Sunday, November 6, 2016

ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜ 5 1987 አ.ም.

በሳምንቱ መጀመሪያ እሁድ  ላይ አንድ ከአዲሳበባ በቅርብ የመጣና ለጊዜው ስራው ጅማ የሆነ ጉዋደኛዬ ባደረገልኝ ግብዣ መሰረት ከሰአቱን ከእርሱጋ አሳለፍኩ:: በመሰረቱ ጥሩ ምሳ ከበላን በሁዋላ እርሱ መኖሪያ ቤት ወለል ላይ በተዘረጋ ቀጭን ፍራሽ ላይ ዘና ብለን ተቀምጠን ንቃተ ህሊናችንን በአረብ ተራ ጫት ቀንበጥ የበለጠ አንቅተን ቧልት የተቀላቀለበት ፍልስፍና ስንሰልቅና የተለያዩ የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎች ስናዳምጥ ዋልን:: በጣም የምቀርባቸውና የምወዳቸው ሁለት ጉዋደኞቼ መንጌና አብይ አብረውኝ ነበሩ::

በማግስቱ ሰኞ በቀደመው ሳምንት የነበረኝን ሕክምና የመማር ልበሙሉነትና ተነሳሽነት የሚያሰርዝ ሁኔታ ገጠመኝ:: ከህሙማኖቼ መካከል አንደኛው  የእግሩ ጡንቻ በሰፊው በመምገሉ (pyomyositis) ጉልበቱና ብሽሽቱ ላይ መሸማቀቅ ደርሶበት እግሩ ባጠቃላይ መዘርጋት አልቻለም (Contracture):: ለዚህ ህመምተኛ የእግሩን ቆዳ በሰፋፊ የቁስል ፕላስተር በመለጠጥ እግሩ እንዲዘረጋ ለማረግ (Skin traction) አስቤ ግን ከዚህ በፊት ሰርቼው የማላውቅ ነገር በመሆኑ ሳልፈፅመው አደርኩኝ::

ማክሰኞ ቁጥር 6 አልጋ ላይ አዲስ ህመምተኛ ነበረኝ:: አንድ ቁመቱ አጭር ሰውነቱ የፈረጠመ  ሰው ነው:: ግራ ደረቱ ላይ አንበሳ ቦጭቆት ነው ወደ ሆስፒታሉ የመጣው:: አንበሳ ፔክቶራሊስ ሜጀሩንና ማይነሩን (Pectoralis major & minor) ገሽልጦ ሰልቅጦታል:: በአንበሳ የተነከሰ ሰው ለመጀመሪያ ግዜ ማየቴ ስለነበር ሰውዬውን  ራሱ እንደ አንበሳ እየፈራሁ ነው ያናገርኩት:: ሰውዬው ፈርጣማ በመሆኑ ነው መሰል የግራ ደረት ጡንቻው ከቦታው ከመጉደሉ በስተቀር ሌላ የህመም ምልክት ሳይታይበት አንዳልታመመ ሰው ነው ያነጋገረኝ:: ይህ ሰው የሚኖርበት አካባቢ በቅርብ ርቀት አንበሶችም እንደሚኖሩና እሱን የነከሰችው  ሴት አንበሳ መሆኗን ነገረኝ:: አንበሲቷ እየነከሰችው  ሳለ ጎረቤቶች ደርሰው አስጣሉትና ይዘውት ወደ ሆስፒታሉ መጡ:: ቁስሉ በድንገተኛ ክፍል የመጀመሪያ እርዳታ ከተደረገለት በሁዋላ ወደመኝታ ክፍል የመጣው በዋናነት ፀረ ህዋስ መድሃኒት (Antibiotic) በደም ስሩ መሰጠት ስላስፈለገው ነው::

እሮብ ጳጉሜ አንድ ቀን ከቤት የላክልኝ ሃምሳ ብር ከእናቴ የደመቀ ሰላምታ ጋር ደረሰኝ:: ይህ በሆነ በሶስተኛው ቀን ቅዳሜ ጳጉሜ 04  ከኛ በሁለት ዓመት የሚበልጡን ሐኪሞች (the 1987 graduates) በመመረቃቸው  በጅማ ሆቴል ያዘጋጁትን የምሽት ዳንኪራ ስካፈል ሃምሳ ብሬንም በሆቴሉ ውስጥ ላለው ባር አካፈልኩ :እነሱም መጠጥ አካፈሉኝ: የኔም ራስ ለሁለት ተከፍሎ ከውድቅት ወዲያ ወደመኝታ ክፍሌ ደረስኩ::


እሁድ ጳጉሜ 5ን በሃንጎቨርውስጥ አሳለፍኩ:: የዚህ ዓመት ጳጉሜ 6 ቀን በመሆኑ እሁድ አዲስ ዘመን ዋዜማ አልነበረም:: 

No comments:

Post a Comment