ሰኞ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ 49 ደቂቃ
በዚህ ቀን ቀን ሞቃት ማታ ማታ ደግሞ ቀዝቃዛ: ደረቅና ነፋሻማ በሆነ ሰሞን የፒሲዋን
ሂደት ጫን እያለ መምጣቱ በብርቱ ተሰምቶኛል:: እሰከ ምሽቱ ሰባት ሰዓት በንባብ ተግቼ እቆይ ዘንድ አልሆነም:: ይህም በውስጤ ቅሬታን ፈጥሩዋል::
በእርግጥ ከቅሬታው ይልቅ ድንጋጤዬ አይሏል ብል ይሻል ይመስለኛል...ነገ ጠዋት እግዜር ከፈቀደ በማለዳ ተነስቼ ያሉኝን ጥቂት ካልሲዎች ውሃና ሳሙና
አስነካቸዋለሁ ብያለሁ:: ደህና ያሳድረኝ..
ሐሙስ ጥቅምት 12 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 7 ሰዓት ከ 19 ደቂቃ
የኔ ውድ አንድ በጣም የምቀርበውና የምወደው አሁን ባላወራውም ታሪኩ ከኔ ታሪክ ጋ የተሳሰረ
ተስፋሁነኝ የሚባል ባልንጀራዬ የአንደኛ ዓመት የህክምና ትምህርቱን በደህና ውጤት አጠናቀቀ:: በዚህም በእውነቱ ከልቤ ደስ አለኝ:: ነገር
ግን ደግሞ አንድ የሚያሳዝን ዜና ሰማሁ:: አንዲት ገነት የምትባል ትንሽ ትንሽ የማውቃት የተስፋሁነኝ ባች አባል የሆነች ተማሪ
ውጤቷ ከበቂ በታች ነው በሚል ከጤና ሳይንሱ እንድትባረር ተወሰነባት:: ይህች ቁመተ ለግላጋና ዝምተኛ ወጣት ሴት ዛሬ ምሽት ላይ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች በተዘጋጀ
የቅዱስ ሚካኤል መንፈሳዊ ፕሮግራም ላይ ተገኝታ በበዚያ ለተሰበሰብነው እድምተኞች ሁሉ አንድ አጠር ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ
አነበበች:: መቼም ብርቱና ሃይማኖተኛ ነበረች:: በተወሰነባት አስከፊ ውሳኔ በልቧ እንደምታዝን ባስብም : በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ
ሆና ከታዳሚ ፊት በመቆም ይህን ማድረግ በመቻሏ ጥንካሬዋን አደነቅሁ:: በአንፃሩ
ደግሞ እጅግ በመባረሯ በጣም አዘንኩ:: ከጤና ሳይንሱ አልፎ አልፎ እንደዚህ ተማሪዎች ሲባረሩ የሚሰማኝ ልዩ የሆነ የሽብር ስሜት ጎበኘኝ........
No comments:
Post a Comment