Sunday, September 27, 2015

ቅዳሜ ህዳር 12 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 8 ሰዓት ከ 32 ደቂቃ

የህዳር ትዝታ

ህዳር...ህዳር.. መልካም ወር...ደስ የሚል ወር ...የፍቅር ትዝታ ወር:: 

አሁን ካለሁበት ይበልጥ ልጅ እግር በነበርኩበት የ1982ቱ የሐይስኩል መጨረሻ ዓመት ላይ የተከሰተውን ህዳር የማስታውሰው ለህዳር ሚካኤል እናቴ ግቢያችንን አፅድታ የከመረችውን ጥራጊ ቆሻሻ ስታነደው አየሩን በሚያጥነው ጭስ ብቻ አይደለም:: ልቤን ለመጀመሪያ ጊዜ በማላውቀው አዲስ አይነት የስሜት ዑድ ባጠነችው ቀይ ባለረዥም ፀጉር ሴት ልጅም ጭምር እንጂ......ታሪኩ ከተሰማኝ ስሜት ዘልቆ ብዙም የተራመደ ባይሆንም ስሜቱ ራሱ ግን እንደ ጥሩ ሽቶ መአዛውን በውስጤ ተክሎ አልፉዋል:: ዛሬ ታዲያ ያን የህዳር ስሜት የምታጭር የጅጤሳ እንስትጋ አጠር ያለ ቆይታ አጋጠመኝ::

እንዳጋጣሚ ሆኖ ዛሬ አመሻሹ ላይ የኢትዮጵያው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ጅጤሳ ብቅ ብለው ነበር:: ስለዚህም በርካታ የጤና ሳይንሱ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ሰራተኞችና ተማሪዎች በመመረቂያዋ ስታዲዮም ተገኝተው ነበር:: እኔም ሄጄ ነበር:: በወቅቱ ፈንጠር ብለው ወደሁዋላ ከቆሙ ስዎች ጋር ተቀላቀልኩ:: በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ይህች ከላይ የጠቀስኩዋት የጅጤሳ እንስት  አጠገቤ መጥታ ቆመች:: በአይን ባውቃትምና ሰላም ብላትም ቀረቤታ ግን አልነበረኝም:: አሁንም ሰላም ብያት አይኔን ጳጳሱ ወዳሉበትና ለመናገሪያ ወደተዘጋጀው መድረክ አዙሬ መቆሜን ቀጠልኩ:: ወጣቷ እንስት በራሷ አነሳሽነት ወሬ ጀመረች:: ያልጠበኩት ቢሆንም ለወሬዋ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት ተሰምቶኝ ይሁን በሌላ ምክንያት እኔም ማውራት ጀመርኩ:: እሱዋ መቼም ስታወራ ድምፁዋ ዝግ ያለና በእርጋታ የሚወጣ ለስላሳና ቀጭን ነበር:: ለጆሮ ደስ የሚል...አንድ አንድ ስንባባል የደመቀ ወሬ ውስጥ ገባን:: ከድምፁዋ ማማር በላይ ጨዋታዋ ደስ አለኝ:: እንዴ??? አልኩ በልቤ:: በቃ ልክ እሱዋን! ማለቴ ከላይ ቀይ ባለረዥም ፀጉር ወጣት ሴት ያልኩዋትን...ያ በልቤ ውስጥ እንደ መልካም ሽቶ መአዛ ተከድኖ ተቀምጦ የነበር ትዝታ ተከፈተ:: ትክክለኛው ህዳር ህዳር ሸተተኝ: ማለቴ ፍቅሩ-ህዳር...ባለ መልካም መአዛው ህዳር...

አቡነ ጳውሎስ ወደ መድረክ ወጡና አስተማሩ ...ጮህ ብለው ሁሉ ተናገሩ ..የሰማቸው የለም:: የጅጤሳዋ እንስት ወጣት ከዚህ በፊት ታውቀኝ እንደነበረ ሆና ማውራቱዋን ቀጠለች...እንዲህ ነችና!


ከአቡኑ ዝግጅት በሁዋላ ታዳሚው ሲበተንና ወጣቱዋ እንስትም ጥላኝ ስትሄድ የኔ ልብ ደግሞ ተበታተነ:: ባዮኬሚስትሪ ለማጥናት ወደ ሌክቸር ሆል መሄድ ሲገባኝ ወደ ዶርሜ ሄድኩ....የተረበሸ አእምሮ ለማስታመም........

Tuesday, September 15, 2015

ሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 1985 አ.ም.  ከምሽቱ 7 ሰዓት ከ 11 ደቂቃ
የኔ ውድ በየቀኑ ከሚከሰቱትና ከሚያጋጥሙኝ በርካታ ክስተቶች አብዛኞቹን ከቁጥር ባላስገባቸውና ባላስተውላቸውም የተወሰኑት ግን ለማመን እስከሚያዳግተኝ ድረስ የሚገርሙኝ ናቸው:: እንደዚህ አይነቶቹ ክስተቶች ያጋጣሚ ብቻ እንዳልሆኑ ለልቤ ዘወትር ይሰማዋል::  ዛሬ ታዲያ እንዲህ ልል የቻልኩት ለምን ይመስልሻል? ነገሩ እንዲህ ነው....በሕቡዕ-ጠማማው መምህር  ምክንያት የማይመቸኝና የሚጎረብጠኝ የፊዚዮሎጂ ትምህርት ግማሽ ሴሚስተር ፈተና ነገ ስለሆነ ሰሞኑን እንደመስሎቼ ሁሉ ሌላውን ትምህርት ወደ ጎን በመተው እሱ ላይ ብቻ ለማተኮርና ዘለግ ያለ ንባብ ለማድረግ ሞክሬ በቅጡ አልተሳካልኝም ነበር:: እናም ስለፈተናው ባደረብኝ ስጋት የተነሳ ምነው በቀረ እያልኩ በሆዴ ከመቶ ግዜ በላይ አሰላሰልኩ:: ታዲያ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ዛሬ ጠዋት ራሱ ሕቡዕ-ጠማማው መምህር ፈተናው መቅረቱን ለሁላችንም ነገረን:: አንዳች ከትከሻዬ ላይ ዱብ ሲል በእርግጥ ተሰምቶኛል:: ፈተናው በአንድ ሳምንት ተላለፈ:: እግዚአብሔር ይመስገን.....


ሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 1985 አ.ም. 
ነገ ደግሞ እኔ የምወደውና ከልቤ የምመሰጥበት የአናቶሚ ትምህርት የቃል (oral exam) ፈተና ይጀመራል በመባሉ እገሌ ከገሌ ሳይል መላ ፒሲዋን የአናቶሚ ደብተሩና ማስታወሻው እንዲሁም ስዕሉ ላይ አድፍጧል:: የዶርሜ አባላት በሙሉ የሉም:: እንደታዘብኩት ከሆነ ሌክቸር ላይ መገኘት ካቆሙ የሰነበቱም አሉ::  ይህ እንግዲህ ለግማሽ ሴሚስተር ፈተና ማለት ነው:: ታህሳስ ውስጥ ዋናው ፈተና ሲመጣ ምን ማድረግ ያቆሙ ይሆን? ወደኔ ስመጣ ትናንት Thorax የተሰኘውን ቻፕተር በሙሉ ለማንበብ አቅጄ እንደተለመደው እቅዱን ከግብ ሳላደርስ ወደ መኝታዬ ያመራሁ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ከቀኑ አስር ሰዓት ጀምሮ በንባብ የወገምኩትን Abdomen የስተሰኘውን ክፍል እንደትናንትናው ሁሉ ሳልጨርስ ልተኛ ተቃርቢያለሁ:: ይህም እንግዲህ ለግማሽ ሴሚስተር ፈተና መሆኑን ልብ በይ:: ነገ እኔም እንደ አንዳንድ ከላይ እንደተጠቀስኩዋቸው ወገኖቼ ሁሉ ምንም አይነት ሌክቸር ላይ ላለመገኘት ለውስጤ ቃል ገብቼለታለሁ:: እንደሌሎቹ በድጋሚ የማንበብ ዕድል ባይኖረኝ እንኩዋ አንድ ዙሩን ራሱ ጨርሼ ለማንበብ እሞክራለሁ:: የአናቶሚን ፈተና ሁኔታ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ፈተናው የቃል ፈተና መሆኑና ነገ የተወሰንነው ብቻ የምንፈተን መሆኑ ነው:: ነገ ያልደረሰው ለከነገወዲያ ማለት ነው:: ከነገወዲያ ያልደረሰው ለቀጣዩ ቀን... እያለ ይቀጥላል:: ነገ ማ እንደሚፈተን ማ እንደማይፈተን ማንኛችንም አናውቅም:: ስለዚህም ሁሉም የአጠናንን ፍጥነቱን የመተረው “ነገ እፈተናለሁ!” በሚል እሳቤ ነው::

ማክሰኞ ህዳር 1 ቀን 1985 አ.ም.

በጅማ ህወቴ ውስጥ እንደዛሬ ንዴቴ ጫፍ ላይ ደርሶ ምንም ነገር ለማድረግ እስካለመቻል ደርሼ አላውቅም:: ምክንያቱ እንዲህ ነው:: ባለፈው ማክሰኞ ይጀመራል ተብሎ የነበረው የአናቶሚ የቃል ፈተና በተባለው ቀን ሳይጀመር ቀርቶና በሶስት ቀን ዝግይቶ በቀን ለአምስትና ስድስት ልጆች ብቻ የሚደርስ ከመሆኑም ባሻገር አመራረጡ በዘፈቀደ ስለነበር እኔና ሌሎች ዘጠኝ ልጆች  ሳይቀናን ቀርቶ ስንገዋለል ወደ ዛሬ ደረስን:: ያናደደኝ ግን ይህ አይደለም:: ፕሮፌሰር ስላህ ከአስራችን ውስጥ አምስቱን ከፈተነ በሁዋላ የቀረነውን አምስት ልጆች ዛሬም ሳይፈትነን ቀረ:: እንደነገሩ ጥሎን ሄደ:: ካሁን ካሁን ስሜ ይጠራል እያልኩ ጆሮየንና አይኔን ማቁልጭልጬ አልጠቀመኝም:: ሳምንቱን ሙሉ አናቶሚ ላይ ብቻ ተኝቼ መክረሜ አበሳጨኝ:: በገንኩኝ:: አረርኩኝ::  የአምስታችን የቀረነው ልጆች ተራ ከሁለት ቀን በሁዋላ ሐሙስ እንደሆነ ተነግሮናል:: እስከዚያ ስንቱን እረሳው ይሆን? የፈለገው ይሁን እንጂ ካሁን በሁዋላ ለአናቶሚ ቅንጣት ታክል ደቂቃ አላባክንም! የሚገርመውና የሚያስፈራው ሀቅ ሌሎቹ የተፈተኑት ባገኙት እፎይታ በመንተራስ ልሎች ትምህርቶችን በእርጋታ ማጥናት መቀጠላቸው ነው! ይህ በእውነቱ አድልዎ ነው:: ምን በደልን? ምን አደረግን?

............የኔ ውድ ብታምኚም ባታምኚም በዚህ ብስጭት ውስጥ ሆኜ በዶርም ቁጥር 207 መስኮት አሻግሬ ሙሉ ጨረቃን በሰማያዊው ሰማይ ላይ ተንሳፋበት አየሁዋት:: በዚህም የተነሳ በድገት ፍቅር ፍቅር አለኝ:: በምልሰት የበለጠ ልጅ እግር ወደነበርኩበት ወደ ህዳር 1982 አ.ም. ሄጄ አንድን ነገር አስታወስኩ ....የወጣት ትዝታ...መልካም ትዝታ................

Monday, September 7, 2015

ሰኞ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ 49 ደቂቃ

በዚህ ቀን ቀን ሞቃት ማታ ማታ ደግሞ ቀዝቃዛ: ደረቅና ነፋሻማ በሆነ ሰሞን የፒሲዋን ሂደት ጫን እያለ መምጣቱ በብርቱ ተሰምቶኛል:: እሰከ ምሽቱ ሰባት ሰዓት በንባብ ተግቼ እቆይ ዘንድ አልሆነም:: ይህም በውስጤ ቅሬታን ፈጥሩዋል:: በእርግጥ ከቅሬታው ይልቅ ድንጋጤዬ አይሏል ብል ይሻል ይመስለኛል...ነገ ጠዋት እግዜር ከፈቀደ በማለዳ ተነስቼ ያሉኝን ጥቂት ካልሲዎች ውሃና ሳሙና አስነካቸዋለሁ ብያለሁ:: ደህና ያሳድረኝ..

ሐሙስ ጥቅምት 12 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 7 ሰዓት ከ 19 ደቂቃ

የኔ ውድ አንድ በጣም የምቀርበውና የምወደው አሁን ባላወራውም ታሪኩ ከኔ ታሪክ ጋ የተሳሰረ ተስፋሁነኝ የሚባል ባልንጀራዬ የአንደኛ ዓመት የህክምና ትምህርቱን በደህና ውጤት አጠናቀቀ:: በዚህም በእውነቱ ከልቤ ደስ አለኝ:: ነገር ግን ደግሞ አንድ የሚያሳዝን ዜና ሰማሁ:: አንዲት ገነት የምትባል ትንሽ ትንሽ የማውቃት የተስፋሁነኝ ባች አባል የሆነች ተማሪ ውጤቷ ከበቂ በታች ነው በሚል ከጤና ሳይንሱ እንድትባረር ተወሰነባት:: ይህች ቁመተ ለግላጋና ዝምተኛ ወጣት ሴት ዛሬ ምሽት ላይ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች በተዘጋጀ የቅዱስ ሚካኤል መንፈሳዊ ፕሮግራም ላይ ተገኝታ በበዚያ  ለተሰበሰብነው እድምተኞች ሁሉ አንድ አጠር ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አነበበች:: መቼም ብርቱና ሃይማኖተኛ ነበረች:: በተወሰነባት አስከፊ ውሳኔ በልቧ እንደምታዝን ባስብም : በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆና ከታዳሚ ፊት በመቆም ይህን ማድረግ በመቻሏ ጥንካሬዋን አደነቅሁ::  በአንፃሩ ደግሞ እጅግ በመባረሯ በጣም አዘንኩ:: ከጤና ሳይንሱ አልፎ አልፎ እንደዚህ ተማሪዎች ሲባረሩ የሚሰማኝ ልዩ የሆነ የሽብር ስሜት ጎበኘኝ........