መጋቢት ፩፮ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም.
ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፫
መሄዴ ነው እኔ መሰናበቴ ነው
በሉ ደህና ሁኑ አመሰግናለሁ
ከዛሬው ነገሬ በፊት: ትናንት ወደ አመሻሹ ላይ በስልክ ከቤተሰቤ ጋ ለመገናኘት ችዬ ነበር:: አንድ ጅማ ያሉ የማውቃቸው ሴትዮ እንደምንም ብለው ደውለው ና ተደዋውለው ከአባቴ ጋ አገናኙኝ:: ለአባቴ ትናንት ውሳኔ ላይ ሳይደርስ ስለተቁዋጨው ስብሰባ አወራሁለት:: ለመወሰንም እንደተቸገርኩ ነገርኩት:: በተቻለ መጠን አብዛኛው ተማሪ የሚያደርገውን እንዳደርግ መከረኝ:: ችግሩ.. ...እንዴት ነው አብዛኛው ተማሪ ምን እንዳሰበ ማወቅ የሚቻለው?
ሌላ ደግሞ ከዛሬው ነገሬ በፊት....ትናንትና ማታ ከዚህ በፊት አድርጌው በማላውቅ ሁኔታ መጠጥ በብዛት ጠጥቼ ነበር:: ደግነቱ ከጉዋደኞቼ ጋ ነው:: በአምሳሉ ጋባዥነት ወደ ከተማው መሀል ወርደን ነበር:: በርከት ያለ ጠርሙስ ወይን ጠጅ ጠጥተን ስናበቃ ጂን በመለኪያ ጨመርንበት:: መጠጥ ባፈዘዘው ዕይታና ባንገዳገደው እርምጃ ወደ ጤና ሳይንሱ ግቢ ስንመለስ ሌሎች በርካታ ተማሪዎች በተመሳሳይ አንዳንዶቹም በላቀ ስካር ዉስጥ ሆነው በግቢው መንገዶች ላይ ከላይ በመቆንጠጫ ተይዞ እንደተሰቀለ ልብስ ሲንገዳገዱና ሲወድቁ አስተውያለሁ:: አረ ጭፈራ ሁሉ ነበር:!! የተስፋ መቁረጥ ይሁን የቆራጥነት አላውቅም:: እኔ ና ጉዋደኞቼ በበኩላችን በጋራ ተስፋ የቆረጥን ይመስለኛል:: ከ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ የጀመረ አንድ ግዙፍ ሆታ የጤና ሳይንሱን ግቢ ከ መመገቢያው አዳራሽ እስከ ዋይት ሃውስ ድረስ አናጋው:: የሚዘፈነው ዘፈን ስለምን እንደነበር ወይም ማን የዘፈኑ አውጪ እንደነበር በቅጡ ማስታወስ አልቻልኩም:: ግን "የእርግብ አሞራ" አይነት ይመስለኛል:: በእርግጠኘት የማስታውሰው ግን በመጠጥ ስሜት ከብዙ በቅርብ ከማላውቃቸው ሌሎች ሰካራም ተማሪዎች ጋር ልክ ተጠፋፍቶ እንደተገናኘ ጉዋደኛማች ስተቃቀፍ ነበር:: ሌሎቹም እርስ በርሳቸው ይተቃቀፉ ነበር:: ለማልቀስ የሚዳዳውም ነበር:: በሆታውና በዘፈኑ ውስጥ የተመለከትኩት አብዛኛው ጨቅላ ና የፍሬሽ ማን ተማሪ መሆኑን በምልሰት ልብ ብያለሁ:: ምን እናውቃለን ገና ልጆች ነን:: እኔ አስራ ስምንት አመት የሚሆነኝ በሚቀጥለው ወር ነው:: ነባር ተማሪዎች ዶርማቸውን ዘግተው እንደዶሮ በግዜ ተኝተው ወይም ሳይተኙ አልጋቸው ላይ ተጋድመው ነበር:: ወደ ብላቴ የመሄዱን ነገር በአንደኝነት የጠሉት እነሱ ይመስሉኛል:: እስካሁን በዘመቻው ዙሪያ በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ደፍረውና ፊት ለፊት ወጥተው ሲከራከሩ ነበር::
አሁን ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ከሩብ ይላል ሰዓቴ:: ከትናንትናው መጠጥ የተረፈውን ራስ ቅሌን ተሸክሜ ከ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ መኝታ ቤታችን አጠገብ በስተግራ ያለ ሌላ አዳራሽ ውሃ ልክ ላይ ቁጭ ብዬ ወደ ብላቴ ይዘውን የሚሄዱትን አውቶቡሶች እየተጠባበኩኝ ነው:: በሁዋላ የሚሆነው ይሆናል ለማንኛውም ሁሉም ሰው ሊያደርግ እንደተዘጋጀው ተሳፍሮ መሄድ ነው:: ግቢው ውስጥ መቅረትም የሚቻል አልመሰለኝም:: እንቅስቃሴ ሁሉ ቆሙዋል:: እንደገባኝ ከሆነ አውቶቡሶቹ በአዲስ አበባ በኩል ማለፋቸው ግድ ነው:: እናም እዚያ ስንደርስ........የሚሆነው አይታወቅም... ወደ ብላቴ ለመሄድ ወይም ላለመሄድ ለመወሰን አሁንም ግዜ አለ:: ብዙ ተማሪ እንደአዚህ እንደሚያስብ አልጠራጠርም::
.....ከተወስኑ ደቂቃዎች በፊት ስታዲዮሙ ውስጥ ለተሰበሰብን ተማሪዎች ዲኑ መጠነኛ የመሰነባበቻ ንግግር አድርገው ነበር:: "ውድ ተማሪዎች ኢንስቲትዩታችሁን አትረሱዋት ዘንድ ይህ የማስታወሻ አርማ ከናንተ ጋር ይሁን ብለው ለተማሪዎች ተወካይ አርማውን ሰጡ:: ንግግራቸውን ቀጠሉ "በውነቱ አይደለም ይህን አጋጣሚ አንፈልገውም ነበር:: ግን ሆነ:: ምንም ማድረግ አንችልም...ውድ ተማሪዎች እኛ ምን ግዜም አንረሳችሁም:: በሄዳቹበት ሁሉ ስለናንተ ሁኔታ እየመጣን ለመጠይቅ እንሞክራለን..........ወዘተ......
No comments:
Post a Comment