫጭና ሶስት ቀያይ ክኒኖች ሰጠኝ:: ሲያስፈልገኝ እንድውጥ:: የክኒኖቹን ስምም ሆነ ለምን ሰባት እንደሆኑ አልጠየኩትም:: እንደምድን ተስፋ በማድረግ ብቻ ከሀኪሙ ቤት ወጣን:: ህመሙ ባይለቀኝም ረፋዱ ላይ ቀነሰ:: በዚያ ወቅት እቤቴ በእናቴ እንክብካቤ ስር ነበርኩ:: እናቴ አመሻሹ ላይ
የተሻለ ብላ ያሰበችው ሌላ የሰፈር ሀኪም ጋ ወሰደችኝ:: ሰውነቴ ክፉኛ ዝሎ ስለነበር ወደ ሐኪሙ ቤት ስንጉዋዝ ሁለት ሶስት ግዜ መንገድ ላይ ማረፍ ነበረብኝ:: ይሄኛው ሀኪም ታሪኬን ከሰማ በሁዋላ በየቀኑ እየተመላለስኩ መርፌ እንድወጋ
አዘዘ:: አንድም እዚያው ወጋኝ:: በሽታዬ ምን እንደሆነ እንዲነገረኝ በድካም ውስጥ እንዳለሁ ጠየኩት:: ቅሬታ ገፁ ላይ ተነበበ:: “አርፈህ ጭንህን ወዲህ በል” አለኝ:: ሶስት ቀን ተመላልሼ ከተወጋሁ በሁዋላ እየተሻለኝ ሄደ:: ብርታት ተሰማኝና መርፌውን በራሴ ውሳኔ አቆምኩት::
እናቴም ተስማማች:: የእናቴ ጉዋደኞችና በርካታ ጎረቤቶች መጥተው ጠየቁኝ:: አብዛኞቹ ጠያቂዎቼ ሕመሜ ብርድ መሆኑን ፈፅሞ አልተጠራጠሩም:: መጋኛ ነው ያሉም አሉ:: የኔ ጥርጣሬ ያረፈው ግን የዛን እለት ምሽት የተመገብነው ቲማቲም ላይ ነው:: እስቲ ጠግበን ውለን ሳለ ምን የማታ ማታ ቲማቲም አስበላን? ምናልባት በንፅህና አልተሠራ ይሆናል:: በኔ ግምት አሜባ ሊሆን ይችላል: አንጀቴን በትክክል አቁስሎታል::
አሜባ እንዲህ ነው እንዴ? ውጋት ብቻ? ያለተቅማጥ? ጥሬ ስጋውስ? የተረፍኩት በእግዜር መሆን አለበት.........
No comments:
Post a Comment