የ PC-1 ጅምር
ሚያዚያ አስራምስት ቀን ለፒሲዋን የመጀመሪያ የሆነውን የላቦራቶሪ ከፍለ ጊዜ ጀመርን: ባዮኬምስትሪ:: አቶ ኢሳያስ በተለያዩ መምጠጫ ቱቦዎች (pipettes) ኬሚካሎችን እንዴት ራሳችንን ሳንጎዳ መምጠጥ
እንደምንችል አሳየን:: እኔ ታዲያ ባለፈው አመት እንደዚሁ በቱቦ ስመጥ ተምዘግዝጎ አፌ ውስጥ የገባው ምንነቱ ያልታወቀ ኬሚካል
ትዝ አለኝ:: ለካ መምጠጥም ትምህርት አለው! በክፍለ ጊዜው ብዙም አልረካሁም:: ምክንያቱም ብዙ የመለኪያ ጠርሙሶች ተበላሽተው
ስለነበር በተረፉት ደህና ጠርሙሶች ዙሪያ የተማሪዎች ሽሚያ ነበር:: እኔ ደሞ ሽሚያ ፈፅሞ አይመቸኝም:: ተሰብስበን ስንሰራ እንጋፋለን::
ከስብስቡ ወደሁዋላ ቆሞ አስረጂው የሚለውን ለመስማት አዳጋች ነው.....
ከአራት ቀናት በፊት
የትንሣዔ በዓል ዋለ:: በዚህ ቀን እኔ: አባይ; አምሳሉ; መንግሥቱና አያሌው ወይዘሮ አልማዝ ቤት ሄደን ነበር:: ወይዘሮ አልማዝና
ቤተሰባቸው በአባይ የተነሳ የምናውቃቸው በጣም ጥሩና ለኛም መልካም አመለካከት ያላቸው ሰዎች ናቸው:: እኛም ዓመት ባል በሆነ
ጊዜ እየሄድን እንኩዋን አደረሳችሁ ብለናቸውና ከበቂ በላይ ተስተናግደን እንመለሳለን:: የዚህኛው ፋሲካም ለት እንደተለመደው ነበር:: በጠዋት ወይዘሮ አልማዝ ቤት ስንደርስ እንኩዋን አደረሳችሁ ከሚለው የዓመት ባል ቃላት ልውውጥ ቀጥሎ የማስታውሰው
በያይነቱ የቀረበልንን ምግብ ነው:: እጅ የሚያስቆረጥም ቀይና አልጫ ዶሮ ወጥ ከአይብ ጋር ተመግበን አብረው የቀረቡልንን አጥንቶች
ቅርጥፍጥፍ አረግናቸው:: የፒሲዋን ትምህርት ግብፆቹ ጅማ በመድረሳቸው መጀመሩ ስለማይቀር በዚህ ዓመት ተረጋግተን የምናከብረው የመጨረሻው
ዓመት ባል ፋሲካ ሆነ:: ወይዘሮ አልማዝ ቤት መመገብ ብቻ ሳይሆን ጠላ እየጠጣንና እየተጫወትን ለሶስት ሰዓታት ያህል ቆየን::
ከቴፕ ረኮርደሩም በሚወጡት የአስቴር ከበደ ጣዕም ያላቸው ሙዚቃዎች ተዝናናን:: ልይዘው ብሞክር ልጨብጠው በጥር......ለካስ በሀስብ
ነው አወይ የኔ ነገር.....
የሁለተኛ ዓመት ትምህርታችንን በትክክል የጀመርነው ሚያዚያ አስራ ዘጠኝ ቀን ነው ማለት ይቻላል:: የፋሲካ ማግስት ሰኞ እለት በግብፆች:: ፕሮፈሰር ሳላህ ና ባለቤቱን ተዋወቅናቸው:: ሁለቱም አናቶሚና እምብርዮሎጂ በጋራ እንደሚያስተምሩን
ፕሮፌሰር ሳላህ ነገረን:: የሚናገሩት እንግሊዝኛ የአረብኛ አክሰንት ቢኖረውም ለመረዳት ያማያስቸግር በመሆኑ ደስ ብሎኛል:: ፕሮፌሰር
ሳላህ አግባቡና ሁኔታው ባጠቃላይ ተመችቶኛል:: የሂስቶሎጂ መምህራችንንም ተዋወቅናቸው:: ጠና ያሉ ሰው ሲሆኑ መሐመድ አብደልማሰን
ይሰኛሉ::
ማክሰኞ ሚያዚያ ሃያአንድ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የምንማርባቸውን አራት ሬሶች(cadavers)
አየናቸው:: በሰፊው የአናቶሚ ላቦራቶሪ ውስጥ ከጡብ በተሰሩ አልጋዎች ላይ በፀጥታ ተጋድመዋል:: ትክክለኛ የሞቱ ሰዎች ናቸው:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም ምንም አልደነገጥኩም:: ሶስቱ ወንዶች ሲሆኑ አንዱዋ ሴት
ናት:: ፕሮፌሰር ሳላህ እያመላከተን ቆዳቸውን መቅደድ ጀመርን:: እኔም በቀደዳው (dissection) ዋና ተሳታፊ ነበርኩ..........
ሣሚ፡ እትዬ አልማዝ ቤት እናንተ ሳትቀድሙን ለመድረስ ብዙ እንጥር ነበር፤ ግን ምን ያደርጋል አባይ ኑሮውን እዚያው ያደረገ ይመስል እሱን መቅደም አንችልም ነበር….
ReplyDelete