Wednesday, March 26, 2014

ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፬

መጋቢት ፩፮ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም.

ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፬


አትሸኙንም ወይ ልንሄድ አይደለም ወይ

በዚህ ቀን ጠዋት ይጀመራል ተብሎ የታሰበው ጉዞ ሳይጀመር ቀረ:: ተማሪውም ሆነ የጤና ሳይንሱ አካባቢ ነዋሪ የአውቶቡሶቹን መነሳት እየተጠባበቀ አርፍዷል:: ለተማሪዎች ከመሄድ ሌላ ምንም አማራጭም ሆነ ግቢው ውስጥ በመቅረት የሚደረግ ነገር አልነበረም:: የጤና ሳይንሱ ግቢ እንቅስቃሴ ተለውጧዋል::ወደ ስልጠና እንድንሄድ የተወሰነ መሆኑ በዲኑ ከተነገረበት ቅፅበት አንስቶ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ምንም ስፍራ እንደሌላቸው የሚያመላክቱ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል:: የጤና ሳይንሱ ሰራተኞችም ከተለመደው የለት ተለት ሂደት በተለዩ ስራዎች ተጠምደዋል:: አልጋዎች ና ቁም ሳጥኖች እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ መገልገያ አቃዎች በነጠላና በጅምላ ወደ ወደ መጋዘን ሲገቡ ተመለከትኩ:: ለወትሮው ውር ውር ሲሉ ይታዩ የነበሩ መኪኖች የተበላሹ ይመስል ያለእንቅስቃሴ ተደርድረው ይታያሉ:: የጅማ እርሻ ኮሌጅ ተማሪዎችም በተመሳሳይ ቀን ና ሰዓት ከተማውን የሚለቁ መሆናቸው ስለታወቀ እንቅስቃሴ የምንጀምርበትን ሁኔታ ለማየት ብዙ የከተማው ሕዝብ በየመንገዱ ተኮልኩሏል:: 

ከጅማ በጠዋት በመነሳት ወሊሶ ከተማ ላይ ምሳ ለማድረግ ነበር የታቀደው:: ይህ ሊሆን ስላልቻለ ለመጨረሻ ግዜ በ ጤና ሳይንሱ ምግብ ቤት ምሳ ተመገብን:: ወጥ ቤቷ አይኖቹዋ እንባ እንዳቆረዘዙ እጇ እየተንቀጠቀጠ የጨመረችልኝ የዛሬው ወጥ በሚገባ ተቁላልቶ ና ትክን ብሎ የተሰራ ምስር ክከ ወጥ ነበር:: ከምሳ በሁዋላ ብዙም ሳንቆይ የሚወስዱን አውቶቡሶች ጥሩምባ እያሰሙ ወደ ጤና ሳይንሱ ቅጥር ግቢ ተከታትለው ገቡ:: ድንገት ጫጫታና ግርግር በዛ:: ሁሉም ተማሪ በአንድ ግዜ እቃውን እየተሸከመ ወደ አውቶቡሶቹ መሮጥና መጠጋት ጀመረ:: እኔም እንግዲህ ሰው እንደሚያደርገው አደረግሁ..አባቴ እንደመከረኝ:: በግርግሩ መሃል ሃሳቤን ለመሰብሰብና አካባቢዬን ለመቃኘት ሞከርኩ:: አንዳንንድ ተማሪዎች በአካባቢው እንደሌሉ አስተዋልኩ:: ለምሳሌ አራቱ የኛ ባች ሴቶች: አራቱ ኤርትራውያን: ሌሎችም....የሉም:: ኦ! የቅርብ ጉዋደኞቼ  በሙሉ አካባቢዬ አሉ:: ተመስገን...ግን ፊታቸውን ስመለከተው አብዛኛዎቹ ቀፍፎአቸዋል:

አውቶቡሶቹ በተማሪዎች መሞላት ጀመሩ:: የጦሩ አባል  እንዲሁም ከኛጋር የህክምና ተማሪ የሆነው ሻምበል ጌታቸው በነገረልን መሰረት የአንደኛ ዓመት የህክምና ተማሪዎች በቁጥር አምስት አውቶቡስ ላይ ተሳፈርን::

ከቀኑ ሰባት ሰዓት አውቶቡሶቹ የጤና ሳይንሱን ግቢ እየለቀቁ መውጣት ጀመሩ::  ሲመጡ እንዳደረጉት ጥሩምባቸውን ለቀቁት...ቢፕ...ቢፕ...አንዳንዶቹ አውቶቡሶች ውስጥ ያሉት ተማሪዎች "አትሸኙንም ወይ ልንሄድ አይደለም ወይ" እያሉ የዘፍኑ ነበር:: ይህም መሬት ላይ ያለውን የከተማውን ሰው ግርግር ጨመረው:: ድምፆች በረከቱ:: ሩጫ ና ጫጫታ በዛ........ከወራት በፊት ጨቅላ ወንዶች የታጨቁባቸው አውቶቡሶች ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ሲንቀሳቀሱ ና የከተማው ሰውም አውቶቡሶቹን እየተከተለ ሲሮጥ  ና ሲያለቅስ እንዳላየሁ እኔም አውቶቡስ ውስጥ ተቀምጬ መሬት ላይ ያለ ሕዝብ ሲከተለኝ አየሁ:: ብዙ የሚያለቅሱ ኢትዮጵያዊ ሴት ፊቶች አየሁ:: እኔም እንባዬ መጣ........

የጤና ሳይንሱ ሰራተኞች እያለቀሱ በግቢው ተሽከርካሪዎች በመሆን እስከ ሰርቦ ከተማ ድረስ ሸኙን:: አውቶቡስ ውስጥም ሆነ ከአውቶቡስ ውጭ የነበረው ግርግር የሰርቦን ከተማ እንዳለፍን እየበረደ መጥቶ መጨረሻ ላይ ቆመ:: እኛም በየተቀመጥንበት የየግላችንን ወሬ ማውራት ጀመርን:: ተዳክመንም ነበር....

በቁጥር አምስት አውቶቡስ ውስጥ የነበሩ ሹፌሩ አካባቢ እነ ሻምበል ጌታቸው: በላይነህ: ፍቅሩ: ኃይሉ: አንበሳው: አያሌው: ፍፁም: ቸርነት: ና ሌሎችም........እኔ ወዳለሁበት አካባቢ ደግሞ: እነ መንግስቱ:አብይ:ሚሊዮን: ማስረሻ: ና አምሳሉ ....... ወደ ሁዋላ አካባቢ እነ ያሬድ: አይዘን አወር: ዘመኑ ይታዩኛል:: ከሌላ ደፓርትመንት አስፋው: አረጋ: ፋሲልና ሚፍታህ.......ብዙዎቻችን አንድ ፍሬ ጨቅሎች ነን...

ሹፌሩን በአውቶቡሱ ካሴት ማጫወቻ ዘፈን እንዲያሰማን ጠየቅነው:: አንድ ቆየት ያለ የአስቴር አወቀ: የጌታቸው ካሳ: የብርቱካን ዱባለ ና አንድ የሱማሌኛ ዘፈን እያፈራረቀ አሰማን::

አውቶቡሶቹም ሸመጠጡ....

Wednesday, March 19, 2014

ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፫



መጋቢት ፩፮ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም.

ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፫

መሄዴ ነው እኔ መሰናበቴ ነው
በሉ ደህና ሁኑ አመሰግናለሁ 

ከዛሬው ነገሬ በፊት: ትናንት ወደ አመሻሹ ላይ በስልክ ከቤተሰቤ ጋ ለመገናኘት ችዬ ነበር:: አንድ ጅማ ያሉ የማውቃቸው ሴትዮ እንደምንም ብለው ደውለው ና ተደዋውለው ከአባቴ ጋ አገናኙኝ:: ለአባቴ ትናንት ውሳኔ ላይ ሳይደርስ ስለተቁዋጨው ስብሰባ አወራሁለት:: ለመወሰንም እንደተቸገርኩ ነገርኩት:: በተቻለ መጠን አብዛኛው ተማሪ የሚያደርገውን እንዳደርግ መከረኝ:: ችግሩ.. ...እንዴት ነው አብዛኛው ተማሪ ምን እንዳሰበ ማወቅ የሚቻለው?

ሌላ ደግሞ ከዛሬው ነገሬ በፊት....ትናንትና ማታ ከዚህ በፊት አድርጌው በማላውቅ ሁኔታ መጠጥ በብዛት ጠጥቼ ነበር:: ደግነቱ ከጉዋደኞቼ ጋ ነው:: በአምሳሉ ጋባዥነት ወደ ከተማው መሀል ወርደን ነበር:: በርከት ያለ ጠርሙስ ወይን ጠጅ ጠጥተን ስናበቃ ጂን በመለኪያ ጨመርንበት:: መጠጥ ባፈዘዘው ዕይታና ባንገዳገደው እርምጃ ወደ ጤና ሳይንሱ ግቢ ስንመለስ ሌሎች በርካታ ተማሪዎች በተመሳሳይ አንዳንዶቹም በላቀ ስካር ዉስጥ ሆነው በግቢው መንገዶች ላይ ከላይ በመቆንጠጫ ተይዞ እንደተሰቀለ ልብስ ሲንገዳገዱና ሲወድቁ አስተውያለሁ:: አረ ጭፈራ ሁሉ ነበር:!! የተስፋ መቁረጥ ይሁን የቆራጥነት አላውቅም:: እኔ ና ጉዋደኞቼ በበኩላችን  በጋራ ተስፋ የቆረጥን ይመስለኛል:: ከ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ የጀመረ አንድ ግዙፍ  ሆታ የጤና ሳይንሱን ግቢ ከ መመገቢያው አዳራሽ እስከ ዋይት ሃውስ ድረስ አናጋው:: የሚዘፈነው ዘፈን ስለምን እንደነበር ወይም ማን የዘፈኑ አውጪ እንደነበር በቅጡ ማስታወስ አልቻልኩም:: ግን "የእርግብ አሞራ" አይነት ይመስለኛል:: በእርግጠኘት የማስታውሰው ግን በመጠጥ ስሜት ከብዙ በቅርብ ከማላውቃቸው ሌሎች ሰካራም ተማሪዎች ጋር ልክ ተጠፋፍቶ እንደተገናኘ ጉዋደኛማች ስተቃቀፍ ነበር:: ሌሎቹም እርስ በርሳቸው ይተቃቀፉ ነበር:: ለማልቀስ የሚዳዳውም ነበር:: በሆታውና በዘፈኑ ውስጥ የተመለከትኩት አብዛኛው ጨቅላ ና የፍሬሽ ማን ተማሪ መሆኑን በምልሰት ልብ ብያለሁ:: ምን እናውቃለን ገና ልጆች ነን:: እኔ አስራ ስምንት አመት የሚሆነኝ በሚቀጥለው ወር ነው:: ነባር ተማሪዎች ዶርማቸውን ዘግተው እንደዶሮ በግዜ ተኝተው ወይም ሳይተኙ አልጋቸው ላይ ተጋድመው ነበር:: ወደ ብላቴ የመሄዱን ነገር በአንደኝነት የጠሉት እነሱ ይመስሉኛል:: እስካሁን በዘመቻው ዙሪያ በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ደፍረውና ፊት ለፊት ወጥተው ሲከራከሩ ነበር::

አሁን ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት  ከሩብ ይላል ሰዓቴ:: ከትናንትናው መጠጥ የተረፈውን ራስ ቅሌን  ተሸክሜ  ከ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ መኝታ ቤታችን አጠገብ በስተግራ ያለ ሌላ አዳራሽ ውሃ ልክ ላይ ቁጭ ብዬ ወደ ብላቴ ይዘውን የሚሄዱትን አውቶቡሶች እየተጠባበኩኝ ነው:: በሁዋላ የሚሆነው ይሆናል ለማንኛውም ሁሉም ሰው ሊያደርግ እንደተዘጋጀው ተሳፍሮ መሄድ ነው:: ግቢው ውስጥ መቅረትም የሚቻል አልመሰለኝም:: እንቅስቃሴ ሁሉ ቆሙዋል:: እንደገባኝ ከሆነ አውቶቡሶቹ በአዲስ አበባ በኩል ማለፋቸው ግድ ነው::  እናም እዚያ ስንደርስ........የሚሆነው አይታወቅም... ወደ ብላቴ ለመሄድ ወይም ላለመሄድ ለመወሰን አሁንም ግዜ አለ:: ብዙ ተማሪ እንደአዚህ እንደሚያስብ አልጠራጠርም::  

.....ከተወስኑ ደቂቃዎች በፊት ስታዲዮሙ ውስጥ ለተሰበሰብን ተማሪዎች ዲኑ መጠነኛ የመሰነባበቻ ንግግር አድርገው ነበር:: "ውድ ተማሪዎች ኢንስቲትዩታችሁን አትረሱዋት ዘንድ ይህ የማስታወሻ አርማ ከናንተ ጋር ይሁን ብለው ለተማሪዎች ተወካይ አርማውን ሰጡ:: ንግግራቸውን ቀጠሉ "በውነቱ አይደለም ይህን አጋጣሚ አንፈልገውም ነበር:: ግን ሆነ:: ምንም ማድረግ አንችልም...ውድ ተማሪዎች እኛ ምን ግዜም አንረሳችሁም:: በሄዳቹበት ሁሉ ስለናንተ ሁኔታ እየመጣን ለመጠይቅ እንሞክራለን..........ወዘተ......


Wednesday, March 12, 2014

ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፪

መጋቢት ፩፭  ፩፱፰፫ አ.ም.  ስድስት ሰዓት ከ ሃያ ሰባት ደቂቃ

ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፪

"It's been too hard living, I am afraid to die
Cos I don't know what's out there beyond the sky"
From Sam Cooke's song A change is gonna come

ከትናንት ወደዛሬ የተማሪዎች ስሜትና ባጠቃላይ ነገሮች ከረር ና መረር እያሉ የሄዱ መስሎ ተሰምቶኛል:: በየደቂቃውና ሰኮንዱ በተማሪዎች ውስጥ አዳዲስ ጥያቄዎች ይፈጠራሉ:: ዛሬ ጠዋት ለሀገራችን የምንዘምት ከሆነ እኛም የምንጠይቀው ጥያቄ ይሟላልን የሚል አስተያየት ሰማሁ:: ሌሎችም ብዙ አይነት ጥያቄዎቹ እየተንሸራሸሩ ነው::  የ ጅጤሳ ዲን የሆኑት ዶክተር ተክለ ፅዮን የመሩት አጠቃላይ ስብሰባ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ በመሰብሰቢያው አዳራሽ ዉስጥ ተደረገ:: በርካታ ጥያቄዎች ከተማሪዎች ወደ ዲኑ ጎረፉ:: የጥያቄዎቹ ይዘት ማሰልጠኛ የምንሄድበት ቀን ይራዘም ከሚለው ለዘብተኛ መሰል አስተያየት ጀምሮ  ወደ ማሰልጠኛ ከመሄዳችን በፊት የደርግ ባለስልጣኖች ይውረዱ እስከሚለው ንዴት የተቀላቀለበት ጥያቄ ይደርሳል:: በሕልሜ ነው የመሰለኝ:: ዲኑ አብዛኛውን ጥያቄ አልመለሱትም:: በእርግጥ "በቀጥታ ለበላይ አካል አስተላልፋለሁ" የሚለውን ሐረግ ወደ መቶ ግዜ ደጋግመው ተናግረዋል:: ለማንኛውም በስብሰባው መጨረሻ ላይ በአዳራሹ የተሰበሰቡት የጤና ሳይንሱ ተማሪዎች በሙሉ ባንድነት ባሰሙት ጩሄትና ጭብጨባ  የታጀበ አስተያየት በአንድ ነባር ተማሪ ተወረወረ::  "የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዘመቱ ስለመሆናቸው በቂ ማስረጃ እስካላገኘን ድረስ የትም አንንቀሳቀስም!!" ከ ግማሽ ሰዓት በሁዋላ ማለትም ከቀኑ ሰባት ሰዓት  በዚሁ አዳራሽ ውስጥ እንደገና ስብሰባ ይካሄዳል:: ዶክተር ተክለፅዮን ከመንግስት ምክር ቤት ጋ ተነጋግረው የሚሰጡንን ምላሽ ለመስማት ይመስለኛል.....

ከጠዋት ጀምሮ በሰማይ ላይ የተንጣለለው ደመና አልገፈፈም:: እኔን ጨምሮ ብዙ ተማሪዎች ወደየት እንደምንሄድ አንወቅ እንጂ እቃችንን በሻንጣ ሸክፈናል:: አንዳንዱ ተማሪ የተጠቀጠቀ ሻንጣ ይዞ ከ ጤና ሳይንሱ ግቢ ሲወጣ ይታያል:: እንደማስበው ለክፉም ለደጉም ጅማ ያለ ወዳጅ ዘመዱ ጋ ውድ የሚላቸውን እቃዎች ለማኖር ነው:: ከዚህም በላይ ቅድም ስብሰባው ላይ ከጥቂት አልባሳትና ጫሞች በቀር የምትይዙት ዕቃ እንዳይኖር ተብለናል:: 

በያንዳንዱ ልብ ውስጥ ያለውን መገመት ቢያያዳግተኝም ቢያንስ ሁሉም የማየው ፊት የከፋውና የቀፈፈው መሆኑን ግን እርግጠኛ ነኝ:: እኔ ራሴ ቀፎኛል:: እንደበፊቱ ፈታ ልል አልቻልኩም:: ተማሪዎች በየኮርነሩና ጥጋጥጉ ተሰባስበው የሚያወሩት ስለዘመቻው ብቻ ነው::  በአንዳንዶቹ ስብሰባዎች ላይ እኔም ራሴ እየተካፈልኩ እንደሌሎቹ ሁሉ አስተያየት እሰጣለሁ:: እንደአብዛኛው ተማሪ ሁሉ የዘመቻውን ሃሳብ አልደገፍኩትም....

ከቀኑ ሰባት ሰዓት ደረሰ:: ስብሰባም ተደረገ:: ስለስብሰባው ዝርዝር መግባት ሳያስፈልገኝ ማለት የምችለው ነገር ዶክተር ተክለ ፅዮን እኛን ከዘመቻ ለማስቀረት የሚያስችል ኃይል አልነበራቸውም:: ከመንግስት ምክር ቤት ያመጡት ምንም አይነት ምላሽ አልነበረም:: በቃ በማንኛውም ሁኔታ ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ እንድንሄድ ተውስኗል:: የወሰነውን እግዚአብሔር ይይለት! ስብሰባው ያለምንም መደምደሚያ ተበተነ:: አሁን የምሬን ነው: ልቤን የሆነ የተደበላለቀ ስሜት ተሰማው:: ከዚህ በሁዋላ በእርግጥም ውሳኔው የግል እንደሆነ ገባኝ:: የቡድንም ሆነ አጠቃላይ ስብሰባ ዋጋ የለውም:: ምን ባደርግ ይሻለኛል? ምናልባት አብዛኛው ተማሪ ወደሚለው ማድላት ሳይሻለኝ አይቀርም:: ግን ሌላው ተማሪ የወሰነውን እንዴት ማወቅ ይቻላል?  ለመወሰን ተቸገርኩ:: ምክንያቱም መሄድም መቅረትም አደገኛ ነው:: 

በዚሁ ቀን ምሽት ላይ ወደመመገቢያው አዳራሽ ከጉዋደኞቼ ጋር እራት ልንበላ ስንገባ ወጥ ታወጣልኝ የነበረችው ሴት ፊቱዋ ሃዘን የተላበሰ ብቻ ሳይሆን አይኑዋ አብጦ ስታለቅስ የነበረ መሆኑን ይናገራል:: ይህንን ብረዳም ዘወትር ከወጥ ቤቶቹ ጋር እንቀላለድ ስለነበር " እንግዲህ የመሰነባበቻውን ከወጡ በደንብ" አልኩዋት:: "እባክህ ተወኝ" ብላ እምባዋን እንደገና ዘረገፈችው......

Wednesday, March 5, 2014

ወደ ብላቴ ስንሄድ - ክፍል አንድ

መጋቢት ፩፬ ፩፱፰፫ አ.ም.

ያ ዶሮዬ ጮከ መንጋቱን ነገረኝ 
በዛሬው ቀን ላርደው ቀጠሮ ነበረኝ 
(ታገል ሰይፉ)

የጅማ አየር ከወትሮው በባሰ ሁኔታ ሞቅና ከበድ አለ:: በሰማዩ ላይ የተንጣለሉት ደመኖች ሊወድቁ የደረሱ መሰለ:: በዚህ እኔና ጉዋደኞቼ ነገሮችን ጠለቅ ብለን በማናስብበት: ፖለቲካም በማይገባን ጨቅላ እድሜ ሳይታሰብ የከፋ ግዜ ብቅ አለ:: ሊቀመንበር መንግስቱ "ዘራፍ!"ብለዋል ተባለ:: ሰኞ: ማለትም ከሁለት ቀናት በሁዋላ የጤና ሳይንሱ ተማሪዎች በሙሉ ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ጉዞ በመጀመር መላውን የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ና ኮሌጅ ተማሪ ዘማቾች እንዲቀላቀሉ የተወሰነ መሆኑ ሲነገር ተማሪ ሁሉ የድንጋጤ ድባብ ተላበሰ:: ከጥቂት ቀናት በፊት በቴሌቪዥን ያየነው የጋለ ና በፍላጎት የተደረገ የሚመስለው የአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሊቀመንበር መንግስቱ ፊት ያሰሙት ጩሀት ቅርፁን ቀይሮና ፈጣን ትእዛዝ ሆኖ ወደ ጅጤሳ መጣ:: ትእዛዙን ተከትሎ የአብዛኛው ተማሪ ባህሪ ለውጥ አሳየ:: ሳቅ የሚባል ነገር ጠፋ:: ጭምት: ዝምተኛና ከስታራ በዛ:: መራወጥና መተራመስ ተጀመረ.....

ዛሬ ከሰዓት የአራተኛ ዓመት ሕክምና ተማሪ ከሆነው የሰፈሬ ልጅ ታጠቅ ጋ በመሆን አልፎ አልፎ እየሄድን ወደየቤታችን ስልክ ከምንመታበት የጅማ ቴሌ (ስልክ ቤት) ሂጄ ነበር:: እንደጠበኩት ስልክ ቤቱ  በተማሪዎች ተጨናንቆ ነበር :: "ጉዞ ጀምሩ ተብሉዋል" "ጉዞ መጀመራችን ነው" የሚሉ መልክቶች ከጠባቦቹ ና አንድ ውይም ሁለት ሰው ብቻ ከሚይዙት የስልክ መደወያ ክፍሎች ውስጥ በተደጋጋሚ ሰማሁ:: አንዳንዱ ተማሪ ከድንጋጤና ከመረበሽ የተነሳ ነገሮችና አካባቢውን ማስተዋል ተስኖታል:: አንድ ተማሪ ተራውን ጠብቆ አንድ ግዜ በተመታለት ስልክ አናግሮ ከጨረሰ በሁዋላ ከመነጋገርያው ጠባብ ከፍል ውስጥ አንገቱን አስግጎ ኦፕሬተሯን "እባክሽ እንደገና ደግሞ እገሌ ጋ ደውይልኝ" አለ:: ሐምሳ የሚሆኑ ሰልፍ ይዘው ተራቸውን የሚጠብቁ ሌሎች ተማሪዎች ባንድነት ስለጮሁበት የውር ድንብሩን እየሮጠ ከቴሌው ወጣ:: እኔ በሩ ላይ ስለነበርኩ ባይኔ ተከተልኩት: ከወጣም በሁዋላ ሩጫውን አላቆመም...እኔ ቤተሰቤን በስልክ እንደማላገኛቸው እርግጠኛ ነበርኩ:: ምክንያቱም በፊት እንኖርበት የነበረውን  ቤት ለቀው ነገ አዲስ ቤት ውስጥ ይገባሉ:: ስለዚህም መስመሩ ስለሚቁዋረጥ...ስልኩ አይሰራም የሚል ግምት ነበረኝ:: ቢሆንም ደወልኩ...እንደገመትኩት ነው ስልኩ አይመልስም:: ታጠቅ ደወለ:: እህቱ ነበረች ስልኩን ያነሳችው:: ሁኔታውን ሲገልፅላት ክፉኛ እንደደነገጠች ገምቻለሁ:: ታጠቅ ከእህቱ ጋ ያረገውን ንግግር ጨርሶ ስልኩን ሲዘጋ ፊቱ ላይ ሃዘን ይታይ ነበር:: እህቱ ስታለቅስ እንደነበር ና የሚላትን ልትሰማ እንዳልቻለች እየቀፈፈው ነገረኝ:: 

የአንደኛና የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች በሙሉ ዛሬ የተውሶ መፅፍቶቻቸውን ለትምህርት ቤቱ አስረከቡ:: ነገ ደሞ አልጋና ቁምሳጥን ይመልሳሉ ተብሉዋል:: ብዙ ተማሪዎች ያላቸውን የግል ዕቃ በሙሉ ልክ ለእረፍት ወደ ቤት እንደሚሄድ ሰው በሻንጣ ሲሸክፉ ዋሉ:: ግዙፍ የ ሽብር ና መረበሽ ድባብ ሰፍኑዋል::   

የሬዲዮና የቴሌቪዥን ዜናዎች ሁሉ ስለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዘመቻ ጥያቄና ምዝገባ ወሬውን በሰፊው እያናፈሱት ነው:: እዚህ ግን ከተማሪዎች ዘንድ የሚነገር የጥርጣሬ አስተያየት እሰማለሁ:: "እስካሁን ድረስ አንድም የተንቀሳቀሰ ኮሌጅ የለም:: አንዳንድ ተማሪዎች ከየኮሌጁና ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ እየጠፉ ነው:: የጥቁር አንበሳ ሕክምና ተማሪዎች የዘመቻውን ጥሪ አልተቀበሉትም:: ና ወዘተ... ቅዳሜ ተመዝግበን ሰኞ ለጉዞ መታዘዛችን በሁለት ቀናት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር በቂ የሆነ የስልክ ግኑኝነት ለማድረግ የማያስችል በመሆኑ: ተማሪዎች እርስበርሳቸው ከሚነጋገሩት ወሬ ለመገመት እንደቻልኩት ሰኞ የመሄዱን ጉዳይ ማንም የተቀበለው አይመስለኝም: ለማንኛውም ነገ ጠዋት ስብሰባ ያለ ይመስለኛል....