Thursday, November 24, 2016

ጳጉሜ 6 ቀን 1987 ሰኞ
ዛሬ 1987 .. የመጨረሻ ቀን ነው: ጳጉሜ 6:: የዶርሚቶሪ አልጋዬ አጠገብ ብቻዬን በትካዜ ተቀምጫለሁ:: በክፍሉ ዉስጥ ከኔ በስተቀር ማንም የለም::: በልቤ ውስጥ ያለን ነገር ለማውጣት እየታገልኩ ነው:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም የተለያዩ ሀሳቦች በእንግሊዝኛ አምሮዬ ውስጥ ይመላለሳሉ ግን በጽሁፍ አሳምሬ እንዳላስቀምጣቸው የቁዋንቁው ችሎታ ያጥረኛል:: በክፍሉ መስኮቶች አሻግሬ ስመለከት ዝናብ ሲዘንብ ይታየኛል ድምፁ ግን አይሰማኝም:: ቀፋፊ ቀን:: ምንም የምሰራው ነገር የለም:: የአዲስ አመት ዋዜማ በመሆኑ የትምህርተ-ሂወት እንቅስቃሴ ሁሉ ቀጥ ብሏል:: ከቤትና ቤተሰብ ርቄ ያለሁ በመሆኔ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በዚህ ያመትባል ዋዜማም ጥልቅ ድብርት እየተሰማኝ ነው:: ላደለው የአዲስ ዓመት ዋዜማ ልዩ ቀን ነው:: ጥፍጥናው ከዋናው አመትባል የሚልቅበት ግዜ ይበዛል…….

በተረፈ ነገ ሌላ ቀንና አመት ነው:: ይህን እመሰክራለሁ::


መስከረም 1 1988 እንቁ ለጣጣሽ!
“አበባዮሽ ቁሙ በተራ እንጨት ሰብሬ ቤት እስክሰራ” የሚለውን የዚህን አመትባል የእንስቶች ተወዳጅ ዘፈን አስታወስኩ:: በተለይም ሁለተኛው ስንኝ ከኔና ከአብሮ ተማሪ ዋደኞቼ ፊት ለተደረደሩት የአምስተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርት  ወሳኝ ወራት ጥሩ መግለጫ ነው:: ሁላችንም ዘንድሮ እንጨት ሰብረን ቤት መስራት ይጠበቅብናል……
  
እንቁጣጣሽ ለት አየሩ የሚደብር አልነበረም:: ጥሩ መልካምና ብራ ቀን ነበር:: ጠዋት እንደተለመደው ከጉዋደኞቼጋ ወይዘሮ አልማዝ ቤት ሂደን እንኩዋን አደረሳችሁ ካልን በሁዋላ የደንቡን ባህላዊ ዶሮ ወጥ ምግብ ተመገብን::  ከዚያም እየተጫወትን በዚያ ቆየን:: ከሰአት ምሳ ዘውድነህ ቤት ተጋብዤ ነበር:: ዛሬ መቸም የመብልና የመጠጥ ቀን ነው:: ዘውድነህ የተማሪዎች ዲን ቢሮ ሃላፊ ነው:: ዘውድነህን የተዋወኩት በተሰፋሁነኝ በኩል ነው:: በዘውድነህ ቤት ዶክተር ተስፋም ነበር የዘውድነህ ባለቤትም እንዲሁ:: ቆንጆ ያመትባል ምግብ ተዘጋጅቶ ነበር:: ብዙ ጠላ በመጠጣቴ ደክሞኝ ስለነበር ከዚያ እንደተመለስኩ መኝታ ክፍሌ ገብቼ ተኛሁ::

መስከረም 2 1988 ሮብ
ሁሉም ነገር ወደነበረበት ተመለሰ:: አመቱ ብቻ ተለውጧል:: ስለዚህም ማጥናት ነበረብኝ:: ዛሬ Fluid and Electrolyte Managementንዲሁም Breast Diseases ለማንበብ ሞክሬ ሁለቱም ጭብጦቻቸው በቀላሉ አልፈታና አልገለፅ ብለውኝ ስለነበር ተበሳጭቼ ዋልኩ::

መስከረም 3 1988 ሃሙስ
ዛሬ ቀን እንዴት Femoral Hernia በቀዶ ጥገና እንደሚስተካከል እየረዳሁ አየሁ:: በምሽቱ በድንገተኛ ክፍል ተመድቤ ነበር:: ኢንተርንሺፕ ሃኪሞች ባጋጣሚ ባለመኖራቸው የነሱን ስራ ተክቼና ሙሉ በሙሉ ራሴን ችዬ የመስራት እድል አጋጥሞኝ ነበር:: በመሆኑም ለመጀመሪያ ግዜ በሽተኛን ወደ ህሙማን ክፍል ገብቶ እንዲታከም አዘዝኩ:: ረዥሙን ፊርማዬን ካርዱ ላይ በማኖር ህመምተኛን ኣድሚት  (Admit) አደረኩ:: ለመጀመሪያ ግዜ የወሰንኩት Clinical Decision…. ከባድ ውሳኔ ነው::  ግን ደስ አኝ:: ወንዳታ አልኩት ራሴን:: ህመምተኛዋ 10 ወር ህጻን ስትሆን በሳምባ ምች (Brncopneumonia) ነው የመጣችው:: እብቅ እብቅ ትተነፍሳለች:: በትንፋሽ ማጠር ምክንያት የእናቷን ጡት መጥባት አልቻለችም:: የሳንባ ራጅ አዝዤ ተሰራላት:: ራጁ ተሰርቶ መጣ:: አየሁት:: ሳምባዎችዋ ሙሉ በሙሉ በደዌው ቆስለዋል:: “በደምስር የሚሰጥ ጸረ ተውሳክ (Antibiotic)ና ኦክሲጂን ባስችኩዋይ ያስፈልጋታል” አልኩዋቸው  ለእናቷና እናቷን አጅበው ለመጡት ቤተዘመዶች :: ስለዚህ በህፃናት መኝታ ከፍል ቆይታ መታከም አለባት:: በኔ ውሳኔና ትዕዛዝ መሰረት ሚጢጢዋ ፍጥረት በእናቷ እቅፍ ውስጥ ሆናና በቤተዘመድ ታጅባ ወደ ሕፃናት መኝታ ክፍል ስትወሰድ እያየሁ……”እውነት ነው?” አልኩ በውስጤ


Sunday, November 6, 2016

ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜ 5 1987 አ.ም.

በሳምንቱ መጀመሪያ እሁድ  ላይ አንድ ከአዲሳበባ በቅርብ የመጣና ለጊዜው ስራው ጅማ የሆነ ጉዋደኛዬ ባደረገልኝ ግብዣ መሰረት ከሰአቱን ከእርሱጋ አሳለፍኩ:: በመሰረቱ ጥሩ ምሳ ከበላን በሁዋላ እርሱ መኖሪያ ቤት ወለል ላይ በተዘረጋ ቀጭን ፍራሽ ላይ ዘና ብለን ተቀምጠን ንቃተ ህሊናችንን በአረብ ተራ ጫት ቀንበጥ የበለጠ አንቅተን ቧልት የተቀላቀለበት ፍልስፍና ስንሰልቅና የተለያዩ የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎች ስናዳምጥ ዋልን:: በጣም የምቀርባቸውና የምወዳቸው ሁለት ጉዋደኞቼ መንጌና አብይ አብረውኝ ነበሩ::

በማግስቱ ሰኞ በቀደመው ሳምንት የነበረኝን ሕክምና የመማር ልበሙሉነትና ተነሳሽነት የሚያሰርዝ ሁኔታ ገጠመኝ:: ከህሙማኖቼ መካከል አንደኛው  የእግሩ ጡንቻ በሰፊው በመምገሉ (pyomyositis) ጉልበቱና ብሽሽቱ ላይ መሸማቀቅ ደርሶበት እግሩ ባጠቃላይ መዘርጋት አልቻለም (Contracture):: ለዚህ ህመምተኛ የእግሩን ቆዳ በሰፋፊ የቁስል ፕላስተር በመለጠጥ እግሩ እንዲዘረጋ ለማረግ (Skin traction) አስቤ ግን ከዚህ በፊት ሰርቼው የማላውቅ ነገር በመሆኑ ሳልፈፅመው አደርኩኝ::

ማክሰኞ ቁጥር 6 አልጋ ላይ አዲስ ህመምተኛ ነበረኝ:: አንድ ቁመቱ አጭር ሰውነቱ የፈረጠመ  ሰው ነው:: ግራ ደረቱ ላይ አንበሳ ቦጭቆት ነው ወደ ሆስፒታሉ የመጣው:: አንበሳ ፔክቶራሊስ ሜጀሩንና ማይነሩን (Pectoralis major & minor) ገሽልጦ ሰልቅጦታል:: በአንበሳ የተነከሰ ሰው ለመጀመሪያ ግዜ ማየቴ ስለነበር ሰውዬውን  ራሱ እንደ አንበሳ እየፈራሁ ነው ያናገርኩት:: ሰውዬው ፈርጣማ በመሆኑ ነው መሰል የግራ ደረት ጡንቻው ከቦታው ከመጉደሉ በስተቀር ሌላ የህመም ምልክት ሳይታይበት አንዳልታመመ ሰው ነው ያነጋገረኝ:: ይህ ሰው የሚኖርበት አካባቢ በቅርብ ርቀት አንበሶችም እንደሚኖሩና እሱን የነከሰችው  ሴት አንበሳ መሆኗን ነገረኝ:: አንበሲቷ እየነከሰችው  ሳለ ጎረቤቶች ደርሰው አስጣሉትና ይዘውት ወደ ሆስፒታሉ መጡ:: ቁስሉ በድንገተኛ ክፍል የመጀመሪያ እርዳታ ከተደረገለት በሁዋላ ወደመኝታ ክፍል የመጣው በዋናነት ፀረ ህዋስ መድሃኒት (Antibiotic) በደም ስሩ መሰጠት ስላስፈለገው ነው::

እሮብ ጳጉሜ አንድ ቀን ከቤት የላክልኝ ሃምሳ ብር ከእናቴ የደመቀ ሰላምታ ጋር ደረሰኝ:: ይህ በሆነ በሶስተኛው ቀን ቅዳሜ ጳጉሜ 04  ከኛ በሁለት ዓመት የሚበልጡን ሐኪሞች (the 1987 graduates) በመመረቃቸው  በጅማ ሆቴል ያዘጋጁትን የምሽት ዳንኪራ ስካፈል ሃምሳ ብሬንም በሆቴሉ ውስጥ ላለው ባር አካፈልኩ :እነሱም መጠጥ አካፈሉኝ: የኔም ራስ ለሁለት ተከፍሎ ከውድቅት ወዲያ ወደመኝታ ክፍሌ ደረስኩ::


እሁድ ጳጉሜ 5ን በሃንጎቨርውስጥ አሳለፍኩ:: የዚህ ዓመት ጳጉሜ 6 ቀን በመሆኑ እሁድ አዲስ ዘመን ዋዜማ አልነበረም:: 

Wednesday, November 2, 2016

የቀዶ ጥገና አንድ ሳምንት ነሐሴ 22 -26 1987 አ.ም.

ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 1987 አ.ም.
እኔና እኔ ያለሁበት ቡድን ዛሬ በጠዋት የአምስተኛ ዓመት የቀዶጥገና (Surgery) አታችመንት ጀመርን:: በደፓርትመንት ኃላው በዶ/ር አለምሰገድ ቢሮ ተገኝተን ከእርሱ መመሪያና ምክር ተቀበልን::  ዶ/ር አለምሰገድ ሰባት ሳምንት በሚፈጀው ቀጣዩ የቀዶ ጥገና ልምምድና ሥራ (attachment) የሚከናወኑ ተግባራትና ከኛ የሚጠበቀውን ዝግጅት አስረዳን:: የመጨረሻ ዓመት ላይ የምንገኝ በመሆኑ ጠንክረን እንድናጠና አስጠነቀቀን::  በዚህ እለት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ወደ ሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና መኝታ ክፍል በመሄድ የተመደቡልኝ ህሙማን ተዋውቄና በማግስቱ ተመልሼ እንደማያቸው ቃል ገብቼ ተመለስኩ:: አሁን እንደአምናው በሽተኛ መቅረብ በፍፁም አይከብደኝም:: አራተኛ ዓመት ሲጀመር የመጀመሪያውን ህመምተኛ ለማናገር የነበረኝን ፍርሃት እስካሁን አልረሳውም:: ዛሬ ሁሉ ቀላል ነው:: ደሞ ህመምተኛ ማናገር ምን ይከብዳል?

ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 1987 አ.ም.
ዛሬ ከዶ/ር ግዛውጋ ቀላል ቀዶ ጥገና አደረግን Herniotomy & Hernioraphe of Epigastric Hernia:: ለመጀመሪያ ግዜ በቀዶ ጥገና ግርዛት (Circumcision) ያየሁትም ዛሬ ነው:: ከሰዓት በሁዋላ ወደ ሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና መኝታ ክፍል በመሄድ የተመደቡልኝን ህሙማን በሙሉ መርምሬና መዝገባቸውን አገላብጬ እንዲሁም የበኩሌን ዘገባ ስለእያንዳንዳቸው ፅፌ አጠናቀኩ:: ለነገ ተዘጋጀሁ::

ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 1987 አ.ም.
ዶ/ር ግዛው ዛሬ ሁሙማኑን በሙሉ እየዞረ ጎበኘ: መረመረ:: እኛም ስለህመምተኞቻችን የዘገብነውን አነበነብንለት:: ይሆናል ያልነውን የላቦራቶር መርመራና አስፈላጊ ሕክምና ጠቆምን: ተናገርን:: እሱም አንዳንዱን ሲከለክል አንዳንዱን ደግሞ ይሁን አለ:: የከለከለውንም ለምን እንደከለከለ አስተማረ:: ከዚያም ከሰዓት ሆነ:: ዘመኑ እና ዮናስ የሚባሉት የኔ ቡድን አባላት ሴሚናር አዘጋጆች ነበሩ:: ይህ በሆነ አርስት ላይ መፅሐፍ አገላብጦና አንብቦ ለታዳሚ የሚቀረብበት ዝግጅት ነው:: በዝግጅቱ መጨረሻ ላይ ታዳሚ ከበድ ያለ ጥያቄ ሊሰነዝር ይችላልና አቅራቢ ሲኮን ያሳስባል:: ዘመኑ እና ዮናስ ዶ/ር አለምሰገድ ባለበት አቀረቡ:: ምንም የተለየ ነገር ሳይኖር ተጠናቀቀ:: በዚህ ቀን ምሽት በቀዶ ጥገና ድንገተኛ ህሙማን የሚታዩበት ክሊኒክ ውስጥ ተረኛ ነበርኩ:: እስከምሽቱ ሶስት ሰዓት ተኩል በዚያ ቆየሁ::

ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 1987 አ.ም.
በዚህ ቀን ደግሙ ከባድ ቀዶ ሕክምና ክፍል (Operating Theatre) ውስጥ ነበርኩ:: ሁለት ቀዶ ጥገናዎች ተደረጉ:: አንደኛው የሆድ ቀዶ ጥገና ሲሆን ህመምተኛዋ ለአንድ አመት ያክል ግዙፍ እባጭ በሆዷ ተሸክማ የቆየች ናት::  ሌላኛው  አንዲት ትንሽ ሴት ሕፃን ልጅ እጇን አንድ አዋቂ ሳያስበው በመጥረቢያ ቆርጦት ነው:: ታሪኩ ቢዘገንነኝም ቁስሏ ሲሰፋና ሲዘጋ እያገዝኩ ተመለከትኩ:: ታዲያ ዛሬ ቀዶጥገና ከሕክምና ትምህርቶች ሁሉ የሚስብ ሆኖ ታየኝ:: ቅፅበታዊ ቀዶ ጠጋኝ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ:: ለዚህም ነው ቀዳጁን ዶ/ር ሚናስን አራተኛ ዓመት እያለሁ በጣም የተደሰትኩበት የህክምና ትምህርት ምን እንደሆነ ሲጠይቀኝ ቀዶ ጥገና! ብዬ የመለስኩለት:: እሱም በጣም ከት ብሎ ሳቀ:: መልሴ የታሰበበት እንዳልሆነ ገብቶታል::


አርብ ነሐሴ 26 ቀን 1987 አ.ም.

ዛሬ ጠዋት በታማሚ አልጋ ዙሪያ ቆመን የምንማርበት ከፍለግዜ (Bed Side) ነበረን:: ህመሙ Gastric outlet obstruction (GOO ብለን አሳጥረን የምንጠራው) ነበር:: አስተማሪው ቀዳጅ ሀኪም ዶ/ር ሚናስ ነበር:: ከሰዓት በሁዋላ ደግሞ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለን ስለ አንድ በሽታ ሕክምና በቻ በጥልቀት የምንወያይበት ክፍለግዜ (Management Session) ነበር:: ትምህርቱ ጅማ ሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ እየታከመ ያለ ወይም ታክሞ የነበረ እውነተኛ ህመምተኛ ላይ ተንተርሶ የሚሰጥ ነው:: የዛሬው ያተኮረው a case of traumatized patient and head injury ላይ ነበር:: አስተማሪው ቀዳጅ ሀኪም ዶ/ር ግዛው ነበር::