Monday, February 23, 2015

ግንቦት 5 1984 አ.ም. ረቡዕ
ከምሽቱ 6 ሰዓት ከ51 ደቂቃ ነው:: የዛሬውን ጥናት አጠናቅቄ ወደ ዶርሜ ልክ አሁን መመለሴ ነው::  እየተረሱ  ከሚያስቸግሩኝ ትምህርቶች ዋነኛ የሆነውን ግን ደግሞ የምወደውን አናቶሚ ትምህርት ሳጠና ነበር የቆየሁት:: አንዳንድ ቆራጥ የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼን በትጋት ማጥናት በመቀጠላቸው እዚያው ማጥኛው ቦታ ጥያቸው ነው የመጣሁት:: ከውጭ የነጎድጉዋድ ድምፅ ይሰማኛል:: ወራቱ በተለምዶ ደረቅ የሚባለው ግንቦት ቢሆንም ሰሞኑን ግን በጅማ ወፈር ያሉ የዝናም ጠብታዎች እየተስተዋሉ ነው.......

ግንቦት 7 1984 አ.ም.  አርብ: ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ 37 ደቂቃ
ዛሬ ደግሞ ምሽቱ ነፋሻ ደረቅና በሙሉ ጨረቃ የተዋበ ነው:: ጨረቃን በረዣዥሞቹ የጅጤሳ ፅድና ዝግባ ዛፎች መካከል ባሉት ቀዳዳዎች አሻግሬ ስመለከታት እጅግ ደምቃና አድማሱ ላይ ለኔ ተብላ እንደተቀመጠች  የመንፈስ ምግብ ሆና ትታየኛለች::  ተስፋን ትለግሰኛለች:: በእውነት ለመናገር ነገን እንዳስብ ታደርገኛለች:: ነገን ሳስብም ጎኔን ባልጋ ራሴንም በመከዳ ላይ አሳርፌ አሸልባለሁ..........


በዚህ የትምህርት ሳምንቱ መጠናቀቂያ በሆነ እለት ምሽት ላይ የተሰማኝ አንድ ትልቅ ነገር ቢኖር ፒሲዋንን ገና በሚገባ ያልተገነዘብኩት እንዲሁም ውሉን ያልጨበጥኩት መሆኑን ነው:: መደረግ ያለባቸው ነገሮች እንዲሁም መነበብ ያለባቸው እውቀቶች በፍጥነት ተከማቹ:: ፋታ ጠፋ:: በድንገት ኑሮአችን እጅግ አጭር በሆነ የእንቅልፍ ሰዓት ለሁለት የተገመሰ የሩጫ ዑደት ሆነ:: በዙሪያዬ የማየው ሁሉ እሳት የተነሳ ይመስስል ወደተለያየ አቅጣጫ ይሮጣል:: በዚህ ሁሉ መሃል ግን ማጥናቴን ቀጥያለሁ:: ያነበብኩትን መርሳቴም አብሮኝ:: በየቀኑ ትከሻዬ አካባቢ ውጥረት ይሰማኛል:: የጭንቀት ምልክት ይሆን? በሳምንቱ ውስጥ ባንዱ ወይም በሁለቱ ቀን ምክንያቱ የማይታወቅ የማጥናት አለመፈለግ ስሜት ውስጥ እገባለሁ:: ቢሆንም እንደምንም ወደ ማንበብ መፈለግ አመጣውና በጥናቴ እቀጥላለሁ:: ሌላ አማራጭ የለኝም::ምክንያቱም ከላይ እንዳልኩት በዙሪያዬ የማየው የሚሮጥና የሚተጋ ብቻ ነው:: ለአፍታ ቀጥ ካልኩ ወደሁዋላ መቅረቴና መቀደሜ ነው! ግን ማነው የሚቀድመኝ? በምንስ ነው የቀደመው? በእውነቱ መልሱን አላውቀውም:: በአንድ ዓመት የሚበልጡን የ ፒሲቱ (PC-2) ተማሪዎች ፕሲዋንን አካብደውና እንድንሸማቀቅ አርገው  ስለነገሩን ይሆን እንዲህ የማስበው? በበኩሌ ያው ከሩጫው: ከመፃፉ ብዛትና ከመረሳቱ በተቀር ምንም የሚያስደንቅ ነገር እስካሁን አላየሁም....

Tuesday, February 10, 2015

ግንቦት 1 1984 አ.ም. ቅዳሜ
ሳይታወቅ የግንቦት ወር ከተፍ አለ:: በትናንትናው እለት የተጠናቀቀው ያለፈው የትምህርት  ሳምንት በከፍተኛ ሁኔታ የተሯሯጥኩበት ሳምንት ነበር:: እኔ ብቻ ሳልሆን ጉዋደኞቼም ጭምር:: የሁለተኛ ዓመት ትምህርት ኮስተር እያለ መጥቷል! ፕሮፌሰር ሳላህ ከያንዳንዱ ሌክቸር በሁዋላ በልምጥምጥ አራት መአዘን ፕላስቲክ ላይ የሳላቸውን የአናቶሚ ስእሎች ትቶልን ይወጣል:: እኛም ስሎቹን ደብተራችን ላይ ለመገልበጥ በምናደርገው ወንድማዊና እህታዊ ሽሚያ ግዚያችንን እንፈጃለን:: ግልበጣው ሰውነት ያዝላል:: እኔ በበኩሌ ከዚህ በፊት አሳይቼው በማላውቀው ሁኔታ የትምህርት ፍላጎቴ የጨመረ ቢሆንም በተለያዩ ጅጤሳ ነክ ምክንያቶች የጥናት ፕሮግራሜ መሰናከሉ አልቀረም:; አሁን ባለፈው አመሻሹ ላይ ቤተ መፅሐፍት ገብቼ አጠናለሁ በሚል ወደዚያው አቅንቼ ሳለ ተዘግቶ ጠበቀኝ:: እንዲያውም ለካ ቤተመፅሃፍቱ ሳምንቱን ሙሉ ዝግ ኑሯል:: ተስፋ ሳልቆርጥና እንደቀድሞው ስሜቴ ሳይነካ ቀን-ቀን የምንማርበት ክፍል (ሌክቸር ሆል) በመሄድ ማንበብ እንደጀመርኩ መብራት ጠፋ! በውስጤ ሊገነፍል ያለን ቱግታ አፍኘ አደርኩ:: በማግስቱ ጠዋት በመልካም ስሜት ቀኑን በመጀመር የልብስ አጠባ ፕሮግራሜን ለመተግበር በትጋት ወደ ቧንቧው ሳቀና ውሃ አልነበረም:: ምንም አይደለም በሚል በመልካም አመለካከቴ ቀጥዬና ደብተሬን ገልጬ ጠዋቱን አናቶሚ ደስ እያለኝ አጠናሁ:: ከሰዓት የተቁዋረጠው የውሃ አገልግሎት ስለጀመረ ልብስ ማጠብ ጀመርኩ:: ነገር ግን በአጠባው በግምት መሃል ላይ ውሃው እንደገና ተቁዋረጠ:: ይመለሳል ብዬ ለሰአታት ጠበኩ:: የቁራ መላክተኛ ሆኖ ቀረ::  ይህ ሲሆን ሰዓቱ ወደ አመሻሹ ገደማ ሆኗል:: በቀዳሚው ቀን ተቁዋርጦ የነበረው መብራት የተመለሰ ቢሆንም ለኔ በዚህ ወቅት አስፈላጊ አልነበረም........

ግንቦት 3 1984 አ.ም. ሰኞ
ዛሬ ፊዚዮሎጂ ትምህርት በይፋ ጀመርን:: ጠዋትም ከሰዓትም በመማር: በጠቅላላ ለአራት ሰዓት ያህል በጨቅላ ጭንቅላቶቻችን ውስጥ በፕሮፌሰር ማሂ አማካይነት በአይነት አዳዲስ የሆኑ እውቀቶች ተጠቀጠቁ::

የፒሲዋን ትምህርቶች ባጠቃላይ ሲነበቡ ደስ የሚያሰኙና የሚስቡ ሲሆኑ ነገር ግን እንደቀልድ እየበዙና እየተከመሩ የሚሄዱ ናቸው:: በፒሲዋን ሌክቸር ሆል ውስጥ እልፍ ሳይንስ ይወራል:: እኛም እልፍ እንፅፋለን እልፍም እንዳምጣለን:: አናቶሚ ደሞ እልፍ ስዕል እንስላለን:: የፕሲዋን ሌክቸሮች በነፍስወከፍ ሁለት ሰዓት የሚፈጁ ሲሆን በመሃል የአምስት እስከ አስር ደቂቃ እረፍት አለ:: በሌክቸሩ ክፍለጊዜ በያንዳንዷ ሰከንድ ከተናጋሪው አፍ የሚወጣው አዲስና ንጥር ጭብጥ ስለሆነ ለቅንጣት ጊዜ ቀልብ ማጣት ወይም ዝንጉ መሆን ቁልፍ የሆነ ግንዛቤን ሊያሳጣ ይችላል:: ስለዚህ ወደድንም ጠላንም ቀልብ ገዝተንና ነቅተን መምህራኑ የተናገሩትን እያንዳንዱዋን ነገር ደብተራችን ላይ በብእራችን መከተብ ይጠበቅብናል:: ሰሞኑን ታዲያ በርካታ ተደጋግመው ቢነበቡም የሚረሱ ሃሳቦችን ፃፍን:: በተለይ አናቶሚና ባዮኬምስትሪ በጣም ብዙ ሄደናል:: ፍሬሽማን ብንሆን ኑሮ እስካሁን በፃፍነውና ባደመጥነው ብዛት የመጀመሪያው ሴሚስተር ተገባዶ ነበር- ይሄኔ! 

ዛሬ ማታ እያጠናሁና እያነበብኩ ያመሸሁ ቢሆንም በጥናቱ አልረካሁም:: ባነባቸውም ላገናዝባቸው: ላብላላቸውና አንዱን ካንዱ ላገናኛቸው ያልቻልኩዋቸው የተለያዩ ጭብጦች (concepts) አሉ በተለይ ባዮከምስትሪ ውስጥ! ከላይ እንዳልኩት በዝንጋታና ቅፅበታዊ ቀልብ ማጣት የተነሳ ሳላዳምጥ ያመለጠኝ ነገር አለ መሰለኝ:.....


በመጨረሻ:-እኔ በበኩሌ እየበዛ ቢሄድም እንኩዋን አናቶሚ ትምህርትን ከሁሉም በጣም የወደድኩት ይመስለኛል:: እርግጠኛ ነኝ በስዕሉ ምክንያት ነው:: የተዋጣልኝ ባልሆንም ከልጅነቴ ጀምሮ ስዕል መሳል እወዳለሁ:: የአናቶሚ ስሎችን ስስል ለጊዜውም ቢሆን ትልቁን የፒሲዋን ጭንቀቴን እረሳለሁ........

Wednesday, February 4, 2015

የ PC-1 ጅምር

ሚያዚያ አስራምስት ቀን ለፒሲዋን የመጀመሪያ የሆነውን የላቦራቶሪ ከፍለ ጊዜ ጀመርን: ባዮኬምስትሪ:: አቶ ኢሳያስ በተለያዩ መምጠጫ ቱቦዎች (pipettes) ኬሚካሎችን እንዴት ራሳችንን ሳንጎዳ መምጠጥ እንደምንችል አሳየን:: እኔ ታዲያ ባለፈው አመት እንደዚሁ በቱቦ ስመጥ ተምዘግዝጎ አፌ ውስጥ የገባው ምንነቱ ያልታወቀ ኬሚካል ትዝ አለኝ:: ለካ መምጠጥም ትምህርት አለው! በክፍለ ጊዜው ብዙም አልረካሁም:: ምክንያቱም ብዙ የመለኪያ ጠርሙሶች ተበላሽተው ስለነበር በተረፉት ደህና ጠርሙሶች ዙሪያ የተማሪዎች ሽሚያ ነበር:: እኔ ደሞ ሽሚያ ፈፅሞ አይመቸኝም:: ተሰብስበን ስንሰራ እንጋፋለን:: ከስብስቡ ወደሁዋላ ቆሞ አስረጂው የሚለውን ለመስማት አዳጋች ነው.....

ከአራት ቀናት በፊት የትንሣዔ በዓል ዋለ:: በዚህ ቀን እኔ: አባይ; አምሳሉ; መንግሥቱና አያሌው ወይዘሮ አልማዝ ቤት ሄደን ነበር:: ወይዘሮ አልማዝና ቤተሰባቸው በአባይ የተነሳ የምናውቃቸው በጣም ጥሩና ለኛም መልካም አመለካከት ያላቸው ሰዎች ናቸው:: እኛም ዓመት ባል በሆነ ጊዜ እየሄድን እንኩዋን አደረሳችሁ ብለናቸውና ከበቂ በላይ ተስተናግደን እንመለሳለን:: የዚህኛው ፋሲካም ለት እንደተለመደው ነበር:: በጠዋት ወይዘሮ አልማዝ ቤት ስንደርስ እንኩዋን አደረሳችሁ ከሚለው የዓመት ባል ቃላት ልውውጥ ቀጥሎ የማስታውሰው በያይነቱ የቀረበልንን ምግብ ነው:: እጅ የሚያስቆረጥም ቀይና አልጫ ዶሮ ወጥ ከአይብ ጋር ተመግበን አብረው የቀረቡልንን አጥንቶች ቅርጥፍጥፍ አረግናቸው:: የፒሲዋን ትምህርት ግብፆቹ ጅማ በመድረሳቸው መጀመሩ ስለማይቀር በዚህ ዓመት ተረጋግተን የምናከብረው የመጨረሻው ዓመት ባል ፋሲካ ሆነ:: ወይዘሮ አልማዝ ቤት መመገብ ብቻ ሳይሆን ጠላ እየጠጣንና እየተጫወትን ለሶስት ሰዓታት ያህል ቆየን:: ከቴፕ ረኮርደሩም በሚወጡት የአስቴር ከበደ ጣዕም ያላቸው ሙዚቃዎች ተዝናናን:: ልይዘው ብሞክር ልጨብጠው በጥር......ለካስ በሀስብ ነው አወይ የኔ ነገር.....

የሁለተኛ ዓመት ትምህርታችንን በትክክል የጀመርነው ሚያዚያ አስራ ዘጠኝ ቀን ነው ማለት ይቻላል:: የፋሲካ ማግስት ሰኞ እለት በግብፆች:: ፕሮፈሰር ሳላህ ና ባለቤቱን ተዋወቅናቸው:: ሁለቱም አናቶሚና እምብርዮሎጂ በጋራ እንደሚያስተምሩን ፕሮፌሰር ሳላህ ነገረን:: የሚናገሩት እንግሊዝኛ የአረብኛ አክሰንት ቢኖረውም ለመረዳት ያማያስቸግር በመሆኑ ደስ ብሎኛል:: ፕሮፌሰር ሳላህ አግባቡና ሁኔታው ባጠቃላይ ተመችቶኛል:: የሂስቶሎጂ መምህራችንንም ተዋወቅናቸው:: ጠና ያሉ ሰው ሲሆኑ መሐመድ አብደልማሰን ይሰኛሉ::


ማክሰኞ ሚያዚያ ሃያአንድ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የምንማርባቸውን አራት ሬሶች(cadavers) አየናቸው:: በሰፊው የአናቶሚ ላቦራቶሪ ውስጥ ከጡብ በተሰሩ አልጋዎች ላይ በፀጥታ ተጋድመዋል:: ትክክለኛ የሞቱ ሰዎች ናቸው:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም ምንም አልደነገጥኩም:: ሶስቱ ወንዶች ሲሆኑ አንዱዋ ሴት ናት:: ፕሮፌሰር ሳላህ እያመላከተን ቆዳቸውን መቅደድ ጀመርን:: እኔም በቀደዳው (dissection) ዋና ተሳታፊ ነበርኩ..........