ጨረቃ
ወኔዬ አልቆ ተሙዋጦ
መንፈሴም ደክሞ ተስፋ ቆርጦ
ብስጭት ገብቶኝ ሞትን ስሻ
መሄጃ አጥቼ መድረሻ
ወደበላዬ ስመለከት
ሰማይ ከዋክብት ወዳሉበት
አየሁ ጨረቃ መሃል ሆና
ምድርን ስታደምቅ በብርሃኗ
እነሆም ተስፋዬ አንሰራራ
ልቤ ተነካ ባምላክ ስራ
ብቻዬን እዳልሆንኩ ተገነዘብኩ
ነገን እያሰብኩ አሸለብኩ
(By Samson Haile)
ማክሰኞ መስከረም 19 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 6 ሰኣት ከ 13 ደቂቃ
ዛሬ ጠዋት ፊዚዮሎጂ ሌክቸር ከመውሰዳችን ቀደም ብሎ ፕሮፈሰር ማሂን ከግንዛቤ በማስገባት አንደሚጨንቀኝ አስቤ ነበር:: ግን ሳልጨነቅ ቀረሁና ያ ደግሞ አስጨነቀኝ:: እንዴት ሳይጨንቀኝ ቀረ?
ለነገሩ ለማን ብዬ ነው የምጨነቀው? አንድ አስተማሪ ደበረኝና ምን ይጠበስ?
በነገራችን ላይ ፒሲ ዋን ሁለተኛ ሴሚስተር በደንብ ተጀመረ:: ዛሬ አስከ ምሽቱ ሰባት ሰአት ለማንበብ እቅድ የነበረኝ ቢሆንም አሁን ደከመኝ: 47 ደቂቃ ሲቀር ማለት ነው.....
ውድ ማስታወሻዬ እኔ ካሁን ወዲያ ላንቺ የምነግርሽ የጨረቃን ድምቀት: የጸሃይን ጥልቀት: የዛፎችን ውዝዋዜና የነፋስን ሽውታ ነው እንጂ በቃ ጭንቀት አላወራም:: ኦ ጭንቀት አልኩ እንዴ? አላወራም ብዬ ስለሱ....
የግቢው አትክልተኛ አበቦቹን በደንብ እያሳመራቸው መሆኑን ተመለከትኩና አንድ ላንቺ ማለት ያለብኝ ነገር ትዝ አለኝ:: "ጥሩ ቀለማትን ከማየት የበለጠ ምን ነገር አለ?" እላለሁ አንዳንዴ:: በእርግጥ በሙዚቃና በስነጽሁፍ ብደሰትም የሰዎች ስራ ከሆኑት ከነዚህ ይልቅ በተፈጥሮ ህብረ ቀለማት ና የወፎች ዝማሬ ይበልጥ የመደሰት ባኅሪ ያለኝ ይመስለኛል......
ሮብ መስከረም 20 ቀን 1985 አ.ም.
ዛሬ ማታ ከቤተመሃፍት ንባብ ለአምስት ደቂቃ እረፍት ለማድረግ ወጥቼ ሳለ የኢንተርንሺፕ ሃኪም የሆነው አብርሃም ሻይ ገዛልኝና ከዚያ በሁዋላ ደስ እያለኝ አጠናሁ:: ቤተመጽሃፍቱ ሲዘጋ እንደተለመደው ወደ ሌክቸር ሆል ሄድኩ:: ወደዚያ እየሄድኩ ወደ ሰማይ ቀና ብዬ አየሁ:: ግማሽ ጨረቃ ትታያለች:: ልቤን በእርግጥ ደስ እንዳለው ይታወቀኝ ነበር:: ከዚህ በሁዋላ በሌክቸር ሆል ውስጥ በንባብ እስከ ምሽቱ 6 ሰኣት ከ40 ደቂቃ ቆይቼ ለመተኛት ወደ ዶርም ኣቀናሁ:: በመንገዴ ላይ እመቤት አብራኝ ነበረች:: ዝናብ እያካፋ የነበር ቢሆንም ርምጃችን የወትሮው ነበር.....
ሐሙስ መስከረም 28 ቀን1985 አ.ም. ከምሽቱ 7ሰኣት ከ 13 ደቂቃ
ዛሬ እንኩዋን የማወራው ነገር የለኝም:: ግን ጨረቃ በሙሉ ድምቀት በሰማያዊ ሰማይ ላይ እየታየች መሆኑን ሳልገልጽ መተኛት ከበደኝ:: ዶርም ቁጥር 207 ውስጥ አልጋዬ ላይ ነኝ:: የምጽፈው ማጣቴን ላልተኙ ጉዋደኞቼ እየነገርኩዋቸው ነው:: መንጌ አልጋው ውስጥ የገባ ቢሆንም አልተኛም:: የሆነ ነገር ይዞ ያነባል:: አባይም እንደዚያው:: አብይ ትንሹዋ ጠረጴዛ አጠገብ ሆኖ እያጠና ነው:: አሌክሱ አምሳሉ ሚሊዮንና ሃይሉ እንዲሁም ቤተማርያም እርግጡን ለመናገር ባልችልም እንቅልፍ ውስጥ ይመስሉኛል:: አባይነህ፥ አመንቴ ና አዳሙ የሉም:: ገና ኣልገቡም:: ውድ ማስታወሻዬ ደህና እደሪ:: ጉዋደኞቼም እንዲህ ይሉሻል.....
አባይ "እግዚኣብሄር ይመስገን"
መንጌ " God should be praised"
አብይ "ኑሮ መሮኛል"
No comments:
Post a Comment