Sunday, May 29, 2016

ህዳር 7 1986 አ.ም.

የንቃት ጅማሬ
ትናንትና በድንገት ከቅርብ ጉዋደኛዬጋ ፍራሽ ላይ ተቀምጬ የጅማን ጫት በአፌ ውስጥ አኖርኩ: : በሂወቴ ጫት ስነካ የመጀመሪያዬ ነው:: ጫቱን አፌ ውስጥ አስገብቼ አኘኩት: እኛኪውንም መጠጥኩት:: እኔና ጉዋደኛዬ ከፊትለፊታችን ፍራሹ ላይ ግማሽ እግሮቻቸው ባለ አስር ሳንቲም ፌስታል ውስጥ ያረፉ የጫት ዝንጣፊዎችን  በግራ እጆቻችን በመያዝ በቀኝ እጆቻችን ቀንበጦቹን አሁንም አሁንም ወደ አፎቻችን በማስገባት አሻመድናቸው:: በቀንበጦቹ ድዶቻችንን አስታከን ለጋ ጉንጮቻችንን ወጠርናቸው: ለተወሰኑ ደቂቃዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አወጋን:: ቧልት እየቦለትን ተሳሳቅን:: አንዳንድ ያጋራ የሆኑ ምናባዊ ሀስቦቻችንን ተለዋወጥን::ከዚያም ፊቶቻችን መሞቅ: ማብለጭለጭና መቅላት ጀመሩ:: አፍታም ሳንቆይ ነቃን:: ወጣት አእምሮዎቻችን ለአትኩሮት ተዘጋጁ:: የእጅ, የእግርና የወገብ ጡንቻዎቻችን ተፍታቱ:: ወደ pathology ንባባችን ገባን:: በበኩሌ ሃሳቤ ተሰባስቦ ካነበብኩባቸው ጥቂት የሚታወሱ ቀናት ይህ አንዱ ነው::

በትናንትናው የጥናት ስኬት በመነሳሳት ታዲያ ጫትን ዛሬም ደገምኩት:: ነገር ግን ውጤቱ እንደንትናንትናው ሊሆን አልቻለም:: አለመሆን ብቻ ሳይሆን እንደ ድካም: እንደመዛል አድርጎ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደኝ: ከቀኑ ሰባት ሰዓት የተኛሁ አስር ሰዓት ላይ ተነሳሁ:: ከዚያም ወደ ቤተ መፅሃፍቱ በመሄድ እስከምሽቱ ሶስት ሰዓት ድረስ አጠናሁ...የእንቅልፉ ነገር ቢገርመኝም ህዳር 8 ቀንም እንደቃምኩ ግን ልብ በል/ይ...የሆነ ጥቅም ያለው መስሎ ተሰምቶኛል...

ህዳር 17 ቀን 1986 አ.ም.

የልቤ ወግ
እንደምን አለሽ ማስታወሻዬ:: እኔ መችም አለሁ:: ምንም አልልም:: በሶስተኛ ዓመት የበረታው የልቤ መከፋት እንደቀጠለ ነው:: ይህን ስል ግን በጉዋደኞቼም ሆነ በሌሎች ሰዎች ፊት ደስታኛና መልካም መስዬ መቅረቤ እንደቀጠለ መሆኑን ላስታውስሽ እወዳለሁ ::

ልቤን በብርቱ እያስከፋው ያለው ነገር የሶስተኛ ዓመት ህክምና ትምህርት የፈተና ውጤቶቼ ከከዚህ ቀደሞቹ አንፃር አመርቂነት እያነሳቸው መምጣቱ ነው:: የዚህ ዋናው ምክንያት ግልፅ ነው: በንባብና በጥናት አለመትጋቴ ነው:: ለማወቅ የከበደኝ ግን ለምን እንደማልተጋ ነው:: በውስጤ ግዙፍ የሆነ የትምህርት ፍላጎት ማነስ አለ:: እስካለፈው ሰሞን ድረስ ቀዶ ጠጋኝ ሀኪም ( surgeon) ለመሆን እመኝ ነበር::  አሁን ግን ይህ ምኞት እውነተኛ ምኞቴ እንዳልሆነ ሆኖ ተሰማኝ:: ስለዚህም አዳፈንኩት:: አሁን በቃ የህክምና ትምህርቴን ለመጨረስ ብቻ ነው የማስበው:: ከዚያ በሁዋላ ወደ ስነ-ጥበብ (Art) ለመግባት ሕልም አለኝ:: ይህ ሕልም አሁን የተፈጠረ አይደለም:: እኔ ሃይስኩልም ሆነ ከዚያ በታች ስማር በነበረበት ወቅት በግጥም ገጣሚነት: በድርሰት: በስእል: እንዲሁም በዘጋቢነት የጎላ ተሳትፎ ነበረኝ:: እንደውም አንዳንድ መምህራንና ጉዋደኞቼ የከፍተኛ ትምህርቴን ከሳይንስ ይልቅ በአርት መንገድ እንዳደርገው መክረውኝ ነበር:: ለምን በአርት መንገድ እንዳልሄድኩ በውል አላውቀውም:: ነገር ግን ባዮሎጂ : ፊዚክስና ሂሳብ ትምህርቶችን ጥልቅ በሆነ ፍላጎት (passion) እወዳቸው እንደነበር አውቃለሁ:: ሳይንስ ተጨባጭ ስለሆነ ይመቸኛል:: ከሳይንስ ትምህርቶች ውስጥ ሕክምናን እንድመርጥ ተፅዕኖ ያሳደሩብኝ ሶስት ሁኔታዎች ይመስሉኛል:: አንደኛ ባደኩበት አካባባቢም ሆነ ከዚያ በሰፋው ማህበረሰባችን ሕክምናና ሀኪም የተሰጣቸው አክብሮትና ስፍራ የትየለሌ መሆኑ: ከዚህ በፊት እንዳልኩት ጮርቃ ልጆች ሆነን ስታድግ/ጊ ምን ለመሆን ነው የምትፈልገ/ጊው ተብለን ስንጠየቅ ብዙዎቻችን የምንመልሰው “ዶክተር” ብለን ነበር:: ሁለተኛው ምክንያቴ የአስራሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ በሆነው የማትሪኩለሽን  ፈትና ባዮሎጂና ሂሳብ “A” ነገር ግን ፊዚክስ “B” ማግኘቴ ነበር:: ከሶስቱ የምወዳቸው ትምህርቶች ወስጥ ፊዚክስን የበለጠ ነበር የምወደው:: ነገር ግን ይህን የፈተና ውጤት ካገኘሁ በሁዋላ ቆም ብዬ አሰብኩ:: በዚህ ምክንያት ኢንጂነሪንግ ወይም አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ምርጫዬ ሳይሆን ቀረ:: ሶስተኛውና በመጨረሻው ሰዓት ላይ ተፅዕኖ ያሳደረብኝ የትምህርትቤቴ (የአዲስከተማ) ተማሪዎች ዲን የነበረው ሰው (ስሙን ሳልረሳው አልቀረም ግን መኩሪያ ይመስለኛል)በማትሪክ ጥሩ ውጤት ያመጣነውን ተማሪዎች ሰብስቦ የተናገረን ነገር ነው:: በትክክል ቃል በቃል ባላስታውሰውም  እንዲህ ያለ ይመስለኛል:: “ውጤታችሁ 3.6ና ከዚያ በላይ በላይ የሆነ ተማሪዎች ሜዲስን ትምህርት መምረጥ አለባችሁ: ከባድ ቢሆንም በጥሩ ሁኔታ ትወጡታላችሁ የሚል ከፍተኛ እምነት አለኝ:: ሌሎቻችሁ ግን ከሜዲስን ውጭ የሆኑ ትምህርቶች ላይ አተኩሩ::” በዚህ አነጋገሩ የሜዲስን ትምህርትን ከባድ ብሎ ቢፈርጀውም ለኔ ልዩ (ብርቅ) አድርጎ አቀረበው:: ለተወስንነው ብቻ የሚሰጥ እንደከበረ ድንጋይ እንደልብ የማይገኝ አርጎ አቀረበው:: ስለዚህም ከላይ ከጠቀስኩዋቸው ሁለት ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ በውስጤ በነበረ የተለየውንና ብርቁን  ነገር የመሻት ተፈጥሮአዊ ግፊት ሜዲስንን ለመማር መረጥኩ::

የህክምና ትምህርት በየቀኑ እጅግ በጣም ረዥም ለሆነ ሰዓት በትዕግስት ሃሳብን አሰባስቦ አእምሮን አሹሎ ማንበብን ይጠይቃል:: በእርግጥ ይህን ማድረግ የሚችሉ አንዳንድ ብርቱ ጉዋደኞቼ አሉ:: ጉዋደኞቼ ካልሆኑትም ውስጥ ጎበዝ የምላቸው አንባቢዎች አሉ:: እነዚህ በጅጤሳ አነጋገር “በራቾች” ይባላሉ:: ብረት ከሚለው ቃል የተወሰደ ነው:: ሕክምና ትምህርት ከተነበበ በሁዋላ ደግሞ ማስታወስን ይፈልጋል:: አንብበው የሚያስታውሱ የመኖራቸውን ያህል ብዙ አንብበው ግን በበቂ ሁኔታ ማስታወስ የሚሳናቸው አሉ:: እነዚህ ያሳዝኑኛል:: አንዳንዶች ደግሞ አሉ:: በቃ በቀላሉ የሚገባቸው:: የሚገልፅላቸው:: እነዚህ ብዙ ማንበብ አያስፈልጋቸውም:: ፈተና ላይም የሚችላቸው የለም:: ያስቀናሉ:: በፍጥነት ማንበብ የሚችሉ ደግሞ አሉ:: ቶሎ ቶሎ የሚያንቡትን ደብተርም ሆነ መፅሐፍ ይገልጡታል:: እንደነዚህ አይነቶቹ አጠገብ ተቀምጦ ማጥናት ሰቀቀን ነው:: ከማስደንገጡም ባሻገር የሞራል ውድቀት ሊያስከትል ይችላል::

ታዲያ እኔ የቱ አይነት ነኝ? ለረዥም ሰዓት ተቀምጠው ማንበብ ከሚችሉት ወገን እንዳልሆንኩ መቸም ግልፅ ነው:: ተፈጥሮዬ አይፈቅድም:: በፍጥነት ከሚያነቡት ውስጥም አይደለሁም:: ብዙ የማያነቡ ካሉ እኔ ከነሱ ወገን ነኝ::

ከላይ እንዳልኩት በዚህ ሰዓት የህክምና ትምህርት ፍላጎቴ ክፉኛ ዳሽቁዋል:: ምናልባት ትንሽም ቢሆን ያነበብኩትን አስታውሳለሁ መሰለኝ.......ከሴሚስተር ወደ ሴሚስተር በመሽጋገር ለሶስተኛ ዓመት የመጨረሻ ማጠቃለያ ፈተና ሰሞን ደርሻለሁ::

ሕክምና ትምህርቴን ለመጨረስ ቁርጠኛ ውሳኔን በልቤ አኖርኩ: ዛሬ.....





No comments:

Post a Comment