አርብ ጥቅምት 9 1988 አ.ም.
ዛሬ በተለካሁበት የተግባር ፈተና ሰርጀሪ ትምህርት በሂወቴ ለመጨረሻ ግዜ ተጠናቀቀ:: ስፔዣላይዝ ላለማድረግ የወሰንኩት የህክምና ዘርፍ ስለሆነ ዳግም በትምህርት መልኩ የሚገጥመኝ አይመስለኝም:: የጠዋቱ ፈተና አንዲት የእንቅርት በሽታ ተጠቂ የሆንች እንስት ላይ ነበር:: ብዙም ታሪካዊ አልነበረም:: ከሰዓት ግን ፈተናዬን ስጨርስ ደስተኛ አልነበርኩም:: የቃል አንካ-ስላንትያው (VIVA EXAM) አባጣ ጎርባጣ የበዛበት ነበር:: የፈተነኝ በጣም የምወደውና የማከብረው ቀዶ ሀኪም ዶክተር ሚናስ ነበር:: እንዳጋጣሚ ሆኖ ግን ፈተናው ላይ ኮከባችን አልገጠመም:: አመላለሴ አልጣመውም:: ሚናስ የተቆጣ መሰለኝ:: ነብር ሆኖ ታየኝ:: ምንድን ነው ችግሩ? የሱን ሁኔታ በማየት ከፈተናው በፊት የተጨነኩት ሳያንስ ፈተና ውስጥ እያለሁ ጨነቀኝ:: ግራ ተጋባሁ:: ከፈተናው በሁዋላ በውስጤ የነበረው ብቸኛው ተስፋ ይህ ፈተና የውስጥ (Internal) የመሆኑ ሀቅና ከፅሁፍ ፈተናው ጋ ተደምሮ የኔን የቀዶ ሕክምና ችሎታ ለመገምገም የሚኖረው ድርሻ ከሲሶ ያነሰ (30% )ብቻ መሆኑ ነው:: ሌላው 70% የሚመጣው ሙሉ በሙሉ ከመጨረሻው የውጭ የተግባር (External) ፈተና ነው:: ያ ፈተና ገና ብዙ ወራቶች ይቀሩታል:: እዚያ ላይ እበረታ ይሆን በሚል በጭንቅላቴ የተፈጠረችውን አናሳ ተስፋ ሙሉ በሙሉ ጨበጥኩዋት እና ሚናስን ረሳሁት......
ሰኞ ና ማክሰኞ ጥቅምት 5 ና 6 1988 አ.ም.
የፈተናዬ ቀን ሮብ መስሎኝ ተሸብሬ ነበር:: በአይኖቼ መንቀጥቀጥ የታጀበ ጥልቅ ጭንቀትና መደናበር ውስጥ ነበርኩ:: ነገር
ግን ዛሬ ሚኪያስ የኔና የርሱ ተራ አርብ መሆኑን ሲነግረኝ ደስ አለኝ::
አርብ ለት ከሚኪያስ ቀጥሎ ሁለተኛው ተፈታኝ ነኝ:: ይህን በማወቄ አሁን መረጋጋት ብቻ ሳይሆን የፈተና ፍራቻዬ ቀንሶ
የንባብ አትኩሮቴ ደሞ ጨምሯል:: ሰውነቴ በቅፅበት ተፍታታ:: እጅግ በጣም ተፍታታ:: ነገ ቢሆንስ ኑሮ ፈተናዬ? አርብ በመሆኑ እድለኛ ነኝ አልኩ በውስጤ
...አንዳንድ ያላነበብኩዋቸውን ሀቆች ለመሸፈን ግዜ አገኘሁ ማለት ነው::
ማክሰኞ ለት ምሽት ላይ መብራት ተቁዋርጦ ስለነበር ለፈተና የማደርገው ዝግጅት ተስተጉዋጉሎ ነበር:: አሁንም ከምሽቱ
ሁለት ሰዓት ተኩል ይህን እየፃፍኩ ያለሁት በሻማ መብራት ነው:: እኔ ይህን ፅሁፍ እየፃፍኩ ባለሁበት ቅፅበት የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ
የሆኑት ቤተማርያምና በየበሩ የሻማ ብርሃን ተጠቅመው እያጠኑ ነው:: በየበሩ ማስታወሽ እየፃፍኩ እንደሆነ አውቁዋልና ይህችን
የሻማ ንባብ ወቅት እንድከትባት አሳሰበኝ:: በዚህ የፈትና ዋዜማ ከመቼውም ግዜ ይበልጥ የሚፈለገው የኤሌትሪክ ብርሃን ባለመኖሩ
እንዴት ፍዳችንን እያየን እንደምናጠና እንድፅፍ አሳሰበኝ:: በዚህ የጭንቅ ሰዓት አጋር ሆና የገኘችው ቀጭኗ ሻማ ምስጋና
ይገባታል:: እርስዋ ባትኖርስ ኖሮ? ነገ ሮብ የሰርጀሪ ተግባር ፈተና በይፋ ይጀመራል:: እኔ ቤተማርያምንና በየበሩን ትቼ አስር
ሚሊ-ግራም ዲያዘፓም ውጬ ልተኛ ዝግጅቴን አጠናቀኩ......
No comments:
Post a Comment