ሚያዚያ ስምንት አስራዘጠኝ ሰማንያ ሦስት
ቁማር....
ኣሁን እኩለ ለሊት ካለፈ 58 ደቂቃ ነው፥፥ ቅድም ልክ ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ላይ ቁማር ቆምሬ የበላሁትን 60 ብር ይዤ ወደ መኝታ ክፍሌ መጣሁ፥፥ ሰሞኑን ቁማርን በፍቅር እየተጫወትኩ ነው፥፥ ግን ገንዘብ ለማግኘት ብዬ እንዳልሆነ እኔና አግዚአብሄር ነን የምናውቀው፥፥ የምሰራው ሌላ ነገር ሰለሌለ የሚገዳደረኝን ዳተኝነት ለመግታት እንዲሁም ጊዜ ለመግደል ስል ነው እንጂ.... ምንም ኣይነት የመቆመር ልምድ የለኝም:: በእርግጥ በልጅነቴ ሰፈር ዉስጥ ብይ ና ዘውድ-ጎፈር ትንሽ ተጫውታለሁ። ፥፥ መቆመሪያው ዶርም ከኔ ዶርም ርቆ የሚገኝ ሲሆን፥ ብዙዎቹ ተጫዋቾች ልምድ ያላቸው ቁንጮ ቆማሪዎች ናቸው። አንዳንዶቹ በድሜ ከኔ የገፉ ጡንቸኛና ጉልበተኛም ሊሆኑ ይችላሉ፥፥ ሸዋጆችም በሽ ናቸው፥፥ እኔ በበኩሌ ብዙውን ግዜ ምንም ኣይነት ስልት ወይም ማሰላሰል ሳይታከልበት ከየት እንዳመጣሁት በማላውቀው ድፍረት ገንዘብ ኣሲዛለሁ፥፥ ለነገሩ ጨዋታው ማሰላሰል የሚጠይቅ አይደለም፡ ብዙውን ግዜ ወጣ-ገባ የሚባለው ነው፥፥ በዚህ መሰረት ኣንደኛው ተጫዋች ከካርታ ክምር ውስጥ ኣንዲት ስቦ ቁጥሩን ለተቀናቃኙ ሳያሳይ ይይዛል፥፥ ተቀናቃኙ ካርታዎችን በየተራ ካርድ መዛዥ ና ራሱ ፊት ለፊት ይጥላል፥፥ ካርድ መዛዥ የያዘውን አይነት ካርታ ፊትለፊቱ የወደቀለት ኣሸናፊ በመሆን የተያዘውን ገንዘብ በሙሉ ይወስዳል፥፥ ከዋናዎቹ ተጫዋቾች ጀርባና ዙሪያ ለሎችም ተማሪ ቆማሪዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከተጫዋቾቹ ጋ ገንዘብ ያስይዛሉ፥፥ በድፍረት(ወይም በጭፍን) በማደርጋቸው እንስቃሴዎች በተደጋጋሚ እድለኛ የመሆኔ ነገር ለራሴ ገርሞኛል:: የዛሬው ቁማር ላይ አብሮኝ የነበረው መንጌ በኔ እድለኛነት ከመተማመኑ የተነሳ ራሱ መጫወት ትቶ እኔ በምጫወተው ሲያስዝ (ና ሲበላ) ነው ያመሸው::
በነገራችን ላይ ዛሬ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በኣል ስለሆነ ለስልጠና አልወጣንም:: በብላቴ የሚገኙ ኣየር ወለዶች እያመጹ መሆናቸውን የሆነ ሰው ሹክ ኣለኝ፥፥ ለምን እንደሆነ አልነገረኝም:: ምንም የተለየ ነገር ባለማየቴ መንገድ ላይ ኣየር ወለድ ባየሁ ቁጥር ኣተኩሬ ስመለከት ነበር፥፥ እውነትም ኣብዛኖቹ ታጥቀዋል፡ቦምና ክላሽ፥፥ እኛን ተማሪዎችን ግን ምንም የሚሉን ነገር የለም....ተማሪው በሚያሳየው ቅጥ ያጣ ባህሪ የተሰላቹ ና እልህ ውስጥ የገቡ ስለመሰለኝ በውስጤ ስስ ሽብር ተሰማኝ:: ቢ*****ስ??
ሚያዚያ ዘጠኝ አስራዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሶስት
ጭብጨባ.....
ጭብጨባ.....
ዛሬ ከቀኑ ሰባት ሰኣት ኣካባቢ ኣንዲት ሄሊኮፕተር ብላቴ ግቢ ውስጥ ኣረፈች ኣንደኛ ብርጌድ ኣካባቢ፥፥ ካየር ወለዶቹ ኣመጽ ጋር በተያያዘ ነው መሰለኝ፥፥ ሰልጣኝ ተማሪ ከያለበት በመሄድ ሄሊኮፕተሩዋን ከበባት፥፥እንደመሰለኝ በርካታ ተማሪ ፕሬዝዳንት መንግስቱ መጥተው ይሆናል የሚል ግምት ነበረው፥፥ እኔ የቆምኩት ራቅ ብዬ ስለበር ከሄሊኮፕተሩዋ የሚወጣውን ባለስልጣን ማየት ኣልቻልኩም፥፥ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለሁ ኣንድ ኣየር ወለድ እኔ ወደቆምኩበት ቦታ ኣቅጣጫ መጣና ቆመ፥፥ እዚያም ለተሰበሰብነው እንዲህ አለን "እኛ የመጣውን ሰው ማን እንደሆነ ኣናውቀውም፥፥ ግን በጀኔራል ባልስልጣን ኣንመራም፥፥ሲቪል ባለስልጣን ነው የምንፈልገው፥፥ተማሪዎችም ድጋፋችሁን እንደምትሰጡን እንተማመናለን፥፥" ፥፥ከተሰበሰብነው ተማሪዎች ውስጥ "አዎ እንደግፋችሁዋለን የሚል ጭብጨባ የተቀላቀለበት የጋራ የሚመስል ድምጽ ወጣ" እንደግፋችሁዋለን የሚለው አባባል ሲገርመኝ ጭብጨባው ለምን እንደሆነ ፈጽሞ አልገባኝም። ለነገሩ ልገረም አይገባኝም።፡ጭብጨባ፡በየቦታው በዝቱዋል። ሳል ልስል ፈልጌ አፍኜ ያዝኩት። ደሞ እንዳይጨበጨብልኝ..
በወጋችን ላይ ዛሬም ቆመርኩ 56 ብር እንክት አድርጌና የ ጡንቸኞችን አይን ፍጥጫ (ብሎም ጡጫ) አምልጬ፡በውድቅት ወደ ዶርሜ እንደእገባሁ ይታወቅ.....
No comments:
Post a Comment