ጥቅምት ፬ ፩፱፰፫ አ.ም.
የመጀመሪያው ዳፍንት...
ትናንትና የጤና ሳይንሱን ግምብ አጥር በውጭ በኩል ተደግፌ ቆሜ ሳለ በእድሜ ከኔ እኩል የሆኑ ወይም የሚያንሱ ጮርቃ ወንዶች ቁጥራቸው አራት በሚሆን አውቶቡሶች ታጭቀው ሲንቀሳቀሱ አየሁ:: መሬት ላይ ብዛት ያላቸው ሰዎች ቁመው አንዳንዶቹም ከአውቶቡሶቹ ጎን እየሮጡ እጃቸውን በማወዛወዝ ሲሰናብቷቸው ተመለከትኩ:: አንዳንድ በእድሜ የገፉ ሴቶች እና እናቶች ያለቅሳሉ:: የአውቶቡሶቹ መድረሻ የብሔራዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ካምፕ እንደሆነ ምንም አልተጠራጠርኩም:: ከዚያም ወደ ጦርነት:: በእውነቱ እጅግ አዘንኩ:: ያን ትዕይንት እያየሁ ታዲያ በውስጤ ሲብሰለሰሉ የነበሩ ጥቃቅን ና እንቶ ፈንቶ ችግር ተብዬ ሃሳቦችን ይዞ መቀጠል የማይመስል ሆኖ ታየኝ:: ስለዚህም በዚያው ቅፅበት እንደ ሲጋራ ቁሩ ወደ መሬት ጥዬ ረገጥኩዋቸው:: የኛ ቅምጥል አልኩት ራሴን:: ደሞ እኔን ብሎ በረባ ባልረባው አሳቢ:: ከዚያ ትዕይንት ጀምሮ ወደፊት ጤና ሳይንሱ ውስጥ እያለሁ ለሚያጋጥሙኝ መሰናክሎች እጅ ላለመስጠት በውስጤ ለራሴ ቃል ገባሁ:: ማትሪክን ባላልፍና እዚህ ባልመጣ ኑሮ የኔም እጣ ፈንታ እንዲህ ነበር ማለት ነው? እዉነት የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዬን ባላልፍ ምን ነበር የማደርገው? የተዘጋጀሁበት ጥያቄ ስላልነበር ዘለልኩት::
ከላይ የገለፅኩትን ቃል መግባት ተከትሎ ምሽት ላይ የኤሌትሪክ መብራት በጤና ሳይንሱ በሙሉ በመቁዋረጡ ዳፍንት ሰፈነ:: ጅማ ከመጣሁ የመጀመሪያዬ የሆነው ይህ ዳፍንት ሲከሰት መፃፍት ቤቱ ውስጥ ቁጭ ብዬ ነበር:: በነገራችን ላይ መፃህፍት ቤቱም ልክ እንደኛ ማደሪያ የተሰራው ከ ቀይ ሸክላ ሲሆን በስፋት ግን ይበልጣል:: ሌሎች እኔን መሰሎች ሲገቡ ስላየሁ እንጅ እኔ በቁም ነገር የማነበው ነገር ኖሮኝ አልነበረም:: ቀደም ብዬ እንዳልኩት ምንና እንዴት እያነበቡ እንደሆነ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው::ግን አለ አይደል ማን ከማን ያንሳል! ማን ገብቶ ማን ይቀራል.... የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ...አይነት አበሻዊ ፉክክር ውስጤን ጎብኝቶት ኑሮ ጅጤሳን በረገጥሁ በሁለት ሳምንቴ በዚያ ሰዓት መፅሐፍት ቤት ተገኘሁ :: ለነገሩ የተቀመጥኩት ሆን ብዬ ዳርቻ ላይ ስለነበር ወጭና ወራጁን የጎሪጥ አንዳንዴም ሙሉ በሙሉ ሳይ ነበር: ዳፍንት አቁዋረጠኝ እንጂ......ለጨለማ አዲስ ባልሆንም ከዚህ በፊት የማዉቀው መለስ: ለስለስ ያለ ነበር:: ይሄኛው ለየት አለብኝ:: ስለዚህም ዳፍንት አልኩት:: ባገራችን አይን ቢወጉ አይታይም እንደሚባለው:: ከቅፅበት በፊት በነበረው ብርሃንና በዳፍንቱ መሃል ያለው ትየለሌ ልዩነት በውስጤ ግዙፍ ድንጋጤን በመንዛቱ ከመጮህ መለስ ያለ ድምፅ ሳይወጣኝ አለቀረም:: እርግጠኛ ግን መሆን አልቻልኩም:: ምክንያቱም በተመሳሳይ ግዜ ብዙ ጭዋሂዎች ነበሩ:: ብቻ ምንነታቸው ያልታውቁ በርካታ ድምፆች ነበሩ:: በለው! ለማንኛውም እኔ ቀደም ብዬ ወደ ማሰልጠኛ የሚሄዱትን ወጣቶች እያየሁ ለእክል ላለመረታት የገባሁትን ትኩስ ቃል በመንተራስ ልቤን አይዞህ እንግዲህ ቼ በል! አልኩት:: በእውነቱ የበለጠ ግን ያጠነከረኝ ዳፍንቱ ሚዛናዊ: ማለትም ሁሉንም ተማሪ ያካተተ መሆኑ ነው:: "ዋናው ማንም አለማንበቡ ነው".....አልኩ በሆዴ:: እንደውም እንኩዋን ጠፋ! ልክ ጠይቄ ያስጠፋሁት ነው የመሰለኝ:: (እርገጥ ነው በሁዋላ እንደሰማሁት አንዳንድ የመኝታ አዳራሻችን ውስጥ ሆነው ሲያነቡ የነበሩ ተማሪዎች ዳፍንቱ በሰፈነበት ቅፅበት በተጠንቀቅ ላይ የነበሩ ሻማዎችን እንደለኮሱ ተስተውሏል)::ብርሃን ተመልሶ እንዲመጣ ብመኝም ግን ትንሽ ሁሉም እስከሚተኛ ዘግየት ቢል አልኩ በልቤ:: ምን አሷሸኝ: እኔን በዚያ ወቅት ያሰኘኝ የሸክላው አዳራሽ በር ጋ ወይም ሌላ የሆነ ቦታ ተቅምጦ ሰብሰብ ብሎ በተፈጠረው ጨለማ ቧልት ማውራት ና መሳሳቅ....... ነገ ግን በቃ የምሬን መማር እጀምራለሁ::
በነገራችን ላይ ጤና ሳይንሱን ከረገጥኩበት ቀን አንስቶ እስከአሁን ድረስ ግቢዉን: የወደፊት ጉዋደኞቼን: ትምህርቶቹንና አስተማሪዎቹን ስለማመድና ሳጠና ነበር:: ቀርቤ ያነጋገርኩዋቸው ተማሪዎች በሙሉ በባህሪ ሸጎች ናቸው:: ምንም አይሉም:: ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ናቸው:: ከነሱ ውስጥ አራት ሴቶችም አሉባቸው:: ከሚያስተምሩን ውስጥ በተደጋጋሚ ያየሁት የዲፓርትመንት ኃላፊ የሆነውን ተስፋልደትን ነው:: ሂሳብ ያስተምረናል:: እስካሁን ባየሁት ፀባዩም ሆነ የማስተማር ችሎታው ተመችቶኛል.....
No comments:
Post a Comment