Sunday, January 31, 2016


ሐምሌ 1 ቀን 1985 አ.ም  ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ 40 ደቂቃ
ባለፈው ሰኔ መጨረሻ ላይ በዋለው ቅዳሜ: በ 1983 አ.ም አብረውን ትምህርታቸውን ጀምረው የነበሩ የዲፕሎማ መረሃ ግብር ተማሪዎች ሁሉ ተመረቁ:: አንዳንዶቹ የቅርብ ጉዋደኞቻችን ነበሩ:: ስለዚህም ከነሱጋ በመለያየታችን ሆድ ባሰን:: ሰሞኑንም ጉዋዛቸውን ሽክፈው ግቢውን እየለቀቁ ነው......

በዚህ ቀዝቃዛ የክረምት ምሽት ላይ የተለመደውና በተደጋጋሚ ከመከሰቱ የተነሳ እንደወንድም ወይም እህት የተላመድኩት የኤሌትሪክ ኃይል መቁዋረጥ ተከስቶ ስለነበር ማጥናትና ማንበብ አይቻልም ነበር:: እሰይ!!! ስለዚህም በዚህ ትምህርታቸውን በትጋት ለሚከታተሉ መጥፎ ለኔ ግን ሸጋ በሆነ አጋጣሚ ከእመቤትና ፅጌረዳ ጋር ረዘም ያለ የእግር ጉዞ እያደረግን ተናፈስን:: አየሩ መቸም ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም ርጋታ የተላበሰ እንዲሁም ባፍንጫና ባፍ ሲምጉት የሆነ ደስ የሚል ነገር ይዞ ወደውስጥ የሚገባ ስነበር ተመችቶኛል:: ከሴቶቹ እንደተለያየሁ አራቱን ጉዋደኞቼንና የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼን አብይ: መንግስቱ: ሚሊዮንና አምሳሉን አገኘሁዋቸው:: ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እንደምናደርገው ዛሬም ወደ ግሪን ሆቴል ሄደን እየጣንና እየተጨዋወትን አመሸን: ኡፍፍፍ...በቃ በጣም ነው ደስ ያለኝ:: እኔ ትምህርት ሳይሆን የሄን ነው የምፈልገው:: ከጉዋደኛጋ መሳቅ: መጫወት: መቦለት: ማውራት:መቃለድ: መቀለድ: እንደገና መሳቅ........ ወደ ጤና ሳይንሱ ስንመለስ የኤሌትሪክ ኃይል ወደቀድሞ ሁኔታው ተመልሶ ስለነበር አንዳንድ የጥናትና ፅሁፍ ግልበጣ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለ-ተማሪዎችን ማየት ይቻል ነበር::

ሐምሌ 3 ቀን 1985 አ.ም 
ዛሬ ጠንከር ያለ የሐምሌ ዝናብ አረንጉዋዴይቱን ጅማን ደበደባት:: ሐምሌ ሐምሌነቱን ለጅማ አሳወቃት:: መጣሁ: ያዥ እንግዲህ! አላት:: ጅማም ይህን ተቀብላ ክረምት ክረምት መሽተት ጀመረች:: ይበልጥ አረንጉዋዴ ሆነች::በየቦታው እሸት በቆሎ መታየት ጀመረ:: ሻይ የሚጠጣ በረከተ:: ወፍራም ልብሶች ተማሪዎች ላይ ፊጥ ብለው ይታዮ ጀመር:: የቤተ መፅሀፍቱ ሙቀት መቀነሻ ቬንትሌተሮች ስራቸውን አቆሙ:: ስለዚህም ቤተመፅሃፍቱ ውስጥ የርምጃና የመፅሀፍ ገለጣ ድምፆች በቬንትሌተሮቹ ዝዝ...ዝታ መሸፈናቸው ቀርቶ ይሰሙ ጀመር:: ጠዋትም ማታም አየሩ መቀዝቀዝ ጀመረ..........

እንደ አምናው የፊዚዮሎጂ ትምህርት በአንድ መስጠሊ ግብፃዊ መምህር የተነሳ ሊደብረኝ የሚሞክረውን የማይክሮባዮሎጂ ትምህርት እንዴት አድርጌ ቀልቤን እንደምሰጠው ግራ ገብቶኛል:: ሰውየው በጭራሽ አልጣመኝም:: ነካ ነካ ነው የማስተማር ዘዴው:: ከትምህርቱ በተጉዋዳኝ ከፍል ውስጥ በላይበላዩ ሲጃራ ያጨሳል::: እያንዳንዱን ሲጃራ አጭሶ ሲጨርስ እሳቱን የጫማው ሶል ላይ ያጠፋና ቁሩውን በመስኮት ወደውጭ ከወረወረ በሁዋላ ከያዘው ባኮ ውስጥ ሌላ አውጥቶ በላይተር ይለኩሳል:: ከዚህ በፊት አይቼ የማላውቀው ነገር ነው::

ባጠቃላይ ከሁለተኛ ዓመት ይልቅ የሻላል ብዬ የተማመንኩበት የሶስተኛ ዓመት ትምህርት ይባስ ብሎ ደረቅና የማይስብ እየሆነብኝ ነው::

ሐምሌ 5 ቀን 1985 አ.ም 

እኔና ጉዋደኛዬ ቤተማርያም ዛሬ ምሽት ላይ ተአምር በመሰለ ሁኔታ ከሌባ ጡጫና ዝርፊያ አመለጥን:: ነገሩ ባጭሩ እንዲህ ነው:: እኔና ቤተማርያም የዛሬውን የሌክቸር ሆልና የላይብረሪ ጥናታችንን አጠናቀንና አንድ ላይ ሆነን ወደ ዶርማችን ስንመለስ ወደ ዋይት ሃውስ ህንፃ የሚያመራው ቀጭን መንገድ ላይ በግምት ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ 45 ላይ ሁለት ሰውነታቸው ገዘፍ ያሉ ሰዎች ከፊትለፊታችን ወደኛ አቅጣጫ እየተራመዱ አለፉን:: ጨዋታ ይዘን ስለበር አላስተዋልናቸውም:: ሰላሳ ሰኮንድም ያህል ሳይቆይ ከበስተጀርባችን ከፍተኛ ጩኸት ሰማንና ፊታችንን ወደሁዋላ በማዞር ባለንበት ቀጥ ብለን ቆምን:: ወዲያውኑ ከየአቅጣጫው የጤና ሳይንሱ ዘበኞችና ሌሎች ተማሪዎች ወደ ተጮኸበት አቅጣጫ ሲሮጡ አየናቸው:: በትክክል እኛን አልፈው የሄዱት ግዙፍ ሰዎች ሌቦች ነበሩ ማለት ነው! እኔ በበኩሌ ካለሁበት ቆሜ ሌቦቹ ወደ በጨለማ ወደተሸፈነው ጫካው ውስጥ እየሮጡ ሲጠፉ ይታየኝ ነበር:: ማንም የተከተላቸው የለም: ያ አደጋ አለውና:: እኔና ቤተማርያም ከሁዋላችን የነበሩትና በሌቦች ጥቃት የተሰነዘረባቸው ተማሪዎች ባይኖሩ ኖሮ የነሱ እጣ ፈንታ የኛ ይሆን እንደነበር በማሰብ ተሸማቀቅን...ኡ

Thursday, January 21, 2016

ግንቦት መጀመሪያ  1985 አ.ም.

ከመጋቢት 7 አስከ ሚያዚያ አጋማሽ አዲሳበባ በተሰቦቼ ጋር ያሳለፍኩትን አረፍት አጠናቅቄ ወደ ዉዷ ጅጤሳ ተመለስኩ:: የሶስተኛ አመት ትምህርቴንም ጀመርኩ::
አጠቃላይ በሆነ እይታ የዚህን አመት ጅምር ብዙም ደስ የሚል ወይም የሚስብ ነገር አጣሁበት:: ዓመቱ ስሙ PC-2 (ፒሲ ቱ) ይባላል:: ትምህርቶቹ በአይነትና በብዛት ከፒሲ-ዋን ትምህርቶች የሚልቁ  ሲሆን በርካታ ከህክምና ጋር በቀጥታ እንዴት አንደሚገናኝኙ ያልገቡኝ ትምህርቶችንም ያካትታል:: ከህክምና ጋር በቀጥታ የሚገናኙትበግብፆች የሚሰጡን እንደነፓቶሎጂና ፋርማኮሎጂ ያሉት የሚስቡ ቢሆንም ተነበው ለመታወስ ሃይልና ጥረት የሚጠይቁ ይመስላል:: ባለፈው እራሴን ለመግለጽ አንደሞከርኩት የንባብ ሀይልና ጥረት አኔ ዘንድ ያሉ ነገሮች አይደሉም::

ከላይ ከህክምና ጋር የማይገናኙ ያልኩዋቸውን ትምህርቶች የሚያስተምሩን መምህራን በሙሉ አበሾት ሲሆኑ ሀኪም አለመሆን ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ አጅግ በጣም በርካታ ሃሳቦችን በበርካታ ትራንስፓረንት ሺቶች ላይ አስፍረው ነው ወደ ሌክቸር ሆል የሚመጡት:: ወደ ክፍሉ እንደገቡ የትራንስፓረንት ሺት ማስቀመጫ ፕሮጀክተር ላይ የመጀመሪያውን ሺት ያኖሩና ጽሁፉ ከሚንጸባረቅበት ነጭ ጨርቅ ላይ አይናቸውን ተክለው እንዲሁም በከፊል ለኛ ለታዳሚዎቹ ጀርባቸውን ሰጥተው መናገር ይጀምራሉ:: ከዚያም አንዱን ትራንስፓረንት ሺት ሲያነሱና ሌላኛውን ሲያስቀምጡ ብሎም ሲናገሩ ቆይተው ክፍሉን ለቀው ይወጣሉ:: የዚህ ኣይነቱ ሂደት ድምር ውጤት ትምህርት ነው ለማለት ይክብደኛል:: ይልቅስ አኔና ሌሎች ብዙ ፒሲ-ቱ ተማሪዎችን ሰነፍ: የደነዘዝንና: የትምህርት ጥላቻ ያለን እንድንሆን አየገፋፋን ነው:: እውነት ለመናገር ሁላችንም እጅግ ከባድ የሚባለውን ፒሲዋንን አልፈን የመጣን ስለሆንን ፒሲ- ላይ ዘና ማለት እንጂ መጨነቅ ምናምን ገለ-መለ አንፈልግም:: እነዚህ ህክምና አልቦ ትምህርቶች ሲታከሉ ደግሞ የሚሆነውን ለማሰብ አይከብድም:: አኔና ጓደኞቼ እንደዚህ አይነት ትምህርቶች የሚሰጡበት ክፍለ ግዜ ላይ ክፍል አካባቢ አለመገኘትን እንደ ፋሽን ከያዝነው ቆየን....


ግንቦት 14 ቀን 1985 አ.ም.

ምናብ
ዛሬ ለምን አንደሆነ በቅጡ ባይገባኝም ከወትሮው እጅግ በተለየ ሁኔታ በዝምታ ነው የዋልኩት:: በቃ ዝም ማለት አማረኝ:: ከሰዎች ጋር ከመነጋገር ይልቅ በውስጤ የማስበውን ሀሳብ ማስታመም ፈልግሁ:: ይህ መቼም ከባድ ነው:: ምክንያቱም ሰዎች በውስጤ የማስበውን ስለማይረዱ መንገድ ላይም ሆነ ሌላ ቦታ ስንገናኝ በማነጋገር የብቸኝነቴን አጥር በርቅሰው ይገባሉ:: ዝም ማለት የፈግሁበትን ምክንያት ጠረጠርኩ: ምናልባት ኪሴ ባዶ በመሆኑ ይሆናል:: ይህ ግን በተደጋጋሚ እንደውም ያለማቁዋረጥ የሚከሰት ስለሆነ አንዴት ዝም ያስብለኛል? አንግዲህ የእጦት መደጋገም: ማድረግ አለመቻልን በማሳሰብ ልቤን አስከፍቶት ይሆናል:: አውነቱን ለመናገር ባሁኑ ሰኣት የመግዛት አቅሜ እሮብና ቅዳሜ ለጫማ ማስጠረጊያ ከማውላቸው ሁለት የምሳ ላይ ዳቦዎች የዘለለ አይደለም፥:: ባያሳፍርም ቅስም ያጣምማል:: በቃ በረዥሙ ከፋኝ:: የመኖር ጉጉቴ ባይቀንስም አንዳንድ ትምህርት ነክ ነገሮችን ለመስራት የሚያስችል ጉልበት ኣጣሁ::ተፈጥሮኣዊ ባህሪዬ የነበረው ሌክቸር ማዳመጥ ራሱ ሃይል የሚጠይቅ ሆነብኝ:: መጻፍማ አይታሰብም:: ብቻ ባጠቃላይ አእምሮዬ ንቃት ሰውነቴ ደግሞ ብርታት ጎደለው:: ተደጋጋሚ የኪስ ባዶነት በፈጠረው መከፋት የተነሳ::ግን አኔ ብቻ ነኝ አንዴ ኪሰ ባዶ የሆነ? ኣይመስለኝም:: ክርስትያን አንደመሆኔ መጠን በእግዚኣብሄር ተስፋ ማድረግ እንደሚጠበቅብኝ ባውቅም ይህን ስሜት ግን አሁን ልቀዳጀው አልቻልኩም:: አንዳውም መንፈሳዊ ሁኔታ ከልቤ ጭራሽ ጠፋ:: አሁን አኔ የማስበው የዚህን ኣለም ተጨባጭ ሁኔታ አንጂ በእግዚኣብሄር አንድ ነገር ይሆናል የሚል ነገር አይደለም:: ወይኔ ተስፋ ቆረጥኩ ማለት ነው? ወደፊቱ ጨልሞ ታየኝ ማለት ነው? እኮ ኪስ ባዶ በመሆኑ ምክንያት?......ሳልሳሳት አልቀርም:: ልክ ነው አምነት ትዕግስትና ተስፋ ያስፈልገኛል .......

Sunday, January 10, 2016

ሰኞ የካቲት 15 ቀን ፩፱፰፭ አ.ም..ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ 45 ደቂቃ

CBTP
የሁለተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርቴን በብቃት በማጠናቀቅ ፈተናዎቹን በሙሉ በማለፍ ለሶስተኛ ዓመት እንደታጨሁ ይፋ ሆነ:: የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼም  ሆኑ ሌሎች እኔን መሰሎች ሁሉ አለፉ:: መግለፅ በሚያዳግት ሁኔታ ሁላችንም ደስ አለን:: ውጤታችን ይፋ ከሆነ በሁዋላ ታስረው እንደተለቀቁ እርግቦች ሆንን.... በጤና ሳይንሱ  ግቢ ውስጥ  ባሉት ረዣዥም  ዛፎች ላይ ወዲያና ወዲህ ከሚስፈነጠሩት ጉሬዛዎች ቀጥሎ እንደልባችን  የምንታይ  እኛ ሆንን:: በተከተሉት ቀናት በኛ ዶርም  ዉስጥ  ከሰዓት ከሰዓት መሰባሰብን ልማዳችን አረግነው:: በብዛት ሙዚቃ ይኖራል:: የመሀሙድ አህመድ የቆዩ እንዲሁም  የአስቴር አወቀ ለስላሳ ዘፈኖች ዋናዎቹ ናቸው:: እነዚህን እየሰማን የባጥ የቆጡን እናወራለን:: በፈተና ወቅት ሳንሰማቸው ያመለጡንን የአለምም ሆነ ያገር ወሬዎች ሰምተን የመረጃ ቁዋቶቻችንን እናድሳለን::

በነገራችን ላይ: በጅማ ጤና ሳይንስ የህክምና ትምህርት መረሃ ግብር መሰረት የአመቱ  ፈተና ካለቀና ውጤት ከተሰማ በሁዋላ ወደቤት መሄድ የለም! Community Based Training Program (CBTP) ላይ ለአንድ ወር መሳተፍ አለብን:: ይህ ሕብረተሰብ ተኮር የጤና ስልጠና የትምህርታችን አካል ነው:: በቡድን ተከፋፍለን ጤና ሳይንሱ በሚመድበን ቀበሌ በመሄድ በየቀኑ የተለያዩ ተግባራት እናከናውናለን:: በዚህ ዓመት የምንሰራው ሥራ በዋነኘት ከነዋሪው መረጃ መሰብሰብ ይሆናል:: ስለዚህም አስቀድሞ የተዘጋጁ ጥያቄዎችን ይዘን ከቤት ቤት እንዞራለን::


እኔ ያለሁበት ቡድን የተመደበው የጅማ ከተማ አካል የሆነ ነገር  ግን ዳርቻ ላይ ያለና ከፊል ገጠራማ ቀበሌ ውስጥ ነው:: ከቡድናችን ውስጥ በተለይ እኔና ኃይሉ የምንሰራበት ቦታ ደምበኛ ገጠር ነው:: እንዴት ይህ ቦታ በጅማ ከተማ ስር እንደሆነ ግራ ገብቶኛል:: በዚህ አካባቢ እኔና ኃይሉ መረጃ ለመሰብሰብ በምንዘዋወርበት ወቅት ያስተዋልኩት አንድና አንድ ነገር ቢኖር ባካባቢው የሚኖሩትን ሰዎች ስር የሰደደ ድህነት ነው:: ከዚህ በፊት ለእረፍት ወደ ራሴ የትውልድ ሰፈር ስመለስ ያስተዋልኩትን የነዋሪ ድህነት አስታውስኩ:: ይህ ግን እጅግ በጣም የባሰ ነው:: ገጠር በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮ ቸርነት የዘሩትን ፍሬ ከመጠበቅ በስተቀር ሌላ ምንም ሃብትና ንብረት የሌላቸው ምስኪን ቤተሰቦች አየሁ:: አንዳንድ ቤተሰቦች ስምንትና ዘጠኝ የሚሆኑ ልጆች ያሉበት ሲሆን የዓመት ገቢያቸውን በምንጠይቃቸው ጊዜ የሚሰጡን መልስ "ከሶስት እስከ አራት ኩንታል በቆሎ" የሚል ነው:: ማመን ያስቸግራል..... እዚህ ገጠራማ የቀበሌ ከፍል የኤሌክትሪክ መስመር ሰንጥቆት ቢያልፍም በየቤቱ ግን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም መብራት የለም:: ስልክም የለም:: የዉሃ መስመር የሚባል ነገር የለም:: ይህ አጋጣሚ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ሀገራችን ድህነት የበለጠ መረዳት ያገኘሁበት ይመስለኛል.....