Friday, January 30, 2015

ሚያዚያ 10 ቀን 1984 አ.ም.
ጅማ


PC-1 እየተባለ የሚጠራውን የሁለተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርቴን ለመከታተል ጅጤሳ ከተመለስኩ ሁለት ሳምንት ሆነኝ:: የቅርቤ ከሆኑት ጉዋደኞቼ ጋር በዋይትሃውስ ዶርም ቁጥር 207 ውስጥ ከትሜያለሁ:: በርካታ የባቼ ልጆች ከእረፍት መልስ የወፈሩና ያማረባቸው ሲሆን እኔና ጥቂት ሌሎች ልጆች አላማረብንም ባይባልም የሰውነታችን ሁኔታ ለውጥ ሳያሳይ ነው የተመለስነው::

የፒሲዋን ትምህርቶች ለህክምና መሰረታዊ የሆኑትን ሳይንሶች Anatomy: Physiology: Biochemistry: Histology ና Embryology ያካተቱ ናቸው:: የአጠቃላይ ዲፓርትመንቱ ኃላፊነት የተሰጠው ሰው አቶ ኢሳያስ ይባላል:: አቶ ኢሳያስ ከቢሮ ኃላፊነቱ በተጨማሪ የBiochemistry እውቀት የታጠቀ እንደሆነና እንደሚያስተምረን በመጀመሪያው ቀን orientation ስብሰባችን ላይ ነግሮናል:: የፒሲዋን ትምህርቶችን መጪውን ዓመት ሙሉ ተቀምጠን የምናዳምጥበትና የምንቀስምበት ክፍል ውስጥ ወስዶ በመንፅሩ የበታች ዳርቻ አሻግሮ እየተመለከተን ረዥም ዲስኩር አደረገ:: ወፈር ያለ ሰውነቱና ጠቆር ያለ ገፅታው በመጀመሪያ ሳየው የሌላ አፍሪካ አገር ዜጋ እንዲመሰለኝ አርድርጎኝ ነበር::

አቶ ኢሳያስ በኦርየንቴሽኑ ወቅት ከተናገራቸው በርካታ ማስፈራሪያ መሰል አረፍተ ነገሮች መካከል አንድ በጣም የወደድኩለት አባባል አለ:: “በምንም ተአምር ከምሽቱ ስድስት በሁዋላ እንዳታነቡ: ዋጋ የለውም!” እኔ ታዲያ በሆዴ አርጎት ነው!? አልኩ ይህን ስሰማ:: ሌላው ደስ ያለኝ ነገር የፒሲዋን ትምህርቶችን የሚያስተምሩን እንደፊቱ ኩባውያን ሳይሆኑ ግብፃውያን እንደሚሆኑ መስማቴ ነው:: ከኛ የቀደሙት በኩባውያን የተስተማሩ ባቾች እንደነገሩን ከሆነ ከኩባውያን እንግሊዝኛ አለመቻል ጋ የተያያዘ ብዙ የመማር ማስተማር ሂደት ችግር ነበር:: ስለዚህም ተማሪዎቹ ለእውቀታቸው መዳበር ላይብረሪ ሂዶ መፅሐፍ ማንበብን እንደዋነኛ ምንጭ አድርገው መትጋትና መፍጋት ነበረባቸው:: እኔ ታዲያ በከዚህ በፊት ታሪኬ እንደገለፅኩት ቤተ መፅሐፍት ተቀምጦ ማንበብ ላይ ያለኝ ስር የሰደደ አሉታዊ አመለካከት በኩባውያን መምህራን ስር ብሆን ችግር መፍጠር ብቻ ሳይሆን ስጋት ውስጥ ይጥለኝ እንደነበር ግልፅ ነው:: ስለዚህም ግብፆቹ በእንግሊዝኛ ቁዋንቁዋ እንደሚያስተምሩን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ባልሆንም የኩባዎቹ ካካባቢው መጥፋት ግን የአእምሮ ረፍት ሰጥቶኛል:: መቼም ግብፃውያኑ በአረብኛ እናስተምራችሁ እንደማይሉ ተስፋ አደርጋለሁ:: 

የሚገርመው ግን ፒሲዋን ከተጀመረ ሁለት ሳምንት ቢሆንም ግብፆቹ ገና አልመጡም:: ወሬያቸውም የለ:: አንዳንድ ወጣት ሀበሻ መምህራን ግብፆቹ እስከሚመጡ በሚል ለማስጀመር ያህል ሌክቸር እየሰጡን ቢሆንም ጥናት የሚባለውን ነገር የምር ለመጀመር ግን ያሚያነሳሳ ሞራል ገና አላበጀሁም: እኔ በበኩሌ:: የሌላውን አላውቅም::

Friday, January 16, 2015

የካቲት 23 1984 አ.ም.

በመጀመሪያ ባለፈው.....
ባለፈው ደብረዘይት አክስቴን ጥየቃ ሄጄ ነበርና በዚያ ሳለሁ ከምሽቱ ፩፪ ሰዓት ሲል ወደ መንገድ ዳር ወጣ ብዬ ነበር:: በዚያም ሰዓት ሰማዩ ደማቅ ሰማያዊ መሆኑን ተመለከትኩና የጅማ ከተማ ሰማይ ትዝ አለኝ:: በተለይ በፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት! ከጤና ሳይንሱ ደጃፍ ወደ ምዕራብ ከከተማው ባሻገር ካለው አድማስ ላይ የጅማ ፀሐይ ግዙፍ ሆና ትታያለች:: አጠላለቁዋ ፈጣን ነው:: በሚገርም ሁኔታ ለአይን ሳታጥበረብር ወርቅ ቢጫ ቀለም እንደተላበሰች ሰማዩን ታክካ ዥ............ው ብላ ትጠልቃለች:: ከአባ ጅፋር ቤተመንግስት ዝቅ ብሎ በሰፈረው ጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲቱት ውስጥ ስኖር ላይኔ ምግብ ከሆኑኝ የተለያዩ ነገሮች ዋነኛ: ስርቅም ከሚናፍቁኝ ነገሮች አንዱ በበጋው ወራት በየቀኑ ከእራት ሰዓት በሁዋላ የፀሐይን ጥልቀት መመልከት ነው::

የካቲት ዘጠኝ የቴሌቪዥን ዜና ስለ ንጉሰ ነገስት ሃይለስላሴ አፅም ትናገረ:: አፅሙ ለብዙ አመታት ተቀብሮ ከነበረበት ቦታ በቁፋሮ መውጣቱን እንዲሁም በመጪው ሐምሌ 16 ቀን 1984 አ.ም. ከንጉሡ መቶኛ ዓመት ልደት ጋር የቀብር ስነስራታቸው እንደሚፈፀም አዳመጥኩ:: እንደዜናው አባባል አፅሙ የመንግስቱ ሃይለማርያም ቢሮ ስር ሶስት ሜትር ዝቅ ብሎ ተቀብሮ ነበር::

ዋናው ታሪክ.....የፍረሽማን እውቀት
የካቲት 19 ቀን ከአንድ ስራው የደህነንት ፖሊስ ከሆነ ደረጄ የሚባል አብሮ አደግ ጉዋደኛዬ ጋ ሰበታ የሚገኘው ሜታ አቦ ብራ ፋብሪካ ሄጄ ነበር:: ወደሰበታ ለመሄድ በግብዣ መልክ ጥያቄ ያቀረበው ደረጄ ነበር:: “በቃ ዛሬ ቀኑን ሙሉ እንከባከብሃለሁ” ብሎ:: ሜታ አቦ ብዙም አልቆየንም:: ሁለታችን ብቻ ስለነበርን እንደታሰበው ቆይታው አጉዋጊ ሊሆን አልቻለም:: ስለዚህም ምሳችንን በልተንና ቢራ ጠጥተን ወጣን:: ከዚያ በሁዋላ እዚያው ሰበታ የሚገኝ ስጋ ቤት ሂደን ጥሬ ስጋ አስቆርጠን ከሰከስን:: የፈረንጅ አረቄና ወይን ጠጅ በመለኪያ አከልንበት........የሚገርም ውሎ ነበር :: መጨረሻ ላይ ከሰበታ ገበያ ብዙ  ማቲም ገዝተን ወደ ወላጆቹ ቤት ሄድን:: እዚያም ከገዛነው ቲማቲም አስከትፈን በንጀራ ቀምሰን ተኛን :: በዚሁ ቀን ሌሊት ከዚህ በፊት አጋጥሞኝ ያማያውቅ ውጋት ግራ ሆዴ ላይ ቀስፎኝ ከእንቅልፌ ነቃሁ:: መቼም ኃይለኛ....ኃይለኛ ውጋት ነበር:: ልክ ሆዴ ውስጥ የሆነ ነገር አንጀቴን ነክሶ ወደ ውስጥ እየሳበው የነበረ ነው የመሰለኝ:: መቆምም ሆነ መቀመጥ አቃተኝ:: ግራ ክንዴና እጄ ዛለ:: ደረጄን ከእንቅልፉ ቀሰቀስኩት:: ህመሙ ብሶብኝ ድምፅ አውጥቼ አለቀስኩ:: የበላሁት እንዲወጣ ጣቴን ላንቃዬ ውስጥ ሰነቀርኩ:: ከዚያም አስታወከኝ:: ነገር ግን ጥቅም አልነበረውም:: ውጋቱ ቀጠለ:: በግራ ሆዴ በኩል ከእምብርቴ ዝቅ ብሎ ነክሶ ይስበኝ ቀጠለ:: ደረጄ ባጋጣሚ ተቀምጦ የነበረ: ዳግም አረቄ ከጉዋዳ አምጥቶ ሰጠኝ:: አንድ መለኪያ ጠጣሁና በተከታታይ አስታወከኝ:: ጨጉዋራዬ ና አንጀቴ ውስጥ ያለው በፍጭት ሂደት ላይ ያለ ምግብ በሙሉ በትውከቱ ውስጥ መካተቱን እርግጠኛ ነበርኩ:: በዚህ ሁኔታ ነጋ:: ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ደረጄ አንድ የሰፈር ሀኪም ዘንድ ይዞኝ ሄደ:: ሰውዬው ሀኪም ቤት እንደሚሰራ እንጂ ትክክለኛ ሙያውም ሆነ የትምህርት ደረጃው አይታውቅም: ግን የሰፈር ሰዎች ሲታመሙ በአነስተኛ ክፍያ ያማክራል: መድኃኒትም ይሰጣል:: መድሃኒቱን ከየት እንደሚያመጣው አይታወቅም:: የሚጠይቅም የለም:: ብዙም ጥያቄ ሳይጠይቀኝ ሁኔታዬን በማየት ብቻ በፍጥነት አንድ መርፌ ወጋኝ:: ከዚያም አራት ነጫጭና ሶስት ቀያይ ክኒኖች ሰጠኝ:: ሲያስፈልገኝ እንድውጥ:: የክኒኖቹን ስምም ሆነ ለምን ሰባት እንደሆኑ አልጠየኩትም:: እንደምድን ተስፋ በማድረግ ብቻ ከሀኪሙ ቤት ወጣን:: ህመሙ ባይለቀኝም ረፋዱ ላይ ቀነሰ:: በዚያ ወቅት እቤቴ በእናቴ እንክብካቤ ስር ነበርኩ:: እናቴ አመሻሹ ላይ የተሻለ ብላ ያሰበችው ሌላ የሰፈር ሀኪም ጋ ወሰደችኝ:: ሰውነቴ ክፉኛ ዝሎ ስለነበር ወደ ሐኪሙ ቤት ስንጉዋዝ ሁለት ሶስት ግዜ መንገድ ላይ ማረፍ ነበረብኝ:: ይሄኛው ሀኪም ታሪኬን ከሰማ በሁዋላ በየቀኑ እየተመላለስኩ መርፌ እንድወጋ አዘዘ:: አንድም እዚያው ወጋኝ:: በሽታዬ ምን እንደሆነ እንዲነገረኝ በድካም ውስጥ እንዳለሁ ጠየኩት:: ቅሬታ ገፁ ላይ ተነበበ:: “አርፈህ ጭንህን ወዲህ በል” አለኝ:: ሶስት ቀን ተመላልሼ ከተወጋሁ በሁዋላ እየተሻለኝ ሄደ:: ብርታት ተሰማኝና መርፌውን በራሴ ውሳኔ አቆምኩት:: እናቴም ተስማማች:: የእናቴ ጉዋደኞችና በርካታ ጎረቤቶች መጥተው ጠየቁኝ:: አብዛኞቹ ጠያቂዎቼ ሕመሜ ብርድ መሆኑን ፈፅሞ አልተጠራጠሩም::  መጋኛ ነው ያሉም አሉ:: የኔ ጥርጣሬ ያረፈው ግን የዛን እለት ምሽት የተመገብነው ቲማቲም ላይ ነው:: እስቲ ጠግበን ውለን ሳለ ምን የማታ ማታ ቲማቲም አስበላን? ምናልባት በንፅህና አልተሠራ ይሆናል:: በኔ ግምት አሜባ ሊሆን ይችላል: አንጀቴን በትክክል አቁስሎታል:: አሜባ እንዲህ ነው እንዴ? ውጋት ብቻ? ያለተቅማጥ? ጥሬ ስጋውስ? የተረፍኩት በእግዜር መሆን አለበት.........

Saturday, January 10, 2015

ጥር 23 ቀን 1984  .

አዲስ አበባ ቀራንዮ

የጥምቀት በዓል ባለፈው ሰሞን ተከበረ:: ይህ በዓል ሲከበር እዚህ ያደኩበት ሰፈር በመሆኔ በእውነት ደስ ብሎኛል:: የጥምቀት በዓል ልጅነቴን ጉልህ አድርገው ከሚያስታውሱኝ ትዝታዎች አንዱ ነው:: በልጅነቴ በየዓመቱ ጥምቀት ሲመጣ ጥምቀተ ባህር እየተባለ  ወደሚጠራ ስፍራ ከሰፈር ጉዋደኞቼ እንሄዳለን:: እዚያም ከዋዜማው እለት ጀምሮ ስንሮጥ: ስንላፋ እንዲሁም ለጥምቀት ብለን ባጠራቀምነው ሳንቲም ብርቱካን: በረዶ: ሸኮራ አገዳ: ብስኩት ወዘተ...እየገዛን ስንበላ ውለን እናመሻለን:: ጧፍ እናበራለን:: እንደሌላው ጊዜ ሳይሆን ለጥምቀት እለት እስከ እኩለሌሊት እንድናመሽ በወላጆቻችን ይፈቀድልናል:: መቼም የልጅነት ጉልበት ያማይልቅበት ነውና ጥምቀተ ባህር ውስጥ በአዋቂዎች እግር ስር ስንሹሎኮሎክና ካንዱ ጫፍ ወደ አንዱ ጫፍ ስንሮጥ አይደክመንም ነበር:: አንዳንድ ጉዋደኞቼ በእርግጥ የሚሮጡት ከሌላ ደከም ካለ/ ልጅ ላይ ብርቱካን ወይም ማስቲካ ወይም ሌላ የሚበላ ነገር መንትፈው ነበር::የቀራንዮ መድኃኔዓለም ታቦት ወደ ጥምቀተ ባህሩ ለጥምቀት ዋዜማ ለት ሲገባና በማግስቱም ከጥምቀተ ባህሩ ወደ ቤተክርስትያኑ ሲመለስ በሚጉዋዝበት ባቡር መንገድ ላይ የነበረው ትእይንት ፈፅሞ አይረሳኝም:: ባንድ ወገን የቤተክርስትያን ዘማሪዎች በቀለማት የደመቀ አንድ አይነት ልብስ ለብሰው  እስከቻሉት ድረስ በመጮህ ከበሮ በመደለቅ ሲዘምሩ ና አንዳንዶቹም ሲዘሉ: እልፍ ብሎ ደግሞ የብሄረሰብ ባህላዊ ጭፈራዎች የሚታዩበት ስብስብ (በተለይ ዶርዜኛ ና ኦሮምኛ): ከዚያ ደግሞ ዘመናዊ ሙዚቃ ሃርሞኒካ የሚዘፈንበትና ወጣቶች የጊዜውን ዳንስ የሚደንሱበት ግሩፕ የሚፈጥሩት የመንገድ ላይ ግርግር እስከዛሬ ባይነ ህሊናዬ አለ:: ዘንድሮ ይሄው አድጌ ወጣት የኮሌጅ ተማሪ ደንብ ደርበብ ብዬ ጥምቀትን ከዳር ቆሜ እንደ ትርኢት አየሁት:: የሀይ ስኩል ጉዋደኛዬና ጎንደር  ሕክምና ትምህርት ቤት የተመደበው ከፈለኝ አብሮኝ ነበረ::  ያኔ እኔ ራሴ ተዋናይ የነበርኩበትን የጥምቀት በዓል ተውኔት እንደ ታዳሚ ተመለከትኩት:: የጥምቀት በዓል ደስ ይላል....

ወደዛሬ ልመለስ:: ዕረፍቴ ረዥም ስለሆነ አንዳንዴ መታከት ብቻ ሳይሆን የምሰራው ግራ ግብት ይለኛል:: ልቦለዶች በተከታታይ እያነበብኩ ነው:: አንድ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር የትርጉም መፅሀፍት በብዛት እየተፃፉ ነው:: ልክ አሁን “Madam X ወይምስም የለሽየተሰኘ ትርጉም ልቦለድ አንብቤ ጨረስኩ::

ትናንትና አርብ ለት ፒያሳ ከሚገኘው British Council ቤተ መፅሃፍት ሂጄ ነበር:: እንደ ጊዜ ማሳለፌያ ነበር የሄድኩት:: አሀ! አዎ ስለ Bronchitis ለማንበብም ፈልጌ ነበር:: አንዲት በቅርብ የማውቃት የናቴ ጉዋደኛ የሆነች ሴት በቅርቡ ሀኪም ቤት ሄዳ ሀኪም “Bronchitis” አለብሽ አላት:: በጣም ያስላታል:: አክታም በብዛት ትተፋለች:: ከዚህ በመነሳት ለምን ስለዚህች ሴት በሽታ አላነብም የሚል ሃሳብ መጣልኝ:: ስለዚህም British Council ተገኘሁ::

 ቤተ መፅሃፍቱ ውስጥ Medicine የሚል ሼልፍ አለ:: እዚያ ሄድኩና የተደረደሩትን መፅሃፍት ሁሉ ቃኘሁዋቸው::  “Pharmacology: Pediatrics: Surgery: Nursing ወዘተ... ለተወሰኑ ደቂቃዎች ካማተርኩ በሁዋላ “Disorders of the Chest” የሚል መፅሐፍ አይቼ አነሳሁት:: አነበብኩ ስለ “Acute Bronchitis” “Chronic Bronchitis” .... “disease of the alveoli” ላል::በተወሰነ መልኩ ማንበቤ ደስ ቢለኝም አሁን ይሕን ማንበቤ ምንም ትርጉም እንደሌለው ሆኖ ተሰማኝ:: ገና ፍሬሽ ማን መጨረሴ ነው:: እንደዚህ አይነቶቹም መፅሃፍት አንብቦ ተረድቶ ለመጠቀም ቢያንስ አራተኛ ዓመት ተማሪ መሆን ያለብኝ ይመስለኛል:: አራተኛ ዓመት ከመደረሱ በፊት ደግሞ ከፊቴ የተደቀኑ ሁለት እንደተራራ የገዘፉ አመቶች አሉ:: በጅጤሳ Preclinical Years ይባላሉ:: የነዚያ ሰው ይበልኝ.....

Friday, January 2, 2015

ጥር ስምንት ቀን  አስራ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት አ.ም.  
አዲስ አበባ
ባይ ባይ ፍሬሽ ማን

በዚህ ቀን ምሽት ላይ አዲስ አበባ ቀራንዮ የሚገኘው ቤታችን ውስጥ ሆኘ ቴሌቪዥን እያየሁ ይህን ፅሁፍ አሰፈርኩ:: እነሆ የአንደኛ ዓመት የህክምና ትምህርቴን አጠናቅቄ ለእረፍት እዚህ ተገኝቻለሁ:: ሶስተኛ ቀኔ መሆኑ ነው::

ባለፈው ጥር ሁለት ቀን አስፋው የተባለውን የባቻችን አባል መሸኛ አደረግንለት:: እንደመሰለኝ አስፋው ፈተናዎቹን ተንጠልጥሎም ቢሆን ያለፈ ሲሆን የወደፊት ሂወቱን ግን በህክምና ትምህርት ውስጥ ሆኖ ላለመቀጠል ወስኑዋል:: ስለዚህም ጅጤሳንና እኛን ተሰናበተን:: የኛ ባች በለፈው ዓመት መስከረም ላይ በ47 አባላት ተጀምሮ አሁን 38 ደረሰ:: በነገራችን ላይ እኔም ወደ ሁለተኛ ዓመት አለፍኩ ማለት ነው::

ጥር አምስት ቀን ጅማን ለቅቄና በክፍለሀገር አውቶቡስ ላይ ተፈናጥጬ ለእረፍት የትውልድ ከተማዬ ከሆነችው አዲስ አበባ ገባሁ:: ጉዞዬ እንደተለመደው ወደ አስር ሰዓት ፈጅቶ ነበር: ለምሳና ለቁርስ የታረፈውን ጨምሮ:: አውቶቡሱ አዲስ አበባ ቃሊቲ ን አልፎ ከካራቆሬ ጀምሮ ያሉትን የኮልፌ ሰፈሮች እየሰነጠቀ ሲያልፍ አካባቢያዊ የሆነ ልዩ ስሜት ተሰማኝ: ደስ ደስ የሚል:: አውቶቡሱ በሹፌሩና በረዳቱ መራጭነት የወቅቱን ኤፍሬም ታምሩ ዘፈን እያንቆረቆረ አሮጌው አውሮፕላን ማርፊያ ሲደርስ እንዲቆምልኝ አስደርጌ ወረድኩ:: ከዚያም ሻንጣዬን እንደተሸከምኩ የመኪና መንገዱን ተሻግሬ በቀኝ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስትያንን በግራ የ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን መኖሪያ ቤት አልፌ ውስጥ ውስጡን ወደ ቀራንዮ መኖሪያ ቤታችን አመራሁ.....

ቤተስቤን በሰላም በማግኘቴ ደስ ያለኝ ቢሆንም በደረስኩ በማግስቱ ሰፈራችንና አካባቢው ውስጥ ከአብሮ አደግ ጉዋደኞቼ ጋር በመሆን ስዘዋወር ባየሁት የሰዉ የኑሮ ሁኔታ ግን ልቤ ሳይደናገጥ አልቀረም:: በአንድ ወቅት ከቤት የማይወጡ የነበሩና ንፅሕናቸው ተጠብቆ ትምህርት ቤት ሲሄዱ አያቸው የነበሩ አንዳንድ "የደህና ቤተሰብ" ሕፃናት ተጎሳቁለውና ቆሽሸው ከቤታቸው በራፍ ላይ በዝተው ተመለከትኩ:: ለወትሮው እሁድና ቅዳሜ ብቻ ሰፈር ውስጥ ይታዩ የነበሩ ለስራ ጠዋት ወጥተው ማታ ይመለሱ የነበሩ በርካታ አባቶች ያለስራ ተቀምጠው ና ሰውነታቸውም ከስቶ ሳይ የአባቴ ማስተማር መጀመር በውስጤ እፎይታ እንዲሰማኝ አደረገኝ:: ትንሽ የኛ ቤተሰብ ይሻላል አልኩ በልቤ:: በርካታ ቤተሰቦች የአጥር ግቢያቸው በራፍ ላይ ሸቀጣ ሸቀጦችን ደርድረው ችርቻሮ ንግድ ጀምረዋል:: በአጠቃላይ የሰፈራችን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ወትሮ ከማውቀው ዝቅ ያለ ሆኖ ተሰማኝ:: ከአብሮአደግ ጉዋደኞቼ ጋ ሳወጋ እንደተገንዘብኩት የመንደር ውስጥ ውንብድናና ዘረፋ ብሎም የመንገድ ላይ ድብድብ ተስፋፍቱዋል:: ብዙ ሰዎች በመንግስት ደስተኞች አለመሆን ብቻ ሳይሆን ጥላቻም ያንፀባርቃሉ::

ዕረፍቴ ሁለት ወር ከአስራምስት ቀን የሚፈጅ ስለሆነ እንዴት እንደማሳልፈው ማሰብ አለብኝ:: ለጊዜው ይሄ ነው የምለው እቅድ የለኝም:: ወላጆቼም ቢሆኑ የገንዘብም ሆነ እኔን ወንድሜንና በቤት ያሉትን አራት እህቶቼን የማስተዳደር አቅማቸው ደካማ ስለሆነ ያቀዱልኝ ምንም አይነት ነገር የለም:: ጤና ሳይንሱ ውስጥ እያለሁ በእርግጥ ለእረፍት አልቸኮልኩም ነበር:: ይልቅስ የቸኮልኩት የአንደኛ ዓመት ትምህርት እንዲጠናቀቅ ነበር:: በዚያ ደስ ይለኛል:: እረፍቱ ግን.........ረዥም ነው:: በተቻለኝ መጠን ብዙ መፅፍትን ለማንበብ አስባለሁ:: በተለይ ለሁለተኛ ዓመት የህክምና ትምህርቴ አስፈላጊ የሆነውን በትዕግስት የማንበብ ልምዴን ለማጎልበት ከአሁን ጀምሮ ልቦለድም ሆነ ሌሎች አይነት መፅሃፍቶችን ለብዙ ሰዓታት ያለማቁዋረጥ ማንበብ መጀመር አለብኝ:: በቤታችን የሚገኙትን የአባቴን  the book of knowledge የተሰኙትን Encyclopedia መፅሃፍት የቻልኩትን ያህል ለማንበብ አስቢያለሁ.....