Wednesday, March 11, 2015

ማክሰኞ ሰኔ 2 ቀን 1984 አ.ም. ከሰአት 11 ሰኣት ከ 52 ደቂቃ
እፅዋትን ልምላሜ: የጨረቃን ድምቀትና የጸሃይን ጥልቀት አንጸባራቂ ብርሃን  በሂወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ማድነቅ የቻልኩት ጅማ ከመጣሁ ወዲህ ነው:: ጅማ ከአመት አስከ አመት ኣረንጓዴ ነው.....ትናንትና ሰኔ ግም አለ! ሰማዩም ላይ ጥቁር ደመናዎች ይታዩ ጀመር:: በጅማ ይህም ያምራል...... ብቻ በክረምቱ መግባት የሚያስፈሩኝ ሁለት ነገሮች አሉ:: ጭቃና የመብራት መቋረጥ::በዛሬአው ቀን አናቶሚ የጽሁፍ ሀተታ ፈተና ወሰድን:: ስለፈተናው ከባድ ይሁን ቀላል ለመናገር ይከብደኛል:: ውጤቱ ሲመጣ ማየት ይሻለኛል....

ሰኔ ዘጠኝ ቀን 1984 አ.ም.
ባለፈው ከባድ የዝርፊያ አደጋ ተፈጸመብኝ:: አጥቤ ያሰጣሁት ሁለት ሱሪ ፥ ሁለት ሹራብ፥ አንድ ጃኬት፥ ሶስት ካኒቴራ፥ አንድ  ቲሸርት፥ አንድ ፎጣና ሁለት የትራስ ልብስ ተሰረቀብኝ:: ደርቋል ብዬ ልሰበስብ ስሄድ ደርቄ ቀረሁ:: የልብስ መስቀያው ገመድ ባዶውን በንፋስ ይወዛወዛል:: ይህን አደጋ ተከትሎ በርካታ የማጽናኛ ቃላት ከጓደኞቼና መኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ የጎረፉ ሲሆን ወዲያውኑም የልብስ ልገሳና ውሰት ሀሳቦች ቀርበውልኛል:: ከሁሉም ደስ የሚለው ነገር ግን የተሰረቀው ልብስ ብዙ ስለነበር ለማዘን አለመመቸቱ ነው:: በዚያ ፈንታ ወዲያው ረሳሁት:: ለነገሩ የፒሲዋን ትምህርትም ለሃዘን ጊዜ የሚሰጥ አይደለምና ኑሮዬን አንደቀድሞው ቀጠልኩ......

ስኔ 11 ቀን 1984 አ.ም. ከምሽቱ ስድስት ሰአት- ስለ ማሂ
ዛሬ ቀን በፊዚዮሎጂ ከፍለጊዜ Cardiovascular System ተጀመረ::ፕሮፌሰር ማሂ አየፈጠነ በመናገሩ በቅጡ የገባኝ ነገር አልነበረም:: ይህን መምህር በዚህ በመፍጠኑ የተነሳ አየጠላሁት ነው:: ለነገሩ ሲያስረዳ ከመፍጠኑም ባሻገር ለኛ ለኢትዮጵያውያን ንቀት ያለው መስሎ ስለሚሰማኝ ቀልቤ አይወደውም:: በእውቀቱ እጅግ ይመካል:: አንዳንዴ ያለምንም ምክንያት የሚሰጠንን ሌክቸር ምስቅልቅሉን ያወጣውና ግራ ያጋባናል:: ያደናብረናል:: እንደሌሎቹ ግብፃውያን መምህራን የተወሰነ ሪፈረንስ መጽሃፍ አይከተልም:: ከትምህርት ውጭ በሆነ ነገር እንኩዋን ከተናደደ ቁጭቱን ሌክቸሩን በማበላሸትና አኛን ግራ በማጋባት ይወጣል:: ብዙ ጊዜ ትልልቅ አንቱ የተሰኙ መፅሀፎችን በስም እየጠራ ይተቻል፥፥ ያንቋሽሻል፥፤ በጣም ሲበዛ ጉረኛ ነው....ማሂ 

Friday, March 6, 2015

የወርሃ ግንቦት ትዝታ- ግንቦት መጨረሻ 1984 አ.ም.

የፒሲዋን ትምህርት ሂደት ተጧጧፈ። ትምህርት በትምህርት ላይ ተከመረ። በተለይ ወደ ኢትዮጵያ ዘግይቶ የደረሰው የፊዚዮሎጂ መምህራችን ፕሮፈሰር ማሂ ጠዋትም ከሰአትም ያስተምረን ገባ። በየቀኑ ለአራት ሰኣት ያህል ፊዚዮሎጂ እንጠጣለን ። አናቶሚና ባዮኬሚስትሪም ሂደታቸውን ቀጥለዋል። በግሌ የምለው ነገር ቢኖር ወደ ሌክቸር ሆል በየቀኑ በመሄድ ትምህርት መጠጣቴን ብቀጥልም ለማንበብ ግን ጊዜ በጣም እያጠረኝ መጥቷል።አብሮም የጭንቀቴ መጠን አይሏል። ጭንቀት ደሞ እንቅልፍ ይከለክል የል ? በቃ መተኛት አልቻልኩም። እንደተለመደውና እንዳቀድኩት ዘወትር ከሰአት ለአንድ ሰአት ያህል ናፕ መውሰድ ኣልቻልኩም። እስከ ኢኩለ ሌሊት ማምሸቴን ቀጥያለሁ። ብዙ ጊዜ ወደ አልጋዬ የምዞረው ከምሽቱ ስድስት ሰአት ተኩል ሲል ነው። በነገራችን ላይ እሁድና ቅዳሜንም በንባብና የጻፍኳቸውን ኖቶች በማስተካከል ስለማሳልፍ ከሰኞ እስከአርብ ካሉት ቀናት ያላቸው ልዩነት ደብዝዟል።

አንዳንዴ ጭንቀቴን ለመርሳት ይመስላል በምልሰትና በትዝታ ወደኋላ ሂጄ በዚያው እቀራለሁ። አሁን ካለሁበት ይልቅ የቀድሞው የልጅነት ጊዜዬ ብርቅና አስደሳች የነበረ ሆኖ ይታየኛል። የአሁኑ የኮሌጅ ውስጥ ኑሮ ምንም ጣአም የሌለው ይሆንብኛል። ሃይ ስኩል በነበርኩ ግዜ ለትምህርትና ለምርምር የነበረኝ ፍቅር ጥልቅና ጠንካራ ነበር። ለሙዚቃና ለቲያትርም እንደዚያው። የማትሪክን ፈተና ከተፈተንኩበት መጋቢት ውጤት እስከሰማሁበት ነሃሴ ወር ድረስ ያሳለፍኳቸው ወራት ስለውጤቴ እያሰብኩ የነበር ቢሆንም በጭንቀት ደረጃ አሁን ካለሁበት እጅግ እጅግ የተሻሉ ነበሩ። ያኔ በግማሽ ልጅነት በግማሽ ወጣትነት ውስጥ ሆኜ በርካታ የአማርኛ ልቦለድ መጽሃፍቶችን ያነበብኩበትም ጊዜ ነበር። የዛሬ አመት ደግሞ በብላቴ የጦር ማሰልጠኛ ካምፕ የመጨረሻ ቀናት ግርግር የነበረበትና እኔም ከዚያ ወደ አዲአበባ ለመሄድ ከጓደኞቼ ጋር ይወስዷችኋል ተብለው በደርግ መንግስት ቃል የተገቡልንን አውቶቡሶች መምጣት የምጠብቅበት ወቅት ነበር። አውቶቦሶቹ ግን የውሃ ሽታ ሆነው በመቅረታቸው ወደ ስልሳ ኪሎ ሜትር የሚሆነውን ከብላቴ እስከ ሞርቾ (ከኣዋሳ 25 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ከተማ) የተዘረጋውን የኮረኮንች መንገድ በእግር ተጉዘናል። በህወቴ የመጀመሪያው ረዥምና ኣድካሚ ጉዞ ነበር። በዚያ ጉዞ ላይ ከቤተሰቤ ጋር ዳግመኛ አልገናኝ ይሆን? ብዬ አስቤ ነበር.... አሁን አኮ ምንም በማይጥምና ተደጋጋሚ የሆኑ አሰልቺ ድርጊቶች  በሚከናወኑበት ጊዜ ላይ ነው ያለሁት! ምንም ትዝታ በማይጥል ሽክርክሪት ውስጥ። በእርግጥ ፕሲዋን ሌላ የሂወት ኮረኮንች ቢባል ሲያንስ ነው...........

በጅማ የግንቦት ቀናት እየተፈራረቁ አለፉ።ይዘንባል ደሞም ደረቅ የሆናል። ባለፈው ፍንትው ስትል የንበረችው ጨረቃ ወደ ወሩ መጨረሻ ከሰመች። እናም  ምሽቶቹ ጥቁር መሆን ጀመሩ። አንዳዴም ጥቁር ምሽቶች ከዝናብ ጋር ተቀላቅለው ቀኑን የበለጠ ከባድ ያደርጉታል። እንደፒሲዋን ተማሪዎች ለሚራወጥና እውቀት ባህር ውስጥ ተዘፍቆ ሌተቀን ራሱን ንባብ ውስጥ ለደበቀ ግን የቀኖቹ መፈራረቅና መለዋወጥ በእውነቱ ትርጉም የለውም.....