Friday, January 2, 2015

ጥር ስምንት ቀን  አስራ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት አ.ም.  
አዲስ አበባ
ባይ ባይ ፍሬሽ ማን

በዚህ ቀን ምሽት ላይ አዲስ አበባ ቀራንዮ የሚገኘው ቤታችን ውስጥ ሆኘ ቴሌቪዥን እያየሁ ይህን ፅሁፍ አሰፈርኩ:: እነሆ የአንደኛ ዓመት የህክምና ትምህርቴን አጠናቅቄ ለእረፍት እዚህ ተገኝቻለሁ:: ሶስተኛ ቀኔ መሆኑ ነው::

ባለፈው ጥር ሁለት ቀን አስፋው የተባለውን የባቻችን አባል መሸኛ አደረግንለት:: እንደመሰለኝ አስፋው ፈተናዎቹን ተንጠልጥሎም ቢሆን ያለፈ ሲሆን የወደፊት ሂወቱን ግን በህክምና ትምህርት ውስጥ ሆኖ ላለመቀጠል ወስኑዋል:: ስለዚህም ጅጤሳንና እኛን ተሰናበተን:: የኛ ባች በለፈው ዓመት መስከረም ላይ በ47 አባላት ተጀምሮ አሁን 38 ደረሰ:: በነገራችን ላይ እኔም ወደ ሁለተኛ ዓመት አለፍኩ ማለት ነው::

ጥር አምስት ቀን ጅማን ለቅቄና በክፍለሀገር አውቶቡስ ላይ ተፈናጥጬ ለእረፍት የትውልድ ከተማዬ ከሆነችው አዲስ አበባ ገባሁ:: ጉዞዬ እንደተለመደው ወደ አስር ሰዓት ፈጅቶ ነበር: ለምሳና ለቁርስ የታረፈውን ጨምሮ:: አውቶቡሱ አዲስ አበባ ቃሊቲ ን አልፎ ከካራቆሬ ጀምሮ ያሉትን የኮልፌ ሰፈሮች እየሰነጠቀ ሲያልፍ አካባቢያዊ የሆነ ልዩ ስሜት ተሰማኝ: ደስ ደስ የሚል:: አውቶቡሱ በሹፌሩና በረዳቱ መራጭነት የወቅቱን ኤፍሬም ታምሩ ዘፈን እያንቆረቆረ አሮጌው አውሮፕላን ማርፊያ ሲደርስ እንዲቆምልኝ አስደርጌ ወረድኩ:: ከዚያም ሻንጣዬን እንደተሸከምኩ የመኪና መንገዱን ተሻግሬ በቀኝ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስትያንን በግራ የ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን መኖሪያ ቤት አልፌ ውስጥ ውስጡን ወደ ቀራንዮ መኖሪያ ቤታችን አመራሁ.....

ቤተስቤን በሰላም በማግኘቴ ደስ ያለኝ ቢሆንም በደረስኩ በማግስቱ ሰፈራችንና አካባቢው ውስጥ ከአብሮ አደግ ጉዋደኞቼ ጋር በመሆን ስዘዋወር ባየሁት የሰዉ የኑሮ ሁኔታ ግን ልቤ ሳይደናገጥ አልቀረም:: በአንድ ወቅት ከቤት የማይወጡ የነበሩና ንፅሕናቸው ተጠብቆ ትምህርት ቤት ሲሄዱ አያቸው የነበሩ አንዳንድ "የደህና ቤተሰብ" ሕፃናት ተጎሳቁለውና ቆሽሸው ከቤታቸው በራፍ ላይ በዝተው ተመለከትኩ:: ለወትሮው እሁድና ቅዳሜ ብቻ ሰፈር ውስጥ ይታዩ የነበሩ ለስራ ጠዋት ወጥተው ማታ ይመለሱ የነበሩ በርካታ አባቶች ያለስራ ተቀምጠው ና ሰውነታቸውም ከስቶ ሳይ የአባቴ ማስተማር መጀመር በውስጤ እፎይታ እንዲሰማኝ አደረገኝ:: ትንሽ የኛ ቤተሰብ ይሻላል አልኩ በልቤ:: በርካታ ቤተሰቦች የአጥር ግቢያቸው በራፍ ላይ ሸቀጣ ሸቀጦችን ደርድረው ችርቻሮ ንግድ ጀምረዋል:: በአጠቃላይ የሰፈራችን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ወትሮ ከማውቀው ዝቅ ያለ ሆኖ ተሰማኝ:: ከአብሮአደግ ጉዋደኞቼ ጋ ሳወጋ እንደተገንዘብኩት የመንደር ውስጥ ውንብድናና ዘረፋ ብሎም የመንገድ ላይ ድብድብ ተስፋፍቱዋል:: ብዙ ሰዎች በመንግስት ደስተኞች አለመሆን ብቻ ሳይሆን ጥላቻም ያንፀባርቃሉ::

ዕረፍቴ ሁለት ወር ከአስራምስት ቀን የሚፈጅ ስለሆነ እንዴት እንደማሳልፈው ማሰብ አለብኝ:: ለጊዜው ይሄ ነው የምለው እቅድ የለኝም:: ወላጆቼም ቢሆኑ የገንዘብም ሆነ እኔን ወንድሜንና በቤት ያሉትን አራት እህቶቼን የማስተዳደር አቅማቸው ደካማ ስለሆነ ያቀዱልኝ ምንም አይነት ነገር የለም:: ጤና ሳይንሱ ውስጥ እያለሁ በእርግጥ ለእረፍት አልቸኮልኩም ነበር:: ይልቅስ የቸኮልኩት የአንደኛ ዓመት ትምህርት እንዲጠናቀቅ ነበር:: በዚያ ደስ ይለኛል:: እረፍቱ ግን.........ረዥም ነው:: በተቻለኝ መጠን ብዙ መፅፍትን ለማንበብ አስባለሁ:: በተለይ ለሁለተኛ ዓመት የህክምና ትምህርቴ አስፈላጊ የሆነውን በትዕግስት የማንበብ ልምዴን ለማጎልበት ከአሁን ጀምሮ ልቦለድም ሆነ ሌሎች አይነት መፅሃፍቶችን ለብዙ ሰዓታት ያለማቁዋረጥ ማንበብ መጀመር አለብኝ:: በቤታችን የሚገኙትን የአባቴን  the book of knowledge የተሰኙትን Encyclopedia መፅሃፍት የቻልኩትን ያህል ለማንበብ አስቢያለሁ.....


No comments:

Post a Comment