Sunday, August 30, 2015

እሁድ ጥቅምት 1 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 2 ሰዓት ተኩል 
ቀንም ሆነ ማታም ሆነ:: ፒሲዋን ሁለተኛ ሴሚስተር ከተጀመረ ልክ 2 ሳምንት:: ከመጀመሪያው ሳምንት ይልቅ በሁለተኛው ሳምንት በጥናትና በንባብ በርትቼ ነበር እላለሁ:: እርግጥ ነው አንዳንዴ ዋይትሃውስ ፎቅ ስር ባለው የተማሪዎች ቴሌቪዥን መመልከቻ አዳራሽ በኩል ሳልፍ በወቅቱ ከቴሌቪዥኑ በሚተላለፈው ዝግጅት ተስቤና ተሰናክዬ ወደ አዳራሹም ገብቼ ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዓት በመቀመጥ ከጥናቴ እዘናጋ ይሆናል:: ቢሆንም.....ቢሆንም.....የመኝታ ሰዓቴ እስካሁን ድረስ ከምሽቱ 7 ሰዓት ዝቅ አላለም:: ሳነብም የማተኮሬና ሃሳቤን የመሰብሰቤ ሁኔታ እስካሁን መልካም ነው::

በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ በሁሉም ደረጃ ያሉ የሁክምና ተማሪዎች በሙሉ በፍጥነት ወዲያና ወዲህ ሲሯሯጡ ማየት የየዕለት ክስተት ነው:: በቃ የሂወት ትንቅንቅ አካል ኖሮት ይታየኛል:: ታዲያ አይቼ አይቼ .....አይቼ ይገርመኝና የህክምና ተማሪ በመሆኔ እደሰታለሁ:: እንደውጭ ሰው ሆኜ ሳየው ውስጡ መልሶ መግባት ይናፍቀኛል:: ግን ደግሞ አለሁበት.....አይደል እንዴ?

ባለፈው ስለአለመጨነቄ ስናገር ነበር አይደል? ዛሬ ታዲያ ከኔ እጥፍ በጥፍ የማትጨነቅ የኛው ባች አባል መኖሯን ላስታውስሽ ወደደኩ:: ትዕግስት! ከኔጋ እንደማንኛውም ተማሪ እንቀራረባለን:: አንዳንድ ሁኔታዋ ያስገርመኛል:: ለምሳሌ በቁጥር በርከት ያሉ ሌክቸሮች ላይ አላየሁዋትም:: አንዳንዴ ደብተሬን ትዋሰኝና ገልብጣ ትመልስልኛለች:: ያንደኛውን ሴሚስተር ያሳለፈችው እንደዚህ ነው:: በጣም በጣም ዘና ብላ:: ታዲያ የባዮስታትስቲክስ አንደኛ ሴሚስተር ፈተና ውጤቷ B መሆኑ ገርሞኛል:: ማለቴ ትንቅንቅ ትይንት ውስጥ ላልታየ ተማሪ በጣም ጥሩ ውጤት ነው ...በተለይ ባዮስታትስቲክስ! ትዕግስት በዚህ ሴሚስተርም በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥላለች:: ሰሞኑን እንደውም አላየሁዋትም:: ተስፋ ቆርጣ አይመስለኝም::  አንድም ቀን ስታማርር ሰምቻት አላውቅም:: እንዲያውም የአንደኛ ሴሚስተር ፈተናዎቻችንን ያጠናቀቅን ለት እኔ በምሬት ስናገር ሰምታኝ “ ተው እንጂ አንድ ሴሚስተር መጨረሻ ላይ መድረስ ራሱ ቀላል አይደለም” ብላኝ ነበር........

ቅዳሜ ጥቅምት 7 1985 አ.ም.  ከምሽቱ 7 ሰዓት 10 ደቂቃ
የአናቶሚ ላቦራቶሪ ፕሪክልኒካል ተብሎ የሚጠራው ህንፃ ውስጥ በግራ በኩል ከዋናው ወለል በተወሰኑ ደረጃዎች ዝቅ ብሎ ይገኛል:: በፈለግነው ሰዓት እንድንገባ ተፈቅዶልናል:: እኔ አናቶሚ ላቦራቶሪ ውስጥ ቁጭ ብዬ ማጥናት ደስ ይለኛል:: ሰሞኑን ምሽት ላይ ከዚያ አልጠፋም:: ቸርነትና እመቤትም አብረውኝ ያመሻሉ:: ታዲያ ሁልጊዜ ቀን ቀን የምንማርባቸው አራት ሬሶች (cadavers) በነጭ ጨርቅ ተሸፍነውና በፀጥታ ተጋድመው ይታያሉ:: ፈፅሞ አይረብሹንም:: በሰፊውና በረዥሙ አናቶሚ ላቦራቶሪ ውስጥ አንደኛው ማዕዘን ጋር ካለው ጠረጴዛ ላይ ከቸርነትና ከእመቤት ጋር ሆነን የምናሳልፈው የጥናት ግዜ ባልፅፈውም ወደፊት የማስታውሰው ይመስለኛል.....


ዛሬ ታዲያ በሚገርም ሁኔታ በትዕግስት አናቶሚ ትምህርት ያለማቁዋረጥ ለሶስት ሰዓት አነበብኩ:: ሀቅ ልናገር ከተባለ ይህ በኔ የጥናት ሂወት ውስጥ ሁልጌዜ አይከሰትም:: ተቀምጦ ለረዥም ሰዓት ማንበብ? እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ በጣም በጣም አንዳንዴ (rare) ከመሆኑ የተነሳ ከዚህ በፊት ለሶስት ሰዓት ያለማቁዋረጥ ያነበብኩበትን ግዜ አስታውሰዋለሁ:: አንድ ግዜ ብቻ ነው የሆነው:: ባለፈው ዓመት አንድ ቀን ሳይኮሎጂ ትምህርት ሳጠና..በቃ! በተማሪነት ሄወቴ ስለራሴ በሂደት ከተገነዝብኩዋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ለንባብ ትዕግስት እንደሚጎድለኝ ነው:: ስለዚህ በየሃያና ሰላሳ ደቂቃው ለማንበብ የተቀመጥኩበትን ቦታ ለቅቄ ገለል ማለት ያስፈልገኛል:: ከአናቶሚ ላቦራቶሪው ጥናት እረፍት የማደርገው ወጣ ብዬ ከፕሪክሊኒካል ህንፃ ፊት ለፊት ካሉት ዛፎች ስር ራመድ ራመድ በማለት ወይም ቆሜ በዛፎቹ መካከል ጨረቃን ፍለጋ ወደሰማይ በመመልከትና ሲያጋጥም ደግሞ የጅማን ደረቅ የምሽት አየር በመማግ: ይሆናል.......

Tuesday, August 25, 2015

ጨረቃ
ወኔዬ አልቆ ተሙዋጦ 
መንፈሴም ደክሞ ተስፋ ቆርጦ
ብስጭት ገብቶኝ ሞትን ስሻ
መሄጃ አጥቼ መድረሻ
ወደበላዬ ስመለከት
ሰማይ ከዋክብት ወዳሉበት
አየሁ ጨረቃ መሃል ሆና 
ምድርን ስታደምቅ በብርሃኗ
እነሆም ተስፋዬ አንሰራራ
ልቤ ተነካ ባምላክ ስራ 
ብቻዬን እዳልሆንኩ ተገነዘብኩ
ነገን እያሰብኩ አሸለብኩ
(By Samson Haile)

ማክሰኞ መስከረም 19 ቀን 1985 አ.ም.  ከምሽቱ 6 ሰኣት ከ 13 ደቂቃ

ዛሬ ጠዋት ፊዚዮሎጂ ሌክቸር ከመውሰዳችን ቀደም ብሎ ፕሮፈሰር ማሂን ከግንዛቤ በማስገባት አንደሚጨንቀኝ አስቤ ነበር:: ግን ሳልጨነቅ ቀረሁና ያ ደግሞ አስጨነቀኝ:: እንዴት ሳይጨንቀኝ ቀረ? 
ለነገሩ ለማን ብዬ ነው የምጨነቀው? አንድ አስተማሪ ደበረኝና ምን ይጠበስ? 

በነገራችን ላይ ፒሲ ዋን ሁለተኛ ሴሚስተር በደንብ ተጀመረ:: ዛሬ አስከ ምሽቱ ሰባት ሰአት ለማንበብ እቅድ የነበረኝ ቢሆንም አሁን ደከመኝ: 47 ደቂቃ ሲቀር ማለት ነው.....

ውድ ማስታወሻዬ እኔ ካሁን ወዲያ ላንቺ የምነግርሽ የጨረቃን ድምቀት: የጸሃይን ጥልቀት: የዛፎችን ውዝዋዜና የነፋስን ሽውታ ነው እንጂ በቃ ጭንቀት አላወራም:: ኦ ጭንቀት ልኩ እንዴ? አላወራም ብዬ ስለሱ....

የግቢው አትክልተኛ አበቦቹን በደንብ እያሳመራቸው መሆኑን ተመለከትኩና  አንድ ላንቺ ማለት ያለብኝ ነገር ትዝ አለኝ:: "ጥሩ ቀለማትን ከማየት የበለጠ ምን ነገር አለ?" እላለሁ አንዳንዴ:: በእርግጥ በሙዚቃና በስነጽሁፍ ብደሰትም የሰዎች ስራ ከሆኑት ከነዚህ ይልቅ በተፈጥሮ ህብረ ቀለማት ና የወፎች ዝማሬ ይበልጥ የመደሰት ባኅሪ ያለኝ ይመስለኛል......

ሮብ መስከረም 20 ቀን 1985 አ.ም.
ዛሬ ማታ ከቤተመሃፍት ንባብ ለምስት ደቂቃ እረፍት ለማድረግ ወጥቼ ሳለ የኢንተርንሺፕ ሃኪም የሆነው አብርሃም ሻይ ገዛልኝና ከዚያ በሁዋላ ደስ እያለኝ ጠናሁ:: ቤተመጽሃፍቱ ሲዘጋ እንደተለመደው ወደ ሌክቸር ሆል ሄድኩ:: ወደዚያ እየሄድኩ ወደ ሰማይ ቀና ብዬ አየሁ:: ግማሽ ጨረቃ ትታያለች:: ልቤን በእርግጥ ደስ እንዳለው ይታወቀኝ ነበር:: ከዚህ በሁዋላ በሌክቸር ሆል ውስጥ በንባብ እስከ ምሽቱ 6 ሰኣት ከ40 ደቂቃ ቆይቼ ለመተኛት ወደ ዶርም ኣቀናሁ:: በመንገዴ ላይ እመቤት አብራኝ ነበረች:: ዝናብ እያካፋ የነበር ቢሆንም ርምጃችን የወትሮው ነበር.....

ሐሙስ መስከረም 28 ቀን1985 አ.ም. ከምሽቱ 7ሰኣት ከ 13 ደቂቃ
ዛሬ እንኩዋን የማወራው ነገር የለኝም:: ግን ጨረቃ በሙሉ ድምቀት በሰማያዊ ሰማይ ላይ እየታየች መሆኑን ሳልገልጽ መተኛት ከበደኝ:: ዶርም ቁጥር 207 ውስጥ አልጋዬ ላይ ነኝ:: የምጽፈው ማጣቴን ላልተኙ ጉዋደኞቼ እየነገርኩዋቸው ነው:: መንጌ ልጋው ውስጥ የገባ ቢሆንም አልተኛም:: የሆነ ነገር ይዞ ያነባል:: አባይም እንደዚያው:: አብይ ትንሹዋ ጠረጴዛ አጠገብ ሆኖ እያጠና ነው:: አሌክሱ አምሳሉ ሚሊዮንና ሃይሉ እንዲሁም ቤተማርያም እርግጡን ለመናገር ባልችልም እንቅልፍ ውስጥ ይመስሉኛል:: አባይነህ፥ አመንቴ ና አዳሙ የሉም:: ገና ኣልገቡም:: ውድ ማስታወሻዬ ደህና እደሪ:: ጉዋደኞቼም እንዲህ ይሉሻል.....

ባይ "እግዚኣብሄር ይመስገን"
መንጌ " God should be praised"
አብይ "ኑሮ መሮኛል"

Friday, August 14, 2015

እሁድ መስከረም 17 ቀን 1985 አ.ም.

ያባይ ልጆች መጡ እንደገና!
ግብፆቹ መምህራኞቻችን እረፍታቸውን ጨርሰው ጅማ እንደደረሱ ወሬ ሰማሁ:: “እሰይ!” ማለት ይገባኝ እንደነበር ባውቅም በነሲብ የተሰማኝ ስሜት ግን ወደ ግራ የወገነ የልብ መደናገጥ ነበር-ሀቅ ልናገር ከተባለ:: ወሬውን እንደ መልካም ወይስ እንደ መጥፎ ዜና መቁጠር እንዳለብኝ ማወቅ ሊሳኝ ዳዳኝ:: ማለቴ እኔም ሆንኩ ጉዋደኞቼ ከእረፍት መልስ በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ እየቦዘንን ስለነበር ግብፆቹ መጥተው ትምህርት መጀመሩ ደስ የሚል ቢሆንም የፒሲዋንን የጥናት ኃላፊነትና የጉሮሮ ለጉሮሮ ትንቅንቅ ግን እንዲሁ ተቻኩዬና እጆቼን ዘርግቼ አቅፈው ዘንድ የሚፈቅድ ልብ አልነበረኝም:: እናም በዚህ የአደይ አበባ ፍካት ጡዘት ላይ በደረሰበት የወርሃ መስከረም አጋማሽ ከባልንጀሮቼ ጋር በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥም ሆነ ከግቢው ውጭ መቦዘኑና መፈንጨቱ እንዲያው ትንሽ ቢቀጥል ደስ ባለኝ.....በአንደኛው ሴሚስተር ከነበረኝ ልምድ በመነሳት የፒዋንን እንደገና መጀመር ሳስበው እንደዚህ ካለ ፀደይ: እንዲህ ካለ በአበቦች ከታጀበ የበጋ መጀመሪያ: እንዲህ ካለ ነፃ ቡረቃ ተነጥቄ የዚህ ተቃራኒ ወደ ሆነ የኑሮ ጥቁር የምወሰድ መሰለኝ::: በቃ የክረምቱ ግዜ አበቃ......በቃ የፀደዩ ወራት አበቃ......ወርቅ ቢጫማውን የጅማ ፀሐይ ጥልቀት እንደልቤ ለመመልከት ዕድል ይኖረኝ ይሆን? ሙሉ ቀይ ጨረቃን በዛፍ ቅርንጫፎች መካከል ለማየትስ? የጅማን ደረቅ ምሽ ንፋስ ሽዉታና በሱም ምክንያት የሚወዛውዙትን ዛፎች ድምፅስ እሰማ ይሆን? በቃ ከዚህ በሁዋላ እኮ ታሰርኩ! ጎበዝ! በግብፆች ቁጥጥር ስር ልገባ ነው:: በተለይም በማይመቸኝ በፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰር ማሂ  ስር! ያባይ ልጅ ያለህ! 
የኔ ነገር ለካ እነሱም ካባይ ናቸው.....

የኔ ውድ የሆንሽ ማስታወሻዬ.... ይልቅ አሁን ይህን አይነት ወሬዬን ልተውና ትናንት እኔና ጉዋደኞቼ የመስቀል ዋዜማን እንዴት እንዳከበርን ለተርክልሽ......


እኔ ጉዋደኞቼና መስቀል

በነገራችን ላይ በዶርም ቁጥር 207 ውስጥ ያለነው ልጆች 10 ስንሆን ክፍሉ ግን ለ12 ልጆች ታስቦ የተሰራ ስለነበር 12 ሎከሮች አሉት:: ከሁለቱ ትርፍ ሎከሮች ውስጥ አንደኛው ዘወትር ክፍት የነበረ ሲሆን አንደኛው ግን ለብዙ ጊዜ የተቆለፈ ነበር:: እኔና ጉዋደኞቼ ታዲያ “እስቲ ውስጡ ምን ይኖር ይሆን?” በሚል ጉጉት ትናንትና ከፈትነው:: በርከት ያሉ ልብሶችና ጥቂት አንሶሎች ደብተሮችና ሌሎቹም ቁሳቁሶች የሎከሩን መከፈት ተከትለው ተንከባለሉ ! የሁላችንም አይንና ልብ ያረፈው አንሶላውና ልብሶቹ ላይ ነበር:: ጅማ ገበያ ላይ ያላቸውን ዋጋ ጠንቅቀን እናውቅ ነበርና:: በዚያ ላይ የመስቀል ዋዜማ ነው:: ወይ የእግዚአብሔር ነገር! የማን ይሆን ልብሱ? የሁሉም ጥያቄ ነበር:: እኛ እዚህ ዶርም ከመግባታችን በፊት ይኖሩበት የነበሩት ያለፈው ዓመት ኢንተርንሺፕ ሀኪሞች እንደነበሩ በሰከነ ውይይት ደረስንበት:: አሁን ተመርቀው በግቢ ውስጥ የሉም:: ወደ ሥራ ዓለም በየአቅጣጫው ተበታትነዋል:: አሀ! የዚህ ልብስ ጌታ ባሁኑ ሰዓት ሃኪም ሲሆን በወር 835 ብር እየበላ ይሆናላ ይሄኔ! በዚህ ነፃ እሳቤ በመታገዝ በቀጣዮቹ ሰዓታት ውስጥ አንሶላውና ልብሶቹ ወደ ገንዘብ ተቀየሩ:: ደንገዝገዝ ሲል የጅማን ከተማ መሃል ለመሃል ሰንጥቀን ጠለቅንባት.....እኔና ጉዋደኞቼ:: በታክሲ  ጩኸት: በሙዚቃ ቤት ሜጋ ስፒከር ድምፅ እንዲሁም ባመትባል ዋዜማ የከተሜ ግርግር ታጅበን ከፈረንጅ አራዳ መልስ : በየጆካ ሆቴል ጀምረን: ካንዱ ቡና ቤት ወዳንዱ እየተሸጋግርን እጅግ በጣም የምንወደውን ቀይ ቪኖ ስንጠጣ ስንደንስና ስንወራጭ አስከ እኩለ ሌሊት በስቲያ አመሸን.... ያ ያምና ኢንተርን የዛሬ ዶክተር እግዜር ይስጠው:: እንጀራ ይውጣለት:: 

የምሽቱ አየር ደረቅና እጅግ በሚመች መልኩ ቀዝቀዝ ያለ ስለነበር ካንዱ ቡና ቤት ሞቅ ብሎን ወጥተን ወደሚቀጥለው እስክንደርስ ሞቅታው በረድ ይልልን ነበር....

Sunday, August 9, 2015

ዛሬ
አኔ የምፅፈውን የምታነብ ሁሉ:: ባለፈው ሚያዚያ አንድ ከልቤ ማህደር የተሰኘ ግጥም ካሰፈርኩ በሁዋላ በመጥፋቴ የቅርታ ልጠይቅ ይገባልና እነሆ:: ነገር ግን የጠፋሁት በከፊል በምክንያት መሆኑን ታውቅልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ:: ከሃያ ዓመት በፊት በህይወቴ ውስጥ የተከናወንን ነገር ለመፃፍ ስፍጨረጨር አሁን በዚህ ዘመን የሚከናወነው ነገር አንዳንዴ ወጥሮ ይይዘኛል:: ባለፉት አራት ወራት የእንጀራዬ ምንጭ የሆነውን የቀድሞ ስራዬን በመተው አዲስ ሥራ በአዲስ ቦታ በመጀመሬ ይህን ለኔም ሆነ ለቤተስቤ በመልካም ሁኔታ ለማስኬድ ቀልቤ ሁሉ እሱ ላይ አተኩሮ ከረመ:: የቀድሞ መኖሪያችንን ለቀን አሁን አዲስ ሰፈርና ቤት ውስጥ ነው ያለነው:: ቤተሰብ አፍርቶ ካንድ ቤት ወደ አንድ ቤት መዘዋወር እንዴት እንደሆነ የደረሰበት ያውቀዋልና ከዚህ በላይ ማለት አልፈልግም::

አሁን እንግዲህ አዲሱ ሥራና ኑሮ ተለምዶ በተወሰነ መልኩ መረጋጋት ላይ በመድረሴ ጣቶቼን ወደ ላፕ-ቶፕ ኪቦርድ ቀሰርኩ.....

ባለፈው ማስተዋሻዬን ያቆሙኩት የሁለተኛ ዓመት አንደኛ ሴሚስተር የህክምና ትምህርት አልቆ በነሐሴ ወር መጀመርያ  ለእረፍት ወደ ቤተሰብ ጋ እንደነጎድኩ በመግለፅ ነበር:: እነሆ ዕረፍቱ አልቆ: የዘመን መለወጫም ተከብሮ: በበነጋው ወደ ጅጤሳ ከመመለሴ የለጠቀውን ማስፈር እጀምራለሁ:: መልካም ንባብ;::

ዕለተ ሐሙስ መስከረም 7 1985 አ.ም.
የሰሞኑ የጅማ አየር ሞቃትና ደረቅ ነው:: የቀኑ ሙቀት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ያደክማል:: ምሽቶቹ በድፍን ጨለማ የተዋጡ ናቸው:: ከቤተሰቤ ጋር የዘመን መለወጫን ባከበርኩ በሁለተኛው ቀን መስከረም 3 ቀን ጅማ ከተማ ገባሁ:: የህክምና ትምህርቴን ለመቀጠል:: ዛሬ እንግዴህ አራተኛ ቀኔ ነው:: በነዚህ ቀናት ውስጥ የአንደኛ ሴሚስተር ፈተና ዉጤቶቻችን በደፓርትመንቱ ሃላፊ አማካይነት ተነግረውናል:: በኔ በኩል ውጤቶቹ ምንም እንኩዋን በጣም ከፍተኛ ባይሆኑም በልቤ ሳስብ ከነበረው እጅግ በጣም የበለጡ ሆነው ስላገኘሁዋቸው ደስ ብሎኛል:: ተስፋዬ በጣም ጨምሯል:: ለካስ በጣምም በትምህርቴ ደካማ አይደለሁም? የሚል ውስጣዊ ስሜት እየተሰማኝ ነው::

ቅዳሜ መስከረም 9 1985 አ.ም. ከምሽቱ 6 ሰዓት ከ 15 ደቂቃ
የዛሬው ቀን ፀሐያማ ሆኖ የዋለ ቢሆንም ወደ አመሻሹ ላይ ዝናብ ጥሎ ነበር:: ዋይት ሃውስ በሚገኘው ዶርም 207 መኝታዬ ላይ ነኝ:: ወደ ስምንት የሚሆኑ የዶርሙ አባላት ድብን ባለ እንቅልፍ ውስጥ ሲሆኑ አዳሙ ብቻ መፅሐፍ ቅዱስ እያነበበ አልጋው ላይ ቁጭ ብሉዋል::  እኔም ይህን ፅፌ ስጨርስ የአዳሙን አርአያ በመከተል መፅሐፍ ቅዱስ አንብቤ ለመተኛት አስባለሁ:: ሰሞኑን ኃይለኛ ጉንፋን ካንዱ ወዳንዱ እየተላለፈ ጉዋደኞቼን ሁሉ ሲያስተኛቸው ያልታመምኩት እኔ ብቻ ነኝ ማለት እችላለሁ:: ለታመሙት ጉዋደኞቼ ከጤና ሳይንሱ የተማሪዎች ምግብ ቤት የበሽተኛ ምግብ በማመላለስ ላይ እገኛለሁ:: 
በነገራችን ላይ ባለፈው ነሐሴ መጀመሪያ እንደኛ እንደተማሪዎቹ ሁሉ ግብፃውያኑ መምህራኖቻችንም ለእረፍት ወደ ሀገራቸው ሄደው ነበር:: እስከዛሬ አልተመለሱም:: በዚህም የተነሳ ትምህርት ገና አልተጀመረም:: በግሌ በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ ና ከግቢ ውጭ በእግር ከመዞር በስተቀር ምንም አይነት ትምህርታዊ እንቅስቃሴ አላደረኩም:: 

ማክሰኞ መስከረም 12 1985 አ.ም. ከምሽቱ 5 ሰዓት
የዛሬውም ምሽት ጨረቃ የለውም:: ከአዲስ አበባ ከመጣሁ ላይኔ የናፈቀው ነገር ቢኖር የጅማ ምሽት ጨረቃ ድምቀት ነው:: ምንም እንኩዋን ለጉዋደኞቼ ውሸት ቢመስላቸውም..ምንም እንኩዋን የሶስተኛው ዓለም ምስኪን ብሆንም..ይህ ስሜቴ ግን አተጨባጭ ነው::
ግብፆች ገና አልመጡም:: ከአንድ ሰው በስተቀር:: ይህ የሂስቶሎጅ ፕሮፌሰር ከዚህ በፊት አይተነው የማናውቅ አዲስ ሰው ነው:: ዛሬ ቀን ሲያስተምረን የመጀመሪያመሪያ ስሙ መሐመድ መሆኑን ነግሮናል:: 

በነገራችን ላይ ጅማ ከመጣሁ ብዙም አልተከፋሁም:: እንዲያውም በሚገርም ሁኔታ በቀን ውስጥ በንቃት ከሚኖረኝ ሰዓት ውስጥ አብዛኛንውን የማሳልፈው ሳልከፋ ነው::