መጋቢት ፩፮ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም.
ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፬
አትሸኙንም ወይ ልንሄድ አይደለም ወይ
በዚህ ቀን ጠዋት ይጀመራል ተብሎ የታሰበው ጉዞ ሳይጀመር ቀረ:: ተማሪውም ሆነ የጤና ሳይንሱ አካባቢ ነዋሪ የአውቶቡሶቹን መነሳት እየተጠባበቀ አርፍዷል:: ለተማሪዎች ከመሄድ ሌላ ምንም አማራጭም ሆነ ግቢው ውስጥ በመቅረት የሚደረግ ነገር አልነበረም:: የጤና ሳይንሱ ግቢ እንቅስቃሴ ተለውጧዋል::ወደ ስልጠና እንድንሄድ የተወሰነ መሆኑ በዲኑ ከተነገረበት ቅፅበት አንስቶ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ምንም ስፍራ እንደሌላቸው የሚያመላክቱ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል:: የጤና ሳይንሱ ሰራተኞችም ከተለመደው የለት ተለት ሂደት በተለዩ ስራዎች ተጠምደዋል:: አልጋዎች ና ቁም ሳጥኖች እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ መገልገያ አቃዎች በነጠላና በጅምላ ወደ ወደ መጋዘን ሲገቡ ተመለከትኩ:: ለወትሮው ውር ውር ሲሉ ይታዩ የነበሩ መኪኖች የተበላሹ ይመስል ያለእንቅስቃሴ ተደርድረው ይታያሉ:: የጅማ እርሻ ኮሌጅ ተማሪዎችም በተመሳሳይ ቀን ና ሰዓት ከተማውን የሚለቁ መሆናቸው ስለታወቀ እንቅስቃሴ የምንጀምርበትን ሁኔታ ለማየት ብዙ የከተማው ሕዝብ በየመንገዱ ተኮልኩሏል::
ከጅማ በጠዋት በመነሳት ወሊሶ ከተማ ላይ ምሳ ለማድረግ ነበር የታቀደው:: ይህ ሊሆን ስላልቻለ ለመጨረሻ ግዜ በ ጤና ሳይንሱ ምግብ ቤት ምሳ ተመገብን:: ወጥ ቤቷ አይኖቹዋ እንባ እንዳቆረዘዙ እጇ እየተንቀጠቀጠ የጨመረችልኝ የዛሬው ወጥ በሚገባ ተቁላልቶ ና ትክን ብሎ የተሰራ ምስር ክከ ወጥ ነበር:: ከምሳ በሁዋላ ብዙም ሳንቆይ የሚወስዱን አውቶቡሶች ጥሩምባ እያሰሙ ወደ ጤና ሳይንሱ ቅጥር ግቢ ተከታትለው ገቡ:: ድንገት ጫጫታና ግርግር በዛ:: ሁሉም ተማሪ በአንድ ግዜ እቃውን እየተሸከመ ወደ አውቶቡሶቹ መሮጥና መጠጋት ጀመረ:: እኔም እንግዲህ ሰው እንደሚያደርገው አደረግሁ..አባቴ እንደመከረኝ:: በግርግሩ መሃል ሃሳቤን ለመሰብሰብና አካባቢዬን ለመቃኘት ሞከርኩ:: አንዳንንድ ተማሪዎች በአካባቢው እንደሌሉ አስተዋልኩ:: ለምሳሌ አራቱ የኛ ባች ሴቶች: አራቱ ኤርትራውያን: ሌሎችም....የሉም:: ኦ! የቅርብ ጉዋደኞቼ በሙሉ አካባቢዬ አሉ:: ተመስገን...ግን ፊታቸውን ስመለከተው አብዛኛዎቹ ቀፍፎአቸዋል:
አውቶቡሶቹ በተማሪዎች መሞላት ጀመሩ:: የጦሩ አባል እንዲሁም ከኛጋር የህክምና ተማሪ የሆነው ሻምበል ጌታቸው በነገረልን መሰረት የአንደኛ ዓመት የህክምና ተማሪዎች በቁጥር አምስት አውቶቡስ ላይ ተሳፈርን::
ከቀኑ ሰባት ሰዓት አውቶቡሶቹ የጤና ሳይንሱን ግቢ እየለቀቁ መውጣት ጀመሩ:: ሲመጡ እንዳደረጉት ጥሩምባቸውን ለቀቁት...ቢፕ...ቢፕ...አንዳንዶቹ አውቶቡሶች ውስጥ ያሉት ተማሪዎች "አትሸኙንም ወይ ልንሄድ አይደለም ወይ" እያሉ የዘፍኑ ነበር:: ይህም መሬት ላይ ያለውን የከተማውን ሰው ግርግር ጨመረው:: ድምፆች በረከቱ:: ሩጫ ና ጫጫታ በዛ........ከወራት በፊት ጨቅላ ወንዶች የታጨቁባቸው አውቶቡሶች ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ሲንቀሳቀሱ ና የከተማው ሰውም አውቶቡሶቹን እየተከተለ ሲሮጥ ና ሲያለቅስ እንዳላየሁ እኔም አውቶቡስ ውስጥ ተቀምጬ መሬት ላይ ያለ ሕዝብ ሲከተለኝ አየሁ:: ብዙ የሚያለቅሱ ኢትዮጵያዊ ሴት ፊቶች አየሁ:: እኔም እንባዬ መጣ........
የጤና ሳይንሱ ሰራተኞች እያለቀሱ በግቢው ተሽከርካሪዎች በመሆን እስከ ሰርቦ ከተማ ድረስ ሸኙን:: አውቶቡስ ውስጥም ሆነ ከአውቶቡስ ውጭ የነበረው ግርግር የሰርቦን ከተማ እንዳለፍን እየበረደ መጥቶ መጨረሻ ላይ ቆመ:: እኛም በየተቀመጥንበት የየግላችንን ወሬ ማውራት ጀመርን:: ተዳክመንም ነበር....
በቁጥር አምስት አውቶቡስ ውስጥ የነበሩ ሹፌሩ አካባቢ እነ ሻምበል ጌታቸው: በላይነህ: ፍቅሩ: ኃይሉ: አንበሳው: አያሌው: ፍፁም: ቸርነት: ና ሌሎችም........እኔ ወዳለሁበት አካባቢ ደግሞ: እነ መንግስቱ:አብይ:ሚሊዮን: ማስረሻ: ና አምሳሉ ....... ወደ ሁዋላ አካባቢ እነ ያሬድ: አይዘን አወር: ዘመኑ ይታዩኛል:: ከሌላ ደፓርትመንት አስፋው: አረጋ: ፋሲልና ሚፍታህ.......ብዙዎቻችን አንድ ፍሬ ጨቅሎች ነን...
ሹፌሩን በአውቶቡሱ ካሴት ማጫወቻ ዘፈን እንዲያሰማን ጠየቅነው:: አንድ ቆየት ያለ የአስቴር አወቀ: የጌታቸው ካሳ: የብርቱካን ዱባለ ና አንድ የሱማሌኛ ዘፈን እያፈራረቀ አሰማን::
አውቶቡሶቹም ሸመጠጡ....
No comments:
Post a Comment