ህዳር 7 1986 አ.ም.
የንቃት ጅማሬ
ትናንትና በድንገት ከቅርብ
ጉዋደኛዬጋ ፍራሽ ላይ ተቀምጬ የጅማን ጫት በአፌ ውስጥ አኖርኩ: : በሂወቴ ጫት ስነካ የመጀመሪያዬ ነው:: ጫቱን አፌ ውስጥ አስገብቼ
አኘኩት: እኛኪውንም መጠጥኩት:: እኔና ጉዋደኛዬ ከፊትለፊታችን ፍራሹ ላይ ግማሽ እግሮቻቸው ባለ አስር ሳንቲም ፌስታል ውስጥ ያረፉ
የጫት ዝንጣፊዎችን በግራ እጆቻችን በመያዝ በቀኝ እጆቻችን ቀንበጦቹን
አሁንም አሁንም ወደ አፎቻችን በማስገባት አሻመድናቸው:: በቀንበጦቹ ድዶቻችንን አስታከን ለጋ ጉንጮቻችንን ወጠርናቸው: ለተወሰኑ
ደቂቃዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አወጋን:: ቧልት እየቦለትን ተሳሳቅን:: አንዳንድ ያጋራ የሆኑ ምናባዊ ሀስቦቻችንን ተለዋወጥን::ከዚያም
ፊቶቻችን መሞቅ: ማብለጭለጭና መቅላት ጀመሩ:: አፍታም ሳንቆይ ነቃን:: ወጣት አእምሮዎቻችን ለአትኩሮት ተዘጋጁ:: የእጅ, የእግርና
የወገብ ጡንቻዎቻችን ተፍታቱ:: ወደ pathology ንባባችን ገባን:: በበኩሌ ሃሳቤ ተሰባስቦ ካነበብኩባቸው ጥቂት የሚታወሱ ቀናት
ይህ አንዱ ነው::
በትናንትናው የጥናት ስኬት
በመነሳሳት ታዲያ ጫትን ዛሬም ደገምኩት:: ነገር ግን ውጤቱ እንደንትናንትናው ሊሆን አልቻለም:: አለመሆን ብቻ ሳይሆን እንደ ድካም:
እንደመዛል አድርጎ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደኝ: ከቀኑ ሰባት ሰዓት የተኛሁ አስር ሰዓት ላይ ተነሳሁ:: ከዚያም ወደ ቤተ መፅሃፍቱ
በመሄድ እስከምሽቱ ሶስት ሰዓት ድረስ አጠናሁ...የእንቅልፉ ነገር ቢገርመኝም ህዳር 8 ቀንም እንደቃምኩ ግን ልብ በል/ይ...የሆነ
ጥቅም ያለው መስሎ ተሰምቶኛል...
ህዳር 17 ቀን
1986 አ.ም.
የልቤ ወግ
እንደምን አለሽ ማስታወሻዬ::
እኔ መችም አለሁ:: ምንም አልልም:: በሶስተኛ ዓመት የበረታው የልቤ መከፋት እንደቀጠለ ነው:: ይህን ስል ግን በጉዋደኞቼም ሆነ
በሌሎች ሰዎች ፊት ደስታኛና መልካም መስዬ መቅረቤ እንደቀጠለ መሆኑን ላስታውስሽ እወዳለሁ ::
ልቤን በብርቱ እያስከፋው
ያለው ነገር የሶስተኛ ዓመት ህክምና ትምህርት የፈተና ውጤቶቼ ከከዚህ ቀደሞቹ አንፃር አመርቂነት እያነሳቸው መምጣቱ ነው:: የዚህ
ዋናው ምክንያት ግልፅ ነው: በንባብና በጥናት አለመትጋቴ ነው:: ለማወቅ የከበደኝ ግን ለምን እንደማልተጋ ነው:: በውስጤ ግዙፍ
የሆነ የትምህርት ፍላጎት ማነስ አለ:: እስካለፈው ሰሞን ድረስ ቀዶ ጠጋኝ ሀኪም ( surgeon) ለመሆን እመኝ ነበር:: አሁን ግን ይህ ምኞት እውነተኛ ምኞቴ እንዳልሆነ ሆኖ ተሰማኝ:: ስለዚህም
አዳፈንኩት:: አሁን በቃ የህክምና ትምህርቴን ለመጨረስ ብቻ ነው የማስበው:: ከዚያ በሁዋላ ወደ ስነ-ጥበብ (Art) ለመግባት
ሕልም አለኝ:: ይህ ሕልም አሁን የተፈጠረ አይደለም:: እኔ ሃይስኩልም ሆነ ከዚያ በታች ስማር በነበረበት ወቅት በግጥም ገጣሚነት:
በድርሰት: በስእል: እንዲሁም በዘጋቢነት የጎላ ተሳትፎ ነበረኝ:: እንደውም አንዳንድ መምህራንና ጉዋደኞቼ የከፍተኛ ትምህርቴን
ከሳይንስ ይልቅ በአርት መንገድ እንዳደርገው መክረውኝ ነበር:: ለምን በአርት መንገድ እንዳልሄድኩ በውል አላውቀውም:: ነገር ግን
ባዮሎጂ : ፊዚክስና ሂሳብ ትምህርቶችን ጥልቅ በሆነ ፍላጎት (passion) እወዳቸው እንደነበር አውቃለሁ:: ሳይንስ ተጨባጭ ስለሆነ
ይመቸኛል:: ከሳይንስ ትምህርቶች ውስጥ ሕክምናን እንድመርጥ ተፅዕኖ ያሳደሩብኝ ሶስት ሁኔታዎች ይመስሉኛል:: አንደኛ ባደኩበት
አካባባቢም ሆነ ከዚያ በሰፋው ማህበረሰባችን ሕክምናና ሀኪም የተሰጣቸው አክብሮትና ስፍራ የትየለሌ መሆኑ: ከዚህ በፊት
እንዳልኩት ጮርቃ ልጆች ሆነን ስታድግ/ጊ ምን ለመሆን ነው የምትፈልገ/ጊው ተብለን ስንጠየቅ ብዙዎቻችን የምንመልሰው “ዶክተር”
ብለን ነበር:: ሁለተኛው ምክንያቴ የአስራሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ በሆነው የማትሪኩለሽን ፈትና ባዮሎጂና ሂሳብ “A” ነገር ግን ፊዚክስ “B” ማግኘቴ ነበር:: ከሶስቱ
የምወዳቸው ትምህርቶች ወስጥ ፊዚክስን የበለጠ ነበር የምወደው:: ነገር ግን ይህን የፈተና ውጤት ካገኘሁ በሁዋላ ቆም ብዬ አሰብኩ::
በዚህ ምክንያት ኢንጂነሪንግ ወይም አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ምርጫዬ ሳይሆን ቀረ:: ሶስተኛውና በመጨረሻው ሰዓት ላይ ተፅዕኖ ያሳደረብኝ
የትምህርትቤቴ (የአዲስከተማ) ተማሪዎች ዲን የነበረው ሰው (ስሙን ሳልረሳው አልቀረም ግን መኩሪያ ይመስለኛል)በማትሪክ ጥሩ ውጤት ያመጣነውን ተማሪዎች ሰብስቦ የተናገረን ነገር ነው::
በትክክል ቃል በቃል ባላስታውሰውም እንዲህ ያለ ይመስለኛል:: “ውጤታችሁ
3.6ና ከዚያ በላይ በላይ የሆነ ተማሪዎች ሜዲስን ትምህርት መምረጥ አለባችሁ: ከባድ ቢሆንም በጥሩ ሁኔታ ትወጡታላችሁ የሚል ከፍተኛ
እምነት አለኝ:: ሌሎቻችሁ ግን ከሜዲስን ውጭ የሆኑ ትምህርቶች ላይ አተኩሩ::” በዚህ አነጋገሩ የሜዲስን ትምህርትን ከባድ ብሎ
ቢፈርጀውም ለኔ ልዩ (ብርቅ) አድርጎ አቀረበው:: ለተወስንነው ብቻ የሚሰጥ እንደከበረ ድንጋይ እንደልብ የማይገኝ አርጎ አቀረበው:: ስለዚህም ከላይ ከጠቀስኩዋቸው ሁለት ምክንያቶች
ጋር ተዳምሮ በውስጤ በነበረ የተለየውንና ብርቁን ነገር የመሻት ተፈጥሮአዊ
ግፊት ሜዲስንን ለመማር መረጥኩ::
የህክምና ትምህርት በየቀኑ
እጅግ በጣም ረዥም ለሆነ ሰዓት በትዕግስት ሃሳብን አሰባስቦ አእምሮን አሹሎ ማንበብን ይጠይቃል:: በእርግጥ ይህን ማድረግ የሚችሉ
አንዳንድ ብርቱ ጉዋደኞቼ አሉ:: ጉዋደኞቼ ካልሆኑትም ውስጥ ጎበዝ የምላቸው አንባቢዎች አሉ:: እነዚህ በጅጤሳ አነጋገር “በራቾች”
ይባላሉ:: ብረት ከሚለው ቃል የተወሰደ ነው:: ሕክምና ትምህርት ከተነበበ በሁዋላ ደግሞ ማስታወስን ይፈልጋል:: አንብበው የሚያስታውሱ
የመኖራቸውን ያህል ብዙ አንብበው ግን በበቂ ሁኔታ ማስታወስ የሚሳናቸው አሉ:: እነዚህ ያሳዝኑኛል:: አንዳንዶች ደግሞ አሉ::
በቃ በቀላሉ የሚገባቸው:: የሚገልፅላቸው:: እነዚህ ብዙ ማንበብ አያስፈልጋቸውም:: ፈተና ላይም የሚችላቸው የለም:: ያስቀናሉ::
በፍጥነት ማንበብ የሚችሉ ደግሞ አሉ:: ቶሎ ቶሎ የሚያንቡትን ደብተርም ሆነ መፅሐፍ ይገልጡታል:: እንደነዚህ አይነቶቹ አጠገብ
ተቀምጦ ማጥናት ሰቀቀን ነው:: ከማስደንገጡም ባሻገር የሞራል ውድቀት ሊያስከትል ይችላል::
ታዲያ እኔ የቱ አይነት
ነኝ? ለረዥም ሰዓት ተቀምጠው ማንበብ ከሚችሉት ወገን እንዳልሆንኩ መቸም ግልፅ ነው:: ተፈጥሮዬ አይፈቅድም:: በፍጥነት ከሚያነቡት
ውስጥም አይደለሁም:: ብዙ የማያነቡ ካሉ እኔ ከነሱ ወገን ነኝ::
ከላይ እንዳልኩት በዚህ
ሰዓት የህክምና ትምህርት ፍላጎቴ ክፉኛ ዳሽቁዋል:: ምናልባት ትንሽም ቢሆን ያነበብኩትን አስታውሳለሁ መሰለኝ.......ከሴሚስተር
ወደ ሴሚስተር በመሽጋገር ለሶስተኛ ዓመት የመጨረሻ ማጠቃለያ ፈተና ሰሞን ደርሻለሁ::
ሕክምና ትምህርቴን ለመጨረስ
ቁርጠኛ ውሳኔን በልቤ አኖርኩ: ዛሬ.....