አርብ ታህሳስ 2 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 6 ሰዓት
ፒሲዋን የተሰኘው የጅጤሳው ሕክምና ትምህርት ዓመት (ክፍለ ዘመን ብለው ይቀለኛል)
ሊጠናቀቅ የቀሩት 5 ሳምንታት ወይም ሰላሳ አምስት ቀናት ብቻ ናቸው:: ይህን ሀቅ ዛሬ በመረዳቴ ከእንቅልፌ ቀስቅሰው “ስማ አንድ ሳምንት ብቻ ቀረ!!!” ያሉኝ ይመስል ክው ብዬ ቀረሁ:: ላለፈው ዓመት ያህል የትምህርት ግዜ በየቀኑ የተለፈለፉ እውቀቶች: ሃሳቦች:
መላምቶች: የሰው ልጅ ህልውና ሳይንሶች: አበላሎች: አተነፋፈሶች: አወላለዶች: አስተሳሰቦች: አጠቃላይ አሰራሮች: ጭንቅላቴ ውስጥ በተዘበራረቀ
ሁኔታ ተከምረውና ተጠቅጥቀው የሚገኙ ሲሆን: የተፃፉ ግን ያልተነበቡ ነጥቦች: ፅሁፎች: የተሳሉ ግን በድጋሚ ያልታዩ የአናቶሚ ስዕሎች
እንዲሁም የፊዚዮሎጂ: የባዮኬምስትሪ ግራፎች: አልጎሪዝሞች: ሳይክሎች: ሂደቶች: ፍጭቶች: ግኑኝነቶች: ወዘተ.....በበርካታ ደብተሮችና ማስተወሻዎች
ላይ ሰፍረው: በእኔ በሳምሶን መገለጥን እየጠበቁ በተጠንቀቅ ላይ
የሚገኙ መስሎ ይሰማኛል:: ለመጨረሻው የፅሁፍም ሆነ የቃል ፈተና በብቃት እቀርብ ዘንድ ፒስዋንን ሀ ብዬ ከጀመርኩበት ከሚያዝያ
ወር 1984 አ.ም. ጀምሮ የተስተማርኩትን: በቅንጭላቴ እንዲሁም በደብተሬ ያኖርኩትን ሁልቆ መሳፍርት እውቀት መልክ መልክ ማስያዝ
ይጠበቅብኛል:: በዚህ በጠቀስኩት ግንዛቤ ያለምንም ማጋነን ደንግጫለሁ:: በቀላሉ ሀኪም አይኮንም ለካ.......
እሁድ ታህሳስ 4 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት
ከ 39 ደቂቃ
በዚህ የአእምሮ ውጥንቅጥ ውስጥ ባለሁበት ወቅት አንድ ቆይቶ በጣም ያሳቀኝን ነገር ከጉዋደኛዬ
ከአብይ ጋር ፈፀምኩ:: እሱም እንደኔ በፒስዋን መጨረሻ መድረስ የድንጋጤ መንፈስ ውስጥ ሳይገባ አይቀርም:: ዛሬ ቀን ላይ እኔና
አብይ ገላችንን ለመታጠብ እኩል አሰብን:: ተገናኝተን ወደገላ መታጠቢያ ቤቱ እየሄድን ሳለ የመሄዱን ሃሳብ ድንገት በመተው ውሃ
በባልዲ ሞልተንና ተሸክመን ወደ ማደሪያ ዶርማችን ተመለስን:: ልብሶቻችንን አወላልቀን የዶርሙ መሃል- ለመሃል- መሃል ላይ በመቆም
በባልዲ ጭነን ያመጣነውን ቀዝቃዛ ውሃ ገላችን ላይ እያፈሰስን ታጠብን.....ሳሙና ተለቀለቅን: እንደገናም ገላዎቻችን ላይ ውሃ
ቸለስን:: ማደሪያ ዶርማችን ውስጥ ማለት ነው:: ሌሎቹ የዶርም ተጋሪዎቻችን ባካባቢው አልነበሩም:: ዶርም ውስጥ ገላችንን ለመታጠብ
ያነሳሳንን ምክንያት በትክክል ባላስታውሰውም ና አብይ የሚሰማውን ባላውቅም ያደረግነውን ነገር ለብቻዬ በተደጋጋግሚ እያሰብኩ ከመሳቄ
የተነሳ ጭንቀቴ ቀለል እንዳለልኝ ግን እርግጠኛ ነኝ........
No comments:
Post a Comment