Sunday, September 23, 2018

ታህሳስ 22 1988 አ.ም. (ጃኑዋሪ 1፣ 1996 እ.ኤ.አ.)

ሀበሻ ላልሆኑ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ለሚኖሩ ስዎች ዛሬ የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ነው:: 1995ን ጨርሰው ወደ 1996 ገቡ:: መልካም አዲስ ዓመት ብያለሁ:: እኔ ግን ይህን ቀን የማስታውሰው የአእምሮ ሕክምና (psychiatry ) ትምህርት የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን በመሆኑ ብቻ ነው:: ያ የለፈው የታህሳስ መጀመሪያ የፈተና ሰሞን አለፈ:: እኔም ፈተናዬን ተፈተንኩ:: ነገር ግን ለትውስታ የሚሆን አንድም ነጥብ ሳላሰፍር እንደተፈተንኩ ላጭር ረፍት ወደ አዲስ አበባ ሂጄ ነበር:: ባለፈው ሰኞ ወደ ጅማ ተመለስኩ:: የአእምሮ ሕክምና ትምህርትም በበነጋው ተጀመረ:: በቅጡ ማንበብ ባልጀምርም ትምህርቱን ወድጀዋለሁ:: ከሕክምና ትምህርቶች ሁሉ አንደኛ የምወደው እሱ ነው ብዬ ደፍሬ መናገር ባልችልም በትምህርቱ ክፍለግዜ ስለሰዎች ባህሪ ፣ አንዲሁም ስለ psychoanalysis የምናደጋቸውን ውይይቶች በጣም ተመስጬባቸዋለሁ:: ምናልባት ቤተሰብ ጋ እረፍት አድርጌ ገና መምጣቴ ስለሆነና ያዕምሮዬም ጤና ጥሩ ስለሆነ ጥሩ ተሰምቶኝ ይሆናል እንዲህ ያልኩት:: 


የካቲት  17 1988 አ.ም. እሁድ 

የአራተኛ አመት የህክምና ተማሪ የሆነው ክንፈ ዛሬ ሞተ:: ራሱን በስቅላት አጠፋ:: በማደሪያ ክፍሉ ባለ ሎከር ውስጥ በኤሌትሪክ ገመድ ተሰቅሎ ተገኘ:: ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም:: እጅግ ጥልቅ የሆነ ሃዘን እየተሰማኝ ነው:: የመሞቱን ወሬ ከሰማሁ በሁዋላ ጉዋደኞቼን አግኝቼ አስከማረጋግጥ አላመንኩም ነበር:: እንደኔና እንደአብዛኞቹ ተማሪዎች ከድሀ ቤተሰብ የተወለደና የወደፊት ሂወቱን ብሩህ ለማድረግ የሚፍጨረጨር ምስኪን  ዜጋ ነበር:: ራሱን አጠፋ? ለምን? ኦ አንተ አግዚአብሔር ወጀቡን አረጋጋው: ቀሪዎቻችንን እንዲህ አናደርግ ዘንድ ጠብቀን! አሜን!

የለም! ገና አልጨረስኩም:: በዚህ ጉዳይ የምለው ተጨማሪ ነገር አለ:: ስለክንፈ ሳይሆን ስለራሴ:: እንዲዚህ አይነትና መሰል ሁኔታዎች ከዚህ በፊት ሲከሰቱ ስለክስተቱ ብቻ ሳይሆን ስለራሴም በጥልቅ  አስባለሁ:: አሁን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ነው:: እኔም ሆንኩ የክንፈን ሞት የሰሙ የጤና ሳይንሱ ተማሪዎች በሙሉ ያልተረጋጋ ስሜት ውስጥ ነን:: አንዳንዶቹ የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ 
ተኝተዋል:: እንደክንፈ አይነት አሟሟት እንደማልሞት አርግጠኛ መሆን አሰኘኝ ::  ሁልግዜ ችግር እንዳለብኝ እያሰብኩ በኑሮም እነጫነጫለሁ:: አሁን ግን ሳስበው ያ ሁሉ እውነት አይደለም:: ሌሎች  መፍትሄ የሌለው ከባድ ችግር ያለባቸው ሰዎች አሉ ማለት ነው:: 

ዛሬ እጀግ ብራ የሆነና ነፋሻ ያማረ መልካም እሁድ ቀን ሆኖ ነው የዋለው:: ክንፈም በመፅሃፍት ቤቱ ውስጥ በትጋት ሲያጠና ነበር- እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ:: ከዚያ ቀጥሎ ወደ ማደሪያ ክፍሉ በመሄድ ራሱን አጠፋ! ብዙ ግዜ ለብቻው የሚራመድ : ብዙ የማይናገርና ብዙም ለትምህርቱ ደንታ የሌለው የሚመስል ልጅ ነበር:: ተማሪ ራሱን ሲያጠፋ በ ጤና ሳይንሱ ታሪክ ክንፈ የመጀመ ሪያው ነው::

ፍርሃት ፍርሃት አለኝ:: ምንን  እንደምፈራ ግን አላውቅም::  መንግስቱ ክንፈን ይቀርበው ነበር:: አሁን መንግስቱ የት ነው ያለው? ሬሳውን አጅቦ ወደ ክንፈ አገር እንድብር ሄዷል መሰለኝ::

እዚግህ ላይ ይብቃኝ መሰለኝ መፃፉ:: 10 ሚሊግራም  ዲያዜፓም ያስፈልገኛል:: አለዚያ እንቅልፍ ላይወስደኝ  ይችላል:: ወይስ አልውሰድ? ትንሽ ልጠብቅ እስቲ ........

ማስታወሻ: በዚህ ቀን ፅሁፌን ከጨረስኩ  በሁዋላ በድንገት ሳላውቀው እንቅልፍ ወሰደኝ:: ያዘጋጀሁትን ዲያዜፓም ታብሌት አልወሰድኩትም 



Wednesday, September 12, 2018

የፈተና ሰሞን 

ማክሰኞ ታህሳስ ሁለት  ቀን 1988 ዓም 

ዛሬ ምሽት ላይ ዝናብ ጣለ:: በጋራ መኝታ ቤታችን ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ ከኔና ከመንጌ በስተቀር ነገ የየተመደቡበትን ክፍል ፈተና ያጠናቅቃሉ:: መንጌ የውስጥ ደዌ ትምህርት ፈተና ሐሙስ የሚያጠናቅቅ ሲሆን እንደ ዕድል ሆኖ እኔ ግን ለመፈተን የመጨረሻው የዶርሙ አባል በመሆን አርብ የውስጥ ደዌ ትምህርቴን እፈተናለሁ:: በህክምና ትምህርት ውስጥ እንዲህ ያሉ የምጥና የመከራ ቀናት ለኔ አዲስ አይደሉም ነገር ግን የዶርም ተጋሪዎቼ በሙሉ ፈተናቸውን ጨርሰው እያየሁ እንዴት አዘልቀዋለሁ! ከባድ ነው የሚሆንብኝ:: ከኔና ከመንጌ በቀር ሌሎቹ ነገ የሚፈተኑት በሙሉ የማንበብ ፍጥነታቸውን ቀንሰው ለማይቀረው ፈተና ሃሳባቸውንና አእምሮአቸውን በማረጋጋጋት ላይ ናቸው:: የመጨረሻው ተፈታኝ በመሆኔ ከፋኝ:: ብቸኝነት ተሰማኝ:: ዛሬ ከሰዓት በሁዋላም የጎሰጎስኩት የጫት ምርት አላመረቀነኝም:: ፀጥ ግን አድርጎኛል:: የመኝታ ክፍል ተጋሪ የሆኑትና የቅርብ ጉዋደኞቼ  በሙሉ በአካል አጠገቤ ቢሆኑም በውስጤ የተፈጠረውን የብቸኝነት  ስሜት ሊያስታግሱት አልቻሉም:: ጭንቀትና የስሜት አዘቅት እየተፈራረቁብኝ ነው......


ሐሙስ ታህሳስ አራት  ቀን 1988 ዓም 

አሁን ከቀኑ ስድስት ሰዓት ነው:: መኝታ ቤታችን ውስጥ ካለው ግዙፍና ባዶ ጠረጴዛ ፊት ተቀምጫለሁ:: ቤተማርያም ትናንት ፈተናውን ያጠናቀቀ በመሆኑ ዛሬ ለሽ ብሎ አልጋው ላይ ተኝቷል ::በዚህ ሰዓት መንጌ ምናልባት የርሱን ፈተና ጨርሶ ይሆናል::  ገና አልመጣም:: ከዚህ መኝታ ክፍል እኔ ብቻ ነገ እፈተናለሁ:: ከጭ ንቀቱና ከስሜት አዘቅቱ ላይ ዛሬ ድካም ታክሎበታል-ጎሽ! ደ ብተርም ሆነ መፅሐፍ ማየት አስጠልቶኛል....

በነገራችን ላይ ዛሬ ጠዋት ከቤት በፖስታ የተላከልኝን  ወርሓዊ ሃምሳ ብር ጅማ ፖስታ ቤት በመሄድ በጠዋት ከተቀበልኩ በሁዋላ የነበሩብኝን የሱቅ ዱቤዎች ከፍዬ ባሁኑ ሰዓት ከወጪ  ቀሪ ምንም የለኝም:: ወደፖስታ ቤት ከመሄዴ በፊት በነበርኩበት አቁዋም ላይ ነኝ :: አሁን ያማረኝ አጭር የመኝታ ግዜ ውይንም ናፕ ነው፣ ከተቻለ :: ስህተት መሆኑን ባውቅም በተደጋጋሚ ፈተናዬ ከባድ ይሆናል ብዬ ማሰቤን መተው አልቻልኩም......