ባለፈው ለቤተሰቤ መልዕክት አሲዤ ልኪያት የነበረች አንዲት የሰፈራችን ሴት ወደ ብላቴ መመለሷን ሰምቼ ልቤ መታ:: እንደው ከቤተሰቤ ደሞ ምላሽ መልዕክት ይዛ መጥታ ይሆናል በሚል ማለት ነው:: ነገር ግን ምንም ይዛ እንዳልመጣች አፍታም ሳልቆይ ተረዳሁ:: በዚህም ምክንያት ጠዋት ትንሽ በስጨት ብዬ ነበር:: ከሰዓት በሁዋላ ግን ነገር ተለወጠ:: ማሰልጠኛው ውስጥ አለፍ አለፍ ብለው የቆሙ ግንዶች ላይ ከተንጠለጠሉ የድምፅ ማጉያዎች ውስጥ ስሜና የመጣሁበት ጅማ ጤና ሳይንስ ተጠርቶ "እዚህ ስቱዲዮ ድረስ በአስቸኩዋይ ትፈለጋለህ" የሚል ንግግር ወጣ:: ምንም ያጠፋሁት ጥፋት ወይም የሰራሁት የተለየ ነገር ባለመኖሩ ባልደነግጥም ለምን ይሆናል የሚል ግምት ግን በጭራሽ አልነበረኝም:: በአንድ የመብራት ኃይል ሹፌር በኩል ከቤተሰብ የተላከ ሃምሳ ብር እንዲሁም ሁለት ሁለት ጥንድ ካኒተራዎች: ሙታንቲዎች ና ካልሲዎች ተሰጡኝ:: የመብራት ኃይሉ ሹፌር እቃውና ገንዘቡን ስረከብ እዚያው ቢሮ ውስጥ ነበሩ:: በጣም አድርጌ አመሰገንኩዋቸው::
በዚሁ ቀን አስራአንድ ሰዓት ላይ በጀርመን ድምፅ 240 ኢትዮጵያውያን ፕሮፌሰሮች ለ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለ ማርያም የስልጣን ልቀቁ ና የሽግግር መንግስት የመመስረት ጥያቄ ማቅረባቸው ሲነገር ሰማሁ:: በቅርቡ ምን እንደሚፈጠር ማን ያውቃል? በዚሁ ሰዓት አዲስ አበባ ውስጥ ኑሮ ተወድዷል እየተባለም ይወራል...
ዛሬ ደግሞ በማሰልጠኛው ውስጥ ያሉ ተማሪዎች የመኝታ ክፍል ምደባቸው በየመጡበት ኮሌጅ እንዲሆን በመወሰኑ የከሰአቱን ጊዜ ያሳለፍነው በመኝታ ቤት ልውውጥ ነው:: ላለፉት ሳምንታት የተለህያየ ኮሌጅ ተማሪዎች ተቀላቅለን ነበር የኖርነው:: ለውጡ በጣምም ባይሆን ደስ ብሎኛል:: እኔ: ሉሉ: አባይ: ግሩም: መንጌ: አብይ: ማስረሻ: ና ሚሊዮን አንድ አካባቢ ሆንን:: በተመሣሳይ ቀን ብላቴ የሚገኙ 1000 የሚሆኑ የኮሌጅ ተማሪ ያልሆኑ እግረኛ ሰልጣኝ ወታደሮች ወደ ፍቼ ሰሜን ሸዋ ዘመቱ:: እግዜሩ ይከተላቸው .......
ሚያዚያ ስድስት አስራ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሶስት አ.ም.
ዛሬ ለብላቴ አየር ወለዶች ዛሬ በጣም አዘንኩኝ:: ቀኑ እሁድ እንደመሆኑ መጠን የሙዚቃ ዝግጅት ተደርጎ ነበር እኛን የተማሩ ሰልጣኞችን ለማዝናናት:: ሞዛቂው ቡድን የፖሊስ ባንድ ነበር:: እስካሁን ከመጡት ባንዶች ሁሉ በጥራት ዝቅ ያለ ሆኖ ተሰምቶኛል:: ኦርጋኑ ድምፅ ያልነበረው ከመሆኑ ባሻገር ማይክሮፎኖቹና ድምፅ ማጉያዎቹ የተበላሹ ናቸው:: በዚያ ላይ የተዘፈኑት ዘፈኖች ዜማቸው የማይስብ ና በጥሩምባዎቹና በ ጊታሮቹ ድምፅ የተዋጠ ስለነበር እኔ በግሌ ውስጣዊ ቱግታ ተሰምቶኝ ነበር:: በአንፃሩ ደግሞ ሌሎች ተማሪዎች ካለፉት ጊዜያት እንደውም በበለጠ ሁኔታ መድረክ ላይ እየወጡ የተወራጩበትና ግርግር ያበዙበት እለት ነው ማለት ይቻላል:: የደስታ ይሁን ወይም ተስፋ መቁረጥ ያመጣው ግድ የለሽነት አይታወቅም:: ግዴለሽነቱ ግን ያስኬዳል:: እንዴት እንደዘህ አይነት ልዩነት በኔና በሌሎች ሰብአዉያን መሃል ሊፈጠር እንደቻለ አይገባኝም:: አረጋሀኝ ወራሽ እንዳጋጠመው ባይሆንም ከፖሊስ ባንድ ጋ የመጣችውን ድምፃዊ ሂሩት በቀለን እነዚሁ መድረክ ላይ የሚወራጩ ተማሪዎች አላዘፍን ብለዋት ነበር:: እኔ ተመልካች ተማሪ የተገጠገጠበት ኮረብታ መሃል ለመሃል መለትም መኮነንኖችና የክብር እንግዶች ከተቀመጡበት ቦታ በስተጀርባ ተቀምጫለሁ:: ከኔ ጀርባ ደግሞ እልፍ ተማሪዎች እንዲሁ ተቀምጠዋል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ድንገት ያልተጠበቀ ግርግር ተከሰተ:: ወደታች ወደ መድረኩ ስመለከት አንድ ተማሪ በወቅቱ ያቀነቅን የነበረውን ድምፃዊ ካልሸለምኩኝ ወይም ካላቀፍኩኝ ብሎ ነው መሰለኝ ከአንድ አየር ወለድ ጋር ይከራከራል:: በዚህ ሁኔታ እያሉ አየር ወለዱ የክብር ኮፍያውን አውልቆ ተማሪውን ሆዶ ላይ በቦክስ ሲመታው ተመለከትኩ:: ኮረብታው ላይ የተገጠገጠው አስር ሺ የሚሆን ተማሪም እንደሚያየው ግልፅ ነበር:: አየር ወለዱ በቦክስ አላቆመም:: በቴስታም ደገመው:: ምናልባት ተማሪው አየርወለዱን ሰድቦት ይሆናል ብዬ አሰብኩ:: የኔ ማሰብ ዋጋ አልነበረውም:: ከዚህ ቅፅበት በሁዋላ የሆነው ነገር እጅግ የሚያስፈራ ነበር:: ተማልካች ተማሪ በሙሉ ማለት ይቻላል በየተቀመጠበት ያገኘውን ኮረትም ሆን ዱባ ዱባ የሚያካክል ድንጋይ እያነሳ ወደ መድረኩ መወርወር ያዘ:: ወደ ሰማይ አቅጣጫ ለቅፅበት ቀና ስል አየሩ ላይ ከወድያ ና ከወዲህ የሚወነጨፉትን ድንጋዮች አይቼ ተሸበርኩ:: አንዳንዶቹ ድንጋዮች እርስ በርሳቸው ይጋጩ ነበር:: መድረኩ ባጭር ግዜ ውስጥ ሰው አልባ ሆነ:: ሁሉም በየፊናው ሮጧል: ሂሩት በቀለን ጨምሮ:: የሙዚቃ መሳሪያዎቹ ብቻቸውን ቀሩ:: ድንጋዮች መወርወራቸውን እንደቀጠሉ የሽጉጥና የክላሽ ተኩስ ድምፅ ደሞ መሰማት ጀመረ:: ደግነቱ ሁኔታውን ለማብረድ መኮንኖቹ ወደላይ የተኮሱዋቸው ነበሩ:: ውርወራው በተኩሱ ሳይሆን ብሎ ብሎ በራሱ ጊዜ እንደዝናብ ቆመ:: መድረኩ አካባቢ የተወሰነ ሰው ክፉኛ ተጎድቶ ነበር መሰለኝ:: ውርወራው ሲቆም ድንጋይ ሲወረውሩ የነበሩት ሰልጣኝ ተማሪዎች ዘፈኑን መመልከታቸውን ትተው በማኩረፍ አይነት ለመሄድ መንቀሳቀስ ጀመሩ:: ሂሩት በቀለ ከተደበቀችበት ወጥታ በድምፅ ማጉያ "እባካችሁ ተመለሱና እንቀጥል" ስትል መማፀኑዋን ልብ ብያለሁ....