Wednesday, December 30, 2015

ጥር መጨረሻ - 1985 አ.ም.
የፒሲዋን ማጠቃለያ ፈተና ትዝታ

በዚህ ህዝበ ፒሲዋን ባይምሮ ጭንቀት በተወጠረበት ሰሞን የባዮኬሚስትሪ ጥናቴን እንድጀምር እነመንጌ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰኣት ቀሰቀሱኝ:: ተነሳሁና ከነወሰንየለው ዶርም ውሃ ኣምጥቼ ሁለተኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ከዶርማችን ፊትለፊት ፊቴን ስለቃለቅ በዚህ ውብ በሆነ ነፋሻማ ለሊት ወደባላምባራስ ሜጫ ቡና ቤት አቅጣጫ ጨረቃን በድፍን ገጽታዋ በከዋክብት መሃል ሆና ተመለከትኩ:: ደስታ ተሰማኝ:: ጨረቃን እያየሁና የባጥ የቆጡን እያሰብኩ በረንዳው ላይ ከቆየሁ በሁዋላ ከሌሊቱ ኣስራ ኣንድ ሰኣት ሲል ወደ ዶርም ገባሁ:: በዚህ ሰኣትም በእርግጥ ዶርሙ ውስጥ በንቃት የቆምኩት እኔ ብቻ እንደሆንኩ ኣስተዋልኩ:: የዶርም ታጋሪዎቼ ሁሉ ተኝተው እስትንፋሳቸው ብቻ ይሰማኛል::  የጭንቀትና የስቃይ እስትንፋሶች ከዶርሙ ኣራቱም ማዕዘኖች አየተነሱ በጆሮዬ ጠለቁ:: ምስኪን እስትንፋሶች:: ሌሊቱ ሊያበቃ የቀረው ኣንድ ሰኣት ብቻ ነው:: ይሄ ሁሉ የተኛ መንጋ አንደነበረ ይቆይ መስሎታል:: የተለመደ የፈተና ሰሞን ግርግሩን ከአፍታ በሁዋላይጀምራል:: ከእንቅልፍ የመቀስቀሴ ምክንያት የሆነውን የባዮኬሚስትሪ ጥናት ገና ኣልጀመርኩም………..

ከላይ የፈተና ሰሞን ግርግር ብዬ ያልኩት መቸም ዘርፈ ብዙ ነው:: በተለይ ይህ የማጠቃለያ ፈተና ለመጀመሪያ ግዜ ከውጭ በመጡ ሳይንስ ኣዋቂዎች በቃል ፈተና የምንገመገምበት ጭምር ስለሆነ የዚህ ክስተት ፍራቻ ትልቁን ስፍራ ይይዛል:: ይህ የቃል ፈተና የጽሁፍ ፈተናዎቹ ከተጠናቀቁ በሁዋላ የሚደረግ በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት የሚኖረን ጭንቀት ሁለት ኣይነት እንዲሆን አድርጎታል:: የመጀመሪያው ለያንዳንዱ የጽሁፍ ፈተና የምነጨነቀው ሲሆን ሁለተኛው ለዚህ በሂወታችን የመጀመሪያ ለሆነ የቃል ፈተና የምንጨነቀው ነው:: ሁለቱም ጭንቀቶች  ግዙፍና ከኣቅም በላይ በመሆናቸው ለመሸከም ኣቅም ይጠይቃሉ:: ስለዚህ ይህ ሰሞን አኔም ሆንኩ እኔን መሰል ፒሲዋነኞች አንዴት አንደምንጨነቅ ራሱ ግራ የገባን ሰሞን ነው:: በዚህ የሩጫና የግርግር ሰሞን ኣለመጨነቅኣበድኩ አንዴ?” የሚል ጥያቄ በመፍጠር ከጭንቀት የተለየ ግን ክብደቱ ተመሳሳይ የሆነ ስሜት ውስጥ ይከታል:: ለዚህ ስሜት ስም አጣሁለት:: በቃ መግለጽ የሚያዳግት የኣአምሮ መዋለል ልበለው? የዚህ ኣይነት ስሜት መገለጫ ኣንዱ ኣላስፈላጊ ያለቦታው የሚገለፅ ፈገግታ ነው:: ብዙ ፒሲዋነኞች ፈገግ ሲሉና ከዚህ በፊት ብለዋቸው ያማያውቁትን ደንታ ቢስ ቃላቶች ሲወረውሩ እሰማለሁ:: ጭምት የነበሩ ኣንዳንዶች: ተጫዋችና ቀልደኛ ሆነዋል:: ኮስታራና ለወትሮው ጥናት የኑሮኣቸው ኣመዛኙ ክፍል የነበሩ ኣንዳንዶች ደሞ ቴሌቪዥን ከፍል መበርከት ጀምረዋል:: በፈተናዎች መካከል ማለት ነው….

የጽሁፍ ፈተናዎች ቀጥለዋል…. ኣንዱ ፈተና ሲጠቃለል ያለምንም ትንፋሽ የሌላው ፈተና ዋዜማ ይሆናል:: ስለዚህም ኣንዱ ፒሲዋነኛ ከሌላው ሲገናኝና ወግ ሲያወጋ ፈተናው ኣጀንዳ መሆኑ ቀርቶ ሌሎች በዚህ ግዜ ያማያሳስቡ ጉዳዮች  ሆነዋል የሚወሩት::

አኔ በበኩሌ ሁልግዜም ቢሆን የሚያስቸግረኝ ለማጥናት ስቀመጥ ብቻ የሚከሰት የቀልብ መበታተን ና የአእምሮ መብሰክሰክ ኣሁን በዚህ የፈተና ሰሞን ከመቼውም ግዜ ልቆ እየተገዳደረኝ ነው:: ኣአምሮየዬ እንቶ ፈንቶ ሃሳቦችን ያለምንም ገደብ በቀላሉ ተቀብሎ ያስተናግዳል:: ማሰብና መቀበል ያቃተው ለፈተናው መነበብ ካለበት ወረቀት ላይ ያለውን ሀሳብ ነው….

በዚህ ሁሉ መካከል ኣንዳንዴያለተስፋ አንዴት መኖር ይቻላል?” የሚለው መፅሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ጥያቄ ይመጣብኛል

ታዲያ ይህን ሁሉ በሆነበት ሰሞን ኣንድ ጠዋት የኣናቶሚ የቃል ፈተና ተራዬ ደርሶ ተፈተንኩ:: አንዳጋጣሚ ሆኖ ኣናቶሚ የሚፈትን ኣዋቂ ከሌላ ቦታ ስላልተገኘ ፈታኞቹ ፕሮፌሰር ሳላህና ሚስቱ ኤቢትሳም ነበሩ:: እምብርዮሎጂም ኣንድ ላይ ተፈተንኩ:: በውነት በጣም ደስ ያለኝ ቀን ነበር:: የተጠየኩትን ጥያቄ ሁሉንም ማለት በሚቻል መልኩ መለስኩ::  ፈተናው ኣልቆ በቃ-ሂድ ሲሉኝ ማመን ኣልቻልኩም:: በቃ ይሄው ነው? ኣልኩ በልቤ:: ከዚህ በሁዋላ ሂወቴን ሙሉ ኣናቶሚ አንደማልፈተን ወይም አንደማልማር ኣሰብኩና ኣዘንኩ:: በጣም አጅግ በጣም የምወደው ትምህርት ነበር:: አኔና የኣናቶሚ ደብተሮቼ አንዲሁም ውድ የሆኑት ኣናቶሚና አምብርዮሎጂ ስዕሎቼ ብቻችንን ቀረን:: ለሁሉም ግዜውን ይጠብቅለታል አንደተባለው የኣናቶሚ ስዕሎቼን በሜዲሲን ተማሪነቴ ሳይሆን በተፈጥሮና ስነጥበብ ኣድናቂነቴ የምመለከትበትና ግዜ ሩቅ አንደማይሆን ተስፋ ኣለኝ….

የቃል ፈተናዬን ያጠናቀኩት በፊዚዮሎጂ ነበር: የካቲት 3 ቀን 1985 ኣ.ም.:: ለገሰ የሚባል ከጥቁር ኣንበሳ ሆስፒታል የመጣ ፊዚዮሎጂስት ነበር የጠየቅኝ:: ፊቱ ዙሪያውን እውነትም ኣዋቂ በሚያሰኝ የተንዠረገገ ጺም የተሸፈነ ከኣፉ በላይ ካይኖቹ በታች ካፍንጫው ዳር ዳር ምንም ኣይነት መስመር የሌለው ኮስመን ያለ ሰው:: በመጀመሪያ በትርፍ ግዜዬ ምን ማድረግ አንደምወድ ጠየቀኝ:: “ስዕ መሳል” ብዬ መለስኩ:: ኣንጎል አንድስልለት ጠየቀኝ:: ግዜም ሳይፈጅብኝ ሳልኩለት:: ከዚያ ቪዡዋል ኮርቴክስ (Visual Cortex) የቱ ጋ ነው? ብሎ የፈተናውን ጥያቄ ጀመረ:: አሳየሁት:: ……

ፈተናውን ጨርሼ ስወጣ የተሰማኝ አንድና አንድ ነገር ቢኖር ወደ ሶስተኛ ኣመት ማለፌ አርግጥ እንደነበረ ነው…

በዚሁ ሰሞን ነበር የህቺን አጭር ግጥም አጀንዳዬ ላይ ያሰፈርኩት

የተጻፈው ሁሉ ላይነበብ ላይጠና
ሲከማመር በላይ በላይ ለፈተና
የዚህን ኣለም ድብቅ ሚስጥር
ያልተሰማ ጥልቅ ነገር
ኣውቀናል አስክንል ድረስ
ከምድር ኣልፈን ሰማያቱን እስክንዳስስ
አውቀት በውቀት ላይ ሲከማመር
ኣለቀ ሲባል ኣዲስ ደሞ ሲፈጠር
ጣቶች በመጻፍ ሲደክሙ
ብእሮች በጭነት ብዛት ሲጣመሙ
ቀኑ ሲመሽ ሌሊቱ ደግሞ ሲነጋ
ኣንድም ቀን አንኩዋን ሳንል ረጋ
ድንጉጥና ችኩል ሆነን
የማያልቅ ሆኖ አየታየን

ይኸው ደረሰ ኣበቃ ፒሲዋን

Monday, October 26, 2015

ጥር ሁለት ቀን 1985 .. ከቀኑ ሰባት ሰዓት
ዉቦቹና በጨረቃ ይደምቁ የነበሩት ምርጦቹ የበጋ ወራት ሕዳርና ታህሳስ ፒሲዋን ማጠቃለያ ፈተና መምጣት ስጋት ተጀቡነው ተራ በተራ በማለፍ ስፍራቸውን ለጥር ለቀቁ:: ጥር ወር ደግሞ  የያንዳችዳችን በጅጤሳ መዝለቅና አለመዝለቅ የሚወሰንበት ወር ለመሆን ታደለ:: ብርቱ የሂወት ፈተና ወቅት:: የድብልቅልቅ ስሜት ወቅት:: ባንድ በኩል አድካሚዎቹ የሌክቸር ክፍለ ጊዜያት የሚያበቁ በመሆናቸው አንፃራዊ እፎይታ ተሰምቶኛል:: በሌላ በኩል ደግሞ ለፈተናው ያደረኩትና ገና የማደርገው ዝግጅት መቼም ቢሆን እንደማይበቃ ከማወቅ የመነጨ የውስጤ መብሰክሰክ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ነው:: እነዚህን የጠቀስኩዋቸውን ስሜቶች ሌሎች ሰላሳ ምናምን የሚሆኑ ፒስዋነኞች  እንደሚጋሩኝ እርግጠኛ ነኝ::

የመጨረሻው የፒሲዋን ሌክቸር ቀን በሚቀጥለው ሮብ እንደሚሆን ተነግሮናል:: ከዚያም ሁለት ሳምንት ከጥናትና በጄም ካለ ከክለሳ መሳ ለመሳ የምንገጥምበት ግዜ ይሆናል:: ያም ሲያበቃ  የዓመቱ ማጠቃለያ የፅሁፍ ፈተና በአናቶሚ ትምህርት ይጀመራል:: እንግዲህ ባወጣ ያውጣው......... እኔ ግን ምንም አልተዘጋጀሁምም ከዚህ በሁዋላም የምዘጋጅ አይመስለኝም.....

በነገራችን ላይ ባለፈው ሰሞን ፊዚዮሎጂ ሌክቸር ላይ ስለ Color Blindness ተማርን:: የፊዚዮሎጂ መምህሩ ለናሙና ይዞ የመጣው  Color Blindness መለያ ወረቀት ላይ የተሳሉ በነጠብጣብ የተሞሉ ክበቦች ለምሳሌነት አንዳንድ ተማሪዎችን እየጠራ ስንት ቁጥር ወይም ምን ይታያቹሃል እያለ ሲጠይቅ ከተጠያቂዎቹ አንዱ እኔ ነበርኩ:: ታዲያ እኔ ላይ ሲደርስ ሌላው ሁሉ ስምንት ይሁን አራት ቁጥር ያለውን እኔ ሶስት ቁጥር ነው ብዬ ድርቅ በማለቴ ለመጀመሪያ ግዜ Color Blind እንደሆንኩ ታወቀ:: ቀይና አረንጉዋዴ ቀለሞች አልፎ አልፎ እንደሚምታቱብኝ ቀደም ብዬ የተረዳሁ ቢሆንም አሁን በደንብ ተነቃብኝ....ወይኔ

ጥር 18 ቀን 1985 .. ከምሽቱ 2 ሰዓት  21 ደቂቃ
በእውነቱ የባለፈውን ማስታወሻ ካሰፈርኩበት ከጥር ሁለት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ባሳለፍኩዋቸው ቀናት የተከናወኑ ድርጊቶች ቢኖሩም ቀናቱ ለኔ ብቻ ሳይሆን ለመላው ፒሲዋነኞች እጅግ አስጨናቂ እንዲሁም የአእምሮን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ቀናት ስለነበሩ እዚህ ማስታወሻ ላይ አሰፍራቸው ዘንድ ከባድ ሆነብኝ:: እጄም ይፅፍ ዘንድ ሳሳ:: ነገር ግን ይህን እላለሁ: በዚህ ሰዓት የዓመቱ ማጠናቀቂያ የፅሁፍ ፈተና  መጀመሪያ ዋዜማ ላይ ከመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ ጋር የሞቀ ወሬ ይዘናል:: ጥናት የሚባል ነገር አቁመናል:: ዘራፍም ብለናል:: አልተጨነቅንም ማለት ግን አልነበረም:: ጥቂቶቹ የተናገሩትን እነሆ...
ሚሊዮን "ቀፎኛል"
አምሳሉ "እንግዲህ ጭንቅላቴን የከበደውን አናቶሚ ነገ ልገላገለው ነው: በጣም ራሴን አሞኛል"
መንጌ "ፒሲዋን መርዝ ነው ግን ሰው አይገድልም"
ኃይሉ "ተስፋ ትልቅ ነገር በውስጤ እየኖረ: ሂወት ትንሽ ነገር ታጓጓኝ ጀመረ"


Sunday, October 11, 2015

ማክሰኞ ታህሳስ 13 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 6 ሰዓት ከሩብ

የፒሲዋን ትምህርት ጥር 8 ቀን  1985 አ.ም. እንደሚጠናቀቅ ተነግሮናል:: ከዚያ በሁዋላ የማጠቃለያ የፅሁፍ ብሎም የቃል ፈተና ይኖረናል:: የቃል ፈተናውን የሚሰጡን ከሌላ የህክምና ትምህርት ቤቶች የመጡ መምህራን ይሆናሉ.....

ዛሬ ከሰአት በአናቶሚ ላቦራቶሪ ውስጥ የነበረንን ቆይታ በዚህ ማስታወሻ እንድከትብ የገፋፋችኝ ፅጌረዳ እንደሆነች ልብ በል/ይ:: ፅጌረዳ አብረውን ከሚማሩት ሶስት የክምና ተማሪ ሴቶች መካካል አንዷ ስትሆን ማስታወሻ እንደምፅፍ ታውቃለች::

ዛሬ ከሰዓት ፕሮፌሰር ሳላህ ከመጨረሻዎቹ አንዱ የሆነውን የአናቶሚ ላቦራቶሪ ክፍለ ጊዜ በሚደንቅ ሁኔታ አካሄደ:: ይህን ሁኔታ መቸም አልረሳውም:: ፕሮፌሰር ሳላህ ከካዳቨሮቹ ራሶች ውስጥ አንጎሎቻቸውን ፈልቅቆ እያወጣ አሳየን:: እሱ አንድ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ቆሞ እኛ ተማሪዎቹ መሬት ላይ ቆመን ክብ ሰርተን ወደላይ በተመስጦ እያየነው አንድ የተገመሰ አንጎል በአንድ እጁ ይዞ በሌላው እጁ ደግሞ በአንጎሉ የውስጥ ክፍል በኩል (medial aspect) እየጠቆመ ብሎም በጎላ ድምፅ በርካታ ስሞችን ነገረን:: ከያንዳንዱም ስያሜ በስተጀርባ ያለውን አገልግሎት ባጭር ባጭሩ አስረዳን.....Internal capsule, putamen, caudate-nucleaus, insula, pallidum, thalamus, ventricles etc.

አሁን ይህን በምፅፍበት ሰዓት ያለሁት በዶርም ቁጥር 207 ነው:: የዶርሙ አባላት በተለያየ ሁኔታና ደረጃ ላይ ይገኛሉ....ማለቴ ጥናትን በተመለከተ ማለት ነው:: አመንቴ የሚባለው ጉዋደኛችን ገና ከእንቅልፉ ተነስቶ አያሌውንና ሚልዮንን እየቀሰቀሳቸው አየሁት:: እነዚህ ሶስቱ እንግዲህ ቀሪውን ሌሊት እስከቻሉና አቅማቸው እስከፈቀደ በንባብና በጥናት ትጋት ለማሳለፍ የሚሹ ናቸው::  እኔ ደሞ ለመተኛት እየተዘጋጀሁ ነው:: ቀስቃሹ ራሱ ግን እንቅልፉን ገና አለመጨረሱ በጉልህ ያስታውቃል:: መልካም ዕድል ተመኘሁለት በልቤ:: አያሌው ላለመነሳት ጥቂት ካንገራገረ በሁዋላ ተነስቶ ፊቱን መታጠብ ጀምሩዋል:: አዳሙ የተባለው ሌላው ወንድማችን  ያለማንም ቀስቃሽ ራሱ ከእንቅልፉ ተነስቶ ማንበብ ለመጀመር እየተሟሟቀ ነው:: አምሳሉ የቤተማርያም አልጋ ላይ ተጋድሞ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ውስጥ ነው:: ታድሎ! ቤተማርያም በዶርሙ ውስጥ የለም:: ጥናት አምባ ርቆ ተሰማርቷል.......

Sunday, October 4, 2015

አርብ ታህሳስ 2 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 6 ሰዓት

ፒሲዋን የተሰኘው የጅጤሳው ሕክምና ትምህርት ዓመት (ክፍለ ዘመን ብለው ይቀለኛል) ሊጠናቀቅ የቀሩት 5 ሳምንታት ወይም ሰላሳ አምስት ቀናት ብቻ ናቸው:: ይህን ሀቅ ዛሬ በመረዳቴ ከእንቅልፌ ቀስቅሰው “ስማ አንድ ሳምንት ብቻ ቀረ!!!” ያሉኝ ይመስል ክው ብዬ ቀረሁ:: ላለፈው ዓመት ያህል የትምህርት ግዜ በየቀኑ የተለፈለፉ እውቀቶች: ሃሳቦች: መላምቶች: የሰው ልጅ ህልውና ሳይንሶች: አበላሎች: አተነፋፈሶች:  አወላለዶች: አስተሳሰቦች: አጠቃላይ አሰራሮች: ጭንቅላቴ ውስጥ በተዘበራረቀ ሁኔታ ተከምረውና ተጠቅጥቀው የሚገኙ ሲሆን: የተፃፉ ግን ያልተነበቡ ነጥቦች: ፅሁፎች: የተሳሉ ግን በድጋሚ ያልታዩ የአናቶሚ ስዕሎች እንዲሁም የፊዚዮሎጂ: የባዮኬምስትሪ ግራፎች: አልጎሪዝሞች: ሳይክሎች: ሂደቶች: ፍጭቶች: ግኑኝነቶች: ወዘተ.....በበርካታ ደብተሮችና ማስተወሻዎች  ላይ ሰፍረው: በእኔ በሳምሶን መገለጥን እየጠበቁ በተጠንቀቅ ላይ የሚገኙ መስሎ ይሰማኛል:: ለመጨረሻው የፅሁፍም ሆነ የቃል ፈተና በብቃት እቀርብ ዘንድ ፒስዋንን ሀ ብዬ ከጀመርኩበት ከሚያዝያ ወር 1984 አ.ም. ጀምሮ የተስተማርኩትን: በቅንጭላቴ እንዲሁም በደብተሬ ያኖርኩትን ሁልቆ መሳፍርት እውቀት መልክ መልክ ማስያዝ ይጠበቅብኛል:: በዚህ በጠቀስኩት ግንዛቤ ያለምንም ማጋነን ደንግጫለሁ:: በቀላሉ ሀኪም አይኮንም ለካ.......

እሁድ ታህሳስ 4 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 12  ሰዓት ከ 39 ደቂቃ


በዚህ የአእምሮ ውጥንቅጥ ውስጥ ባለሁበት ወቅት አንድ ቆይቶ በጣም ያሳቀኝን ነገር ከጉዋደኛዬ ከአብይ ጋር ፈፀምኩ:: እሱም እንደኔ በፒስዋን መጨረሻ መድረስ የድንጋጤ መንፈስ ውስጥ ሳይገባ አይቀርም:: ዛሬ ቀን ላይ እኔና አብይ ገላችንን ለመታጠብ እኩል አሰብን:: ተገናኝተን ወደገላ መታጠቢያ ቤቱ እየሄድን ሳለ የመሄዱን ሃሳብ ድንገት በመተው ውሃ በባልዲ ሞልተንና ተሸክመን ወደ ማደሪያ ዶርማችን ተመለስን:: ልብሶቻችንን አወላልቀን የዶርሙ መሃል- ለመሃል- መሃል ላይ በመቆም በባልዲ ጭነን ያመጣነውን ቀዝቃዛ ውሃ ገላችን ላይ እያፈሰስን ታጠብን.....ሳሙና ተለቀለቅን: እንደገናም ገላዎቻችን ላይ ውሃ ቸለስን:: ማደሪያ ዶርማችን ውስጥ ማለት ነው:: ሌሎቹ የዶርም ተጋሪዎቻችን ባካባቢው አልነበሩም:: ዶርም ውስጥ ገላችንን ለመታጠብ ያነሳሳንን ምክንያት በትክክል ባላስታውሰውም ና አብይ የሚሰማውን ባላውቅም ያደረግነውን ነገር ለብቻዬ በተደጋጋግሚ እያሰብኩ ከመሳቄ የተነሳ ጭንቀቴ ቀለል እንዳለልኝ ግን እርግጠኛ ነኝ........

Sunday, September 27, 2015

ቅዳሜ ህዳር 12 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 8 ሰዓት ከ 32 ደቂቃ

የህዳር ትዝታ

ህዳር...ህዳር.. መልካም ወር...ደስ የሚል ወር ...የፍቅር ትዝታ ወር:: 

አሁን ካለሁበት ይበልጥ ልጅ እግር በነበርኩበት የ1982ቱ የሐይስኩል መጨረሻ ዓመት ላይ የተከሰተውን ህዳር የማስታውሰው ለህዳር ሚካኤል እናቴ ግቢያችንን አፅድታ የከመረችውን ጥራጊ ቆሻሻ ስታነደው አየሩን በሚያጥነው ጭስ ብቻ አይደለም:: ልቤን ለመጀመሪያ ጊዜ በማላውቀው አዲስ አይነት የስሜት ዑድ ባጠነችው ቀይ ባለረዥም ፀጉር ሴት ልጅም ጭምር እንጂ......ታሪኩ ከተሰማኝ ስሜት ዘልቆ ብዙም የተራመደ ባይሆንም ስሜቱ ራሱ ግን እንደ ጥሩ ሽቶ መአዛውን በውስጤ ተክሎ አልፉዋል:: ዛሬ ታዲያ ያን የህዳር ስሜት የምታጭር የጅጤሳ እንስትጋ አጠር ያለ ቆይታ አጋጠመኝ::

እንዳጋጣሚ ሆኖ ዛሬ አመሻሹ ላይ የኢትዮጵያው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ጅጤሳ ብቅ ብለው ነበር:: ስለዚህም በርካታ የጤና ሳይንሱ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ሰራተኞችና ተማሪዎች በመመረቂያዋ ስታዲዮም ተገኝተው ነበር:: እኔም ሄጄ ነበር:: በወቅቱ ፈንጠር ብለው ወደሁዋላ ከቆሙ ስዎች ጋር ተቀላቀልኩ:: በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ይህች ከላይ የጠቀስኩዋት የጅጤሳ እንስት  አጠገቤ መጥታ ቆመች:: በአይን ባውቃትምና ሰላም ብላትም ቀረቤታ ግን አልነበረኝም:: አሁንም ሰላም ብያት አይኔን ጳጳሱ ወዳሉበትና ለመናገሪያ ወደተዘጋጀው መድረክ አዙሬ መቆሜን ቀጠልኩ:: ወጣቷ እንስት በራሷ አነሳሽነት ወሬ ጀመረች:: ያልጠበኩት ቢሆንም ለወሬዋ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት ተሰምቶኝ ይሁን በሌላ ምክንያት እኔም ማውራት ጀመርኩ:: እሱዋ መቼም ስታወራ ድምፁዋ ዝግ ያለና በእርጋታ የሚወጣ ለስላሳና ቀጭን ነበር:: ለጆሮ ደስ የሚል...አንድ አንድ ስንባባል የደመቀ ወሬ ውስጥ ገባን:: ከድምፁዋ ማማር በላይ ጨዋታዋ ደስ አለኝ:: እንዴ??? አልኩ በልቤ:: በቃ ልክ እሱዋን! ማለቴ ከላይ ቀይ ባለረዥም ፀጉር ወጣት ሴት ያልኩዋትን...ያ በልቤ ውስጥ እንደ መልካም ሽቶ መአዛ ተከድኖ ተቀምጦ የነበር ትዝታ ተከፈተ:: ትክክለኛው ህዳር ህዳር ሸተተኝ: ማለቴ ፍቅሩ-ህዳር...ባለ መልካም መአዛው ህዳር...

አቡነ ጳውሎስ ወደ መድረክ ወጡና አስተማሩ ...ጮህ ብለው ሁሉ ተናገሩ ..የሰማቸው የለም:: የጅጤሳዋ እንስት ወጣት ከዚህ በፊት ታውቀኝ እንደነበረ ሆና ማውራቱዋን ቀጠለች...እንዲህ ነችና!


ከአቡኑ ዝግጅት በሁዋላ ታዳሚው ሲበተንና ወጣቱዋ እንስትም ጥላኝ ስትሄድ የኔ ልብ ደግሞ ተበታተነ:: ባዮኬሚስትሪ ለማጥናት ወደ ሌክቸር ሆል መሄድ ሲገባኝ ወደ ዶርሜ ሄድኩ....የተረበሸ አእምሮ ለማስታመም........

Tuesday, September 15, 2015

ሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 1985 አ.ም.  ከምሽቱ 7 ሰዓት ከ 11 ደቂቃ
የኔ ውድ በየቀኑ ከሚከሰቱትና ከሚያጋጥሙኝ በርካታ ክስተቶች አብዛኞቹን ከቁጥር ባላስገባቸውና ባላስተውላቸውም የተወሰኑት ግን ለማመን እስከሚያዳግተኝ ድረስ የሚገርሙኝ ናቸው:: እንደዚህ አይነቶቹ ክስተቶች ያጋጣሚ ብቻ እንዳልሆኑ ለልቤ ዘወትር ይሰማዋል::  ዛሬ ታዲያ እንዲህ ልል የቻልኩት ለምን ይመስልሻል? ነገሩ እንዲህ ነው....በሕቡዕ-ጠማማው መምህር  ምክንያት የማይመቸኝና የሚጎረብጠኝ የፊዚዮሎጂ ትምህርት ግማሽ ሴሚስተር ፈተና ነገ ስለሆነ ሰሞኑን እንደመስሎቼ ሁሉ ሌላውን ትምህርት ወደ ጎን በመተው እሱ ላይ ብቻ ለማተኮርና ዘለግ ያለ ንባብ ለማድረግ ሞክሬ በቅጡ አልተሳካልኝም ነበር:: እናም ስለፈተናው ባደረብኝ ስጋት የተነሳ ምነው በቀረ እያልኩ በሆዴ ከመቶ ግዜ በላይ አሰላሰልኩ:: ታዲያ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ዛሬ ጠዋት ራሱ ሕቡዕ-ጠማማው መምህር ፈተናው መቅረቱን ለሁላችንም ነገረን:: አንዳች ከትከሻዬ ላይ ዱብ ሲል በእርግጥ ተሰምቶኛል:: ፈተናው በአንድ ሳምንት ተላለፈ:: እግዚአብሔር ይመስገን.....


ሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 1985 አ.ም. 
ነገ ደግሞ እኔ የምወደውና ከልቤ የምመሰጥበት የአናቶሚ ትምህርት የቃል (oral exam) ፈተና ይጀመራል በመባሉ እገሌ ከገሌ ሳይል መላ ፒሲዋን የአናቶሚ ደብተሩና ማስታወሻው እንዲሁም ስዕሉ ላይ አድፍጧል:: የዶርሜ አባላት በሙሉ የሉም:: እንደታዘብኩት ከሆነ ሌክቸር ላይ መገኘት ካቆሙ የሰነበቱም አሉ::  ይህ እንግዲህ ለግማሽ ሴሚስተር ፈተና ማለት ነው:: ታህሳስ ውስጥ ዋናው ፈተና ሲመጣ ምን ማድረግ ያቆሙ ይሆን? ወደኔ ስመጣ ትናንት Thorax የተሰኘውን ቻፕተር በሙሉ ለማንበብ አቅጄ እንደተለመደው እቅዱን ከግብ ሳላደርስ ወደ መኝታዬ ያመራሁ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ከቀኑ አስር ሰዓት ጀምሮ በንባብ የወገምኩትን Abdomen የስተሰኘውን ክፍል እንደትናንትናው ሁሉ ሳልጨርስ ልተኛ ተቃርቢያለሁ:: ይህም እንግዲህ ለግማሽ ሴሚስተር ፈተና መሆኑን ልብ በይ:: ነገ እኔም እንደ አንዳንድ ከላይ እንደተጠቀስኩዋቸው ወገኖቼ ሁሉ ምንም አይነት ሌክቸር ላይ ላለመገኘት ለውስጤ ቃል ገብቼለታለሁ:: እንደሌሎቹ በድጋሚ የማንበብ ዕድል ባይኖረኝ እንኩዋ አንድ ዙሩን ራሱ ጨርሼ ለማንበብ እሞክራለሁ:: የአናቶሚን ፈተና ሁኔታ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ፈተናው የቃል ፈተና መሆኑና ነገ የተወሰንነው ብቻ የምንፈተን መሆኑ ነው:: ነገ ያልደረሰው ለከነገወዲያ ማለት ነው:: ከነገወዲያ ያልደረሰው ለቀጣዩ ቀን... እያለ ይቀጥላል:: ነገ ማ እንደሚፈተን ማ እንደማይፈተን ማንኛችንም አናውቅም:: ስለዚህም ሁሉም የአጠናንን ፍጥነቱን የመተረው “ነገ እፈተናለሁ!” በሚል እሳቤ ነው::

ማክሰኞ ህዳር 1 ቀን 1985 አ.ም.

በጅማ ህወቴ ውስጥ እንደዛሬ ንዴቴ ጫፍ ላይ ደርሶ ምንም ነገር ለማድረግ እስካለመቻል ደርሼ አላውቅም:: ምክንያቱ እንዲህ ነው:: ባለፈው ማክሰኞ ይጀመራል ተብሎ የነበረው የአናቶሚ የቃል ፈተና በተባለው ቀን ሳይጀመር ቀርቶና በሶስት ቀን ዝግይቶ በቀን ለአምስትና ስድስት ልጆች ብቻ የሚደርስ ከመሆኑም ባሻገር አመራረጡ በዘፈቀደ ስለነበር እኔና ሌሎች ዘጠኝ ልጆች  ሳይቀናን ቀርቶ ስንገዋለል ወደ ዛሬ ደረስን:: ያናደደኝ ግን ይህ አይደለም:: ፕሮፌሰር ስላህ ከአስራችን ውስጥ አምስቱን ከፈተነ በሁዋላ የቀረነውን አምስት ልጆች ዛሬም ሳይፈትነን ቀረ:: እንደነገሩ ጥሎን ሄደ:: ካሁን ካሁን ስሜ ይጠራል እያልኩ ጆሮየንና አይኔን ማቁልጭልጬ አልጠቀመኝም:: ሳምንቱን ሙሉ አናቶሚ ላይ ብቻ ተኝቼ መክረሜ አበሳጨኝ:: በገንኩኝ:: አረርኩኝ::  የአምስታችን የቀረነው ልጆች ተራ ከሁለት ቀን በሁዋላ ሐሙስ እንደሆነ ተነግሮናል:: እስከዚያ ስንቱን እረሳው ይሆን? የፈለገው ይሁን እንጂ ካሁን በሁዋላ ለአናቶሚ ቅንጣት ታክል ደቂቃ አላባክንም! የሚገርመውና የሚያስፈራው ሀቅ ሌሎቹ የተፈተኑት ባገኙት እፎይታ በመንተራስ ልሎች ትምህርቶችን በእርጋታ ማጥናት መቀጠላቸው ነው! ይህ በእውነቱ አድልዎ ነው:: ምን በደልን? ምን አደረግን?

............የኔ ውድ ብታምኚም ባታምኚም በዚህ ብስጭት ውስጥ ሆኜ በዶርም ቁጥር 207 መስኮት አሻግሬ ሙሉ ጨረቃን በሰማያዊው ሰማይ ላይ ተንሳፋበት አየሁዋት:: በዚህም የተነሳ በድገት ፍቅር ፍቅር አለኝ:: በምልሰት የበለጠ ልጅ እግር ወደነበርኩበት ወደ ህዳር 1982 አ.ም. ሄጄ አንድን ነገር አስታወስኩ ....የወጣት ትዝታ...መልካም ትዝታ................

Monday, September 7, 2015

ሰኞ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ 49 ደቂቃ

በዚህ ቀን ቀን ሞቃት ማታ ማታ ደግሞ ቀዝቃዛ: ደረቅና ነፋሻማ በሆነ ሰሞን የፒሲዋን ሂደት ጫን እያለ መምጣቱ በብርቱ ተሰምቶኛል:: እሰከ ምሽቱ ሰባት ሰዓት በንባብ ተግቼ እቆይ ዘንድ አልሆነም:: ይህም በውስጤ ቅሬታን ፈጥሩዋል:: በእርግጥ ከቅሬታው ይልቅ ድንጋጤዬ አይሏል ብል ይሻል ይመስለኛል...ነገ ጠዋት እግዜር ከፈቀደ በማለዳ ተነስቼ ያሉኝን ጥቂት ካልሲዎች ውሃና ሳሙና አስነካቸዋለሁ ብያለሁ:: ደህና ያሳድረኝ..

ሐሙስ ጥቅምት 12 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 7 ሰዓት ከ 19 ደቂቃ

የኔ ውድ አንድ በጣም የምቀርበውና የምወደው አሁን ባላወራውም ታሪኩ ከኔ ታሪክ ጋ የተሳሰረ ተስፋሁነኝ የሚባል ባልንጀራዬ የአንደኛ ዓመት የህክምና ትምህርቱን በደህና ውጤት አጠናቀቀ:: በዚህም በእውነቱ ከልቤ ደስ አለኝ:: ነገር ግን ደግሞ አንድ የሚያሳዝን ዜና ሰማሁ:: አንዲት ገነት የምትባል ትንሽ ትንሽ የማውቃት የተስፋሁነኝ ባች አባል የሆነች ተማሪ ውጤቷ ከበቂ በታች ነው በሚል ከጤና ሳይንሱ እንድትባረር ተወሰነባት:: ይህች ቁመተ ለግላጋና ዝምተኛ ወጣት ሴት ዛሬ ምሽት ላይ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች በተዘጋጀ የቅዱስ ሚካኤል መንፈሳዊ ፕሮግራም ላይ ተገኝታ በበዚያ  ለተሰበሰብነው እድምተኞች ሁሉ አንድ አጠር ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አነበበች:: መቼም ብርቱና ሃይማኖተኛ ነበረች:: በተወሰነባት አስከፊ ውሳኔ በልቧ እንደምታዝን ባስብም : በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆና ከታዳሚ ፊት በመቆም ይህን ማድረግ በመቻሏ ጥንካሬዋን አደነቅሁ::  በአንፃሩ ደግሞ እጅግ በመባረሯ በጣም አዘንኩ:: ከጤና ሳይንሱ አልፎ አልፎ እንደዚህ ተማሪዎች ሲባረሩ የሚሰማኝ ልዩ የሆነ የሽብር ስሜት ጎበኘኝ........

Sunday, August 30, 2015

እሁድ ጥቅምት 1 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 2 ሰዓት ተኩል 
ቀንም ሆነ ማታም ሆነ:: ፒሲዋን ሁለተኛ ሴሚስተር ከተጀመረ ልክ 2 ሳምንት:: ከመጀመሪያው ሳምንት ይልቅ በሁለተኛው ሳምንት በጥናትና በንባብ በርትቼ ነበር እላለሁ:: እርግጥ ነው አንዳንዴ ዋይትሃውስ ፎቅ ስር ባለው የተማሪዎች ቴሌቪዥን መመልከቻ አዳራሽ በኩል ሳልፍ በወቅቱ ከቴሌቪዥኑ በሚተላለፈው ዝግጅት ተስቤና ተሰናክዬ ወደ አዳራሹም ገብቼ ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዓት በመቀመጥ ከጥናቴ እዘናጋ ይሆናል:: ቢሆንም.....ቢሆንም.....የመኝታ ሰዓቴ እስካሁን ድረስ ከምሽቱ 7 ሰዓት ዝቅ አላለም:: ሳነብም የማተኮሬና ሃሳቤን የመሰብሰቤ ሁኔታ እስካሁን መልካም ነው::

በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ በሁሉም ደረጃ ያሉ የሁክምና ተማሪዎች በሙሉ በፍጥነት ወዲያና ወዲህ ሲሯሯጡ ማየት የየዕለት ክስተት ነው:: በቃ የሂወት ትንቅንቅ አካል ኖሮት ይታየኛል:: ታዲያ አይቼ አይቼ .....አይቼ ይገርመኝና የህክምና ተማሪ በመሆኔ እደሰታለሁ:: እንደውጭ ሰው ሆኜ ሳየው ውስጡ መልሶ መግባት ይናፍቀኛል:: ግን ደግሞ አለሁበት.....አይደል እንዴ?

ባለፈው ስለአለመጨነቄ ስናገር ነበር አይደል? ዛሬ ታዲያ ከኔ እጥፍ በጥፍ የማትጨነቅ የኛው ባች አባል መኖሯን ላስታውስሽ ወደደኩ:: ትዕግስት! ከኔጋ እንደማንኛውም ተማሪ እንቀራረባለን:: አንዳንድ ሁኔታዋ ያስገርመኛል:: ለምሳሌ በቁጥር በርከት ያሉ ሌክቸሮች ላይ አላየሁዋትም:: አንዳንዴ ደብተሬን ትዋሰኝና ገልብጣ ትመልስልኛለች:: ያንደኛውን ሴሚስተር ያሳለፈችው እንደዚህ ነው:: በጣም በጣም ዘና ብላ:: ታዲያ የባዮስታትስቲክስ አንደኛ ሴሚስተር ፈተና ውጤቷ B መሆኑ ገርሞኛል:: ማለቴ ትንቅንቅ ትይንት ውስጥ ላልታየ ተማሪ በጣም ጥሩ ውጤት ነው ...በተለይ ባዮስታትስቲክስ! ትዕግስት በዚህ ሴሚስተርም በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥላለች:: ሰሞኑን እንደውም አላየሁዋትም:: ተስፋ ቆርጣ አይመስለኝም::  አንድም ቀን ስታማርር ሰምቻት አላውቅም:: እንዲያውም የአንደኛ ሴሚስተር ፈተናዎቻችንን ያጠናቀቅን ለት እኔ በምሬት ስናገር ሰምታኝ “ ተው እንጂ አንድ ሴሚስተር መጨረሻ ላይ መድረስ ራሱ ቀላል አይደለም” ብላኝ ነበር........

ቅዳሜ ጥቅምት 7 1985 አ.ም.  ከምሽቱ 7 ሰዓት 10 ደቂቃ
የአናቶሚ ላቦራቶሪ ፕሪክልኒካል ተብሎ የሚጠራው ህንፃ ውስጥ በግራ በኩል ከዋናው ወለል በተወሰኑ ደረጃዎች ዝቅ ብሎ ይገኛል:: በፈለግነው ሰዓት እንድንገባ ተፈቅዶልናል:: እኔ አናቶሚ ላቦራቶሪ ውስጥ ቁጭ ብዬ ማጥናት ደስ ይለኛል:: ሰሞኑን ምሽት ላይ ከዚያ አልጠፋም:: ቸርነትና እመቤትም አብረውኝ ያመሻሉ:: ታዲያ ሁልጊዜ ቀን ቀን የምንማርባቸው አራት ሬሶች (cadavers) በነጭ ጨርቅ ተሸፍነውና በፀጥታ ተጋድመው ይታያሉ:: ፈፅሞ አይረብሹንም:: በሰፊውና በረዥሙ አናቶሚ ላቦራቶሪ ውስጥ አንደኛው ማዕዘን ጋር ካለው ጠረጴዛ ላይ ከቸርነትና ከእመቤት ጋር ሆነን የምናሳልፈው የጥናት ግዜ ባልፅፈውም ወደፊት የማስታውሰው ይመስለኛል.....


ዛሬ ታዲያ በሚገርም ሁኔታ በትዕግስት አናቶሚ ትምህርት ያለማቁዋረጥ ለሶስት ሰዓት አነበብኩ:: ሀቅ ልናገር ከተባለ ይህ በኔ የጥናት ሂወት ውስጥ ሁልጌዜ አይከሰትም:: ተቀምጦ ለረዥም ሰዓት ማንበብ? እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ በጣም በጣም አንዳንዴ (rare) ከመሆኑ የተነሳ ከዚህ በፊት ለሶስት ሰዓት ያለማቁዋረጥ ያነበብኩበትን ግዜ አስታውሰዋለሁ:: አንድ ግዜ ብቻ ነው የሆነው:: ባለፈው ዓመት አንድ ቀን ሳይኮሎጂ ትምህርት ሳጠና..በቃ! በተማሪነት ሄወቴ ስለራሴ በሂደት ከተገነዝብኩዋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ለንባብ ትዕግስት እንደሚጎድለኝ ነው:: ስለዚህ በየሃያና ሰላሳ ደቂቃው ለማንበብ የተቀመጥኩበትን ቦታ ለቅቄ ገለል ማለት ያስፈልገኛል:: ከአናቶሚ ላቦራቶሪው ጥናት እረፍት የማደርገው ወጣ ብዬ ከፕሪክሊኒካል ህንፃ ፊት ለፊት ካሉት ዛፎች ስር ራመድ ራመድ በማለት ወይም ቆሜ በዛፎቹ መካከል ጨረቃን ፍለጋ ወደሰማይ በመመልከትና ሲያጋጥም ደግሞ የጅማን ደረቅ የምሽት አየር በመማግ: ይሆናል.......

Tuesday, August 25, 2015

ጨረቃ
ወኔዬ አልቆ ተሙዋጦ 
መንፈሴም ደክሞ ተስፋ ቆርጦ
ብስጭት ገብቶኝ ሞትን ስሻ
መሄጃ አጥቼ መድረሻ
ወደበላዬ ስመለከት
ሰማይ ከዋክብት ወዳሉበት
አየሁ ጨረቃ መሃል ሆና 
ምድርን ስታደምቅ በብርሃኗ
እነሆም ተስፋዬ አንሰራራ
ልቤ ተነካ ባምላክ ስራ 
ብቻዬን እዳልሆንኩ ተገነዘብኩ
ነገን እያሰብኩ አሸለብኩ
(By Samson Haile)

ማክሰኞ መስከረም 19 ቀን 1985 አ.ም.  ከምሽቱ 6 ሰኣት ከ 13 ደቂቃ

ዛሬ ጠዋት ፊዚዮሎጂ ሌክቸር ከመውሰዳችን ቀደም ብሎ ፕሮፈሰር ማሂን ከግንዛቤ በማስገባት አንደሚጨንቀኝ አስቤ ነበር:: ግን ሳልጨነቅ ቀረሁና ያ ደግሞ አስጨነቀኝ:: እንዴት ሳይጨንቀኝ ቀረ? 
ለነገሩ ለማን ብዬ ነው የምጨነቀው? አንድ አስተማሪ ደበረኝና ምን ይጠበስ? 

በነገራችን ላይ ፒሲ ዋን ሁለተኛ ሴሚስተር በደንብ ተጀመረ:: ዛሬ አስከ ምሽቱ ሰባት ሰአት ለማንበብ እቅድ የነበረኝ ቢሆንም አሁን ደከመኝ: 47 ደቂቃ ሲቀር ማለት ነው.....

ውድ ማስታወሻዬ እኔ ካሁን ወዲያ ላንቺ የምነግርሽ የጨረቃን ድምቀት: የጸሃይን ጥልቀት: የዛፎችን ውዝዋዜና የነፋስን ሽውታ ነው እንጂ በቃ ጭንቀት አላወራም:: ኦ ጭንቀት ልኩ እንዴ? አላወራም ብዬ ስለሱ....

የግቢው አትክልተኛ አበቦቹን በደንብ እያሳመራቸው መሆኑን ተመለከትኩና  አንድ ላንቺ ማለት ያለብኝ ነገር ትዝ አለኝ:: "ጥሩ ቀለማትን ከማየት የበለጠ ምን ነገር አለ?" እላለሁ አንዳንዴ:: በእርግጥ በሙዚቃና በስነጽሁፍ ብደሰትም የሰዎች ስራ ከሆኑት ከነዚህ ይልቅ በተፈጥሮ ህብረ ቀለማት ና የወፎች ዝማሬ ይበልጥ የመደሰት ባኅሪ ያለኝ ይመስለኛል......

ሮብ መስከረም 20 ቀን 1985 አ.ም.
ዛሬ ማታ ከቤተመሃፍት ንባብ ለምስት ደቂቃ እረፍት ለማድረግ ወጥቼ ሳለ የኢንተርንሺፕ ሃኪም የሆነው አብርሃም ሻይ ገዛልኝና ከዚያ በሁዋላ ደስ እያለኝ ጠናሁ:: ቤተመጽሃፍቱ ሲዘጋ እንደተለመደው ወደ ሌክቸር ሆል ሄድኩ:: ወደዚያ እየሄድኩ ወደ ሰማይ ቀና ብዬ አየሁ:: ግማሽ ጨረቃ ትታያለች:: ልቤን በእርግጥ ደስ እንዳለው ይታወቀኝ ነበር:: ከዚህ በሁዋላ በሌክቸር ሆል ውስጥ በንባብ እስከ ምሽቱ 6 ሰኣት ከ40 ደቂቃ ቆይቼ ለመተኛት ወደ ዶርም ኣቀናሁ:: በመንገዴ ላይ እመቤት አብራኝ ነበረች:: ዝናብ እያካፋ የነበር ቢሆንም ርምጃችን የወትሮው ነበር.....

ሐሙስ መስከረም 28 ቀን1985 አ.ም. ከምሽቱ 7ሰኣት ከ 13 ደቂቃ
ዛሬ እንኩዋን የማወራው ነገር የለኝም:: ግን ጨረቃ በሙሉ ድምቀት በሰማያዊ ሰማይ ላይ እየታየች መሆኑን ሳልገልጽ መተኛት ከበደኝ:: ዶርም ቁጥር 207 ውስጥ አልጋዬ ላይ ነኝ:: የምጽፈው ማጣቴን ላልተኙ ጉዋደኞቼ እየነገርኩዋቸው ነው:: መንጌ ልጋው ውስጥ የገባ ቢሆንም አልተኛም:: የሆነ ነገር ይዞ ያነባል:: አባይም እንደዚያው:: አብይ ትንሹዋ ጠረጴዛ አጠገብ ሆኖ እያጠና ነው:: አሌክሱ አምሳሉ ሚሊዮንና ሃይሉ እንዲሁም ቤተማርያም እርግጡን ለመናገር ባልችልም እንቅልፍ ውስጥ ይመስሉኛል:: አባይነህ፥ አመንቴ ና አዳሙ የሉም:: ገና ኣልገቡም:: ውድ ማስታወሻዬ ደህና እደሪ:: ጉዋደኞቼም እንዲህ ይሉሻል.....

ባይ "እግዚኣብሄር ይመስገን"
መንጌ " God should be praised"
አብይ "ኑሮ መሮኛል"

Friday, August 14, 2015

እሁድ መስከረም 17 ቀን 1985 አ.ም.

ያባይ ልጆች መጡ እንደገና!
ግብፆቹ መምህራኞቻችን እረፍታቸውን ጨርሰው ጅማ እንደደረሱ ወሬ ሰማሁ:: “እሰይ!” ማለት ይገባኝ እንደነበር ባውቅም በነሲብ የተሰማኝ ስሜት ግን ወደ ግራ የወገነ የልብ መደናገጥ ነበር-ሀቅ ልናገር ከተባለ:: ወሬውን እንደ መልካም ወይስ እንደ መጥፎ ዜና መቁጠር እንዳለብኝ ማወቅ ሊሳኝ ዳዳኝ:: ማለቴ እኔም ሆንኩ ጉዋደኞቼ ከእረፍት መልስ በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ እየቦዘንን ስለነበር ግብፆቹ መጥተው ትምህርት መጀመሩ ደስ የሚል ቢሆንም የፒሲዋንን የጥናት ኃላፊነትና የጉሮሮ ለጉሮሮ ትንቅንቅ ግን እንዲሁ ተቻኩዬና እጆቼን ዘርግቼ አቅፈው ዘንድ የሚፈቅድ ልብ አልነበረኝም:: እናም በዚህ የአደይ አበባ ፍካት ጡዘት ላይ በደረሰበት የወርሃ መስከረም አጋማሽ ከባልንጀሮቼ ጋር በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥም ሆነ ከግቢው ውጭ መቦዘኑና መፈንጨቱ እንዲያው ትንሽ ቢቀጥል ደስ ባለኝ.....በአንደኛው ሴሚስተር ከነበረኝ ልምድ በመነሳት የፒዋንን እንደገና መጀመር ሳስበው እንደዚህ ካለ ፀደይ: እንዲህ ካለ በአበቦች ከታጀበ የበጋ መጀመሪያ: እንዲህ ካለ ነፃ ቡረቃ ተነጥቄ የዚህ ተቃራኒ ወደ ሆነ የኑሮ ጥቁር የምወሰድ መሰለኝ::: በቃ የክረምቱ ግዜ አበቃ......በቃ የፀደዩ ወራት አበቃ......ወርቅ ቢጫማውን የጅማ ፀሐይ ጥልቀት እንደልቤ ለመመልከት ዕድል ይኖረኝ ይሆን? ሙሉ ቀይ ጨረቃን በዛፍ ቅርንጫፎች መካከል ለማየትስ? የጅማን ደረቅ ምሽ ንፋስ ሽዉታና በሱም ምክንያት የሚወዛውዙትን ዛፎች ድምፅስ እሰማ ይሆን? በቃ ከዚህ በሁዋላ እኮ ታሰርኩ! ጎበዝ! በግብፆች ቁጥጥር ስር ልገባ ነው:: በተለይም በማይመቸኝ በፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰር ማሂ  ስር! ያባይ ልጅ ያለህ! 
የኔ ነገር ለካ እነሱም ካባይ ናቸው.....

የኔ ውድ የሆንሽ ማስታወሻዬ.... ይልቅ አሁን ይህን አይነት ወሬዬን ልተውና ትናንት እኔና ጉዋደኞቼ የመስቀል ዋዜማን እንዴት እንዳከበርን ለተርክልሽ......


እኔ ጉዋደኞቼና መስቀል

በነገራችን ላይ በዶርም ቁጥር 207 ውስጥ ያለነው ልጆች 10 ስንሆን ክፍሉ ግን ለ12 ልጆች ታስቦ የተሰራ ስለነበር 12 ሎከሮች አሉት:: ከሁለቱ ትርፍ ሎከሮች ውስጥ አንደኛው ዘወትር ክፍት የነበረ ሲሆን አንደኛው ግን ለብዙ ጊዜ የተቆለፈ ነበር:: እኔና ጉዋደኞቼ ታዲያ “እስቲ ውስጡ ምን ይኖር ይሆን?” በሚል ጉጉት ትናንትና ከፈትነው:: በርከት ያሉ ልብሶችና ጥቂት አንሶሎች ደብተሮችና ሌሎቹም ቁሳቁሶች የሎከሩን መከፈት ተከትለው ተንከባለሉ ! የሁላችንም አይንና ልብ ያረፈው አንሶላውና ልብሶቹ ላይ ነበር:: ጅማ ገበያ ላይ ያላቸውን ዋጋ ጠንቅቀን እናውቅ ነበርና:: በዚያ ላይ የመስቀል ዋዜማ ነው:: ወይ የእግዚአብሔር ነገር! የማን ይሆን ልብሱ? የሁሉም ጥያቄ ነበር:: እኛ እዚህ ዶርም ከመግባታችን በፊት ይኖሩበት የነበሩት ያለፈው ዓመት ኢንተርንሺፕ ሀኪሞች እንደነበሩ በሰከነ ውይይት ደረስንበት:: አሁን ተመርቀው በግቢ ውስጥ የሉም:: ወደ ሥራ ዓለም በየአቅጣጫው ተበታትነዋል:: አሀ! የዚህ ልብስ ጌታ ባሁኑ ሰዓት ሃኪም ሲሆን በወር 835 ብር እየበላ ይሆናላ ይሄኔ! በዚህ ነፃ እሳቤ በመታገዝ በቀጣዮቹ ሰዓታት ውስጥ አንሶላውና ልብሶቹ ወደ ገንዘብ ተቀየሩ:: ደንገዝገዝ ሲል የጅማን ከተማ መሃል ለመሃል ሰንጥቀን ጠለቅንባት.....እኔና ጉዋደኞቼ:: በታክሲ  ጩኸት: በሙዚቃ ቤት ሜጋ ስፒከር ድምፅ እንዲሁም ባመትባል ዋዜማ የከተሜ ግርግር ታጅበን ከፈረንጅ አራዳ መልስ : በየጆካ ሆቴል ጀምረን: ካንዱ ቡና ቤት ወዳንዱ እየተሸጋግርን እጅግ በጣም የምንወደውን ቀይ ቪኖ ስንጠጣ ስንደንስና ስንወራጭ አስከ እኩለ ሌሊት በስቲያ አመሸን.... ያ ያምና ኢንተርን የዛሬ ዶክተር እግዜር ይስጠው:: እንጀራ ይውጣለት:: 

የምሽቱ አየር ደረቅና እጅግ በሚመች መልኩ ቀዝቀዝ ያለ ስለነበር ካንዱ ቡና ቤት ሞቅ ብሎን ወጥተን ወደሚቀጥለው እስክንደርስ ሞቅታው በረድ ይልልን ነበር....