ሐምሌ 30 ቀን 1985 አ.ም.
ባለፈው ሰሞን አንድ ቆየት ያለ
ከእናቴ የተላከ ደብዳቤ ደረሰኝ:: ከተፃፈ አንድ ወር ይሆነዋል:: ደብዳቤው ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ እናቴ ስልክ ደውላ
ፈልጋኝ ነበር አሉ:: እንዳጋጣሚ ሆኖ አልተገናኘንም:: የደወለችበት ዋናው ምክንያት በባንክ ቤት በኩል ሃምሳ ብር
እንደላከችልኝ ልትነግረኝ ነበር:: ሸጋ ዜና ነው:: ይህንኑ ብር ከባንክ ቤት ከተቀበልኩ በሁዋላ ከመንጌጋ ወደ ጅማ መርካቶ በመሄድ አንድ ጨርቅ
ሱሪ በግማሹ ገዛሁ:: በተረፈው ጉዋደኞቼን ሰብስቤ ሻይና የበቆሎ ጥብስ ጋበዝኩበት…..የሄው ነው ያምሳ ብሩ ታሪክ::
በዚህ ቀፋፊ የሐምሌ ቀን በትክክል ምን ተሰምቶኝ እንደሆን ለመናገር ባልችልም የሚከተለውን
የስንኝ ቁዋጠሮ ግን አሰፈርኩ….
ሃሳብ ከሃሳብ ተጋጭቶ አንዳች ነገር ላይፈጥር
እርስ በርሱ ሲተካካ በላይ በላይ ሲደረደር
ሁሉ ነገር ባዶ ሲሆን የማይጠቅም ሲመስል
የሚያስበው ነገር አጥቶ አእምሮ ባየር ሲዋልል
ዓለም ሁሉ ከንቱ ሲሆን የማይረባ
ጭብጥ የሌለው ከቁምነገር የማይገባ
ደስታ ነገር ሳቅ ጨዋታ ጭልጥ ሲል
ባዘኔታ ተለውጦ በቁዘማ ሲጠቃለል
አየር ለጫንቃ ሲከብድ..ወኔ ስፈራርስ ሲናድ
አእምሮ ነገር ሲያሳድድ..አንድም ላያገኝ የሚወደድ
ሁዋላም በራሱ ሲፈርድ..በምንም ሃሳብ ላይጠመድ
እንቅልፍ እልም ብሎ ሲጠፋ
ጭንቀት በምትክ ሲስፋፋ
ከቶ መጥፎ ነው የሚመር
አንድ ቀን ኑሮ ሲደብር
ከዚህ የስሜት ጢቅታ በተቃራኒ ደግሞ ሐምሌ መጨረሻ ላይ አየሩ መልካም እየሆነ የመጣ መስሎ
ተሰምቶኛል:: ዝናብ ከዘነበ ጠዋት ብቻ ነው:: ከሰአትና ምሽት ላይ አየሩ ቀዝቀዝ ይልና መጠነኛ ነፋስ ሽው.. ሿ ስል ይሰማል::
በአሁኑ ሰዓት በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ ያሉት የህክምና ተማሪዎች ብቻ ናቸው ማለት እችላለሁ::
ከሁለተኛ ዓመት ላቦራቶሪ ተማሪዎች በስተቀር ሁሉም የዲፕሎማ መረሃ ግብር ተማሪዎች ለእረፍት ወደየመጡበት ሄደዋል:: እኛም
ብንሆን ከሁለት ሳምንት በሁዋላ እረፍት እንወጣለን:: ቀሪውን ክረምትና አዲስ አመት እንቁጣጣሽን ከቤተሰቦቻችን ጋር
እናሳልፋለን ማለት ነው:: ይህ መቼም እጅግ ደስ የሚል አጋጣሚ ነው:: ተስፋም ነው:: በበኩሌ ለአብዛኞቹ የሶስተኛ ዓመት ትምህርቶችም ሆነ መምህራን ካደረብኝ ብርቱ
ጥላቻ የተነሳ እረፍትንም ሆነ ባጠቃላይ ከዚህ አካባቢ ለተወሰነ ግዜ መለየትን ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ስሻ ነበር:: ተመስገን
ነው:: ለነገሩ የሶስተኛ ዓመት ትምህርቶች ደስ የሚሉ ሊሆኑ ይችላሉ:: ግን የሚያስተምሩት ሰዎች ላይ ቅሬታና የሻከረ ግምት አለኝ::
ለምሳሌ አንዳንዶቹ እንደ ማይክሮባዮሎጂ መምህር ያሉት ሲጀመር ባህሪያቸው አይስማማኝም:: ጠማማ ሆኖ ነው ለኔ የሚታየኝ::
አንዳንዴ እኔ ራሴን መቼ ይሆን መምህር የማመሰግነው? ብዬ እጠይቀዋለሁ:: ችግሩ የኔ ብቻ ይሆን እንዴ? ግን ደግሞ ወደ ሁዋላ
ተመልሼ በጣም የምወዳቸውና የማከብራቸውን መምህራኖቼን አስታውስና እፅናናለሁ:: ለምሳሌ የአስራ አንደኛና አስራሁለተኛ ክፍል ፊዚክስ
መምህሬ የነበረውን ህንዳዊውን ሚስተር ናየርን መቼም አልረሳውም:: እዚህ ጅጤሳ ፍሬሽማን ሂሳብ ያስተማረኝን ተስፋልደትን
እንዲሁም ያለፈው ዓመት አናቶሚ ፕሮፌሰሬን ግብፃዊውን ሳላህን
በልቤ ከፍተኛ ሰፍራ እሰጣቸዋለሁ:: እነዚህን ሰዎች ሁሉ በበኩሌ አንድ የሚያደርጋቸው ሆኔታ አለ እላለሁ:: ሁሉም የሚያስተምሩትን
ትምህርት እጅግ አዋቂዎች: በስራቸው ታታሪዎችና ዘወትር ለሌሎች ቀና አሳቢዎች ነበሩ….
No comments:
Post a Comment