የፈተና ሰሞን
ማክሰኞ ታህሳስ ሁለት ቀን 1988 ዓም
ዛሬ ምሽት ላይ ዝናብ ጣለ:: በጋራ መኝታ ቤታችን ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ ከኔና ከመንጌ በስተቀር ነገ የየተመደቡበትን ክፍል ፈተና ያጠናቅቃሉ:: መንጌ የውስጥ ደዌ ትምህርት ፈተና ሐሙስ የሚያጠናቅቅ ሲሆን እንደ ዕድል ሆኖ እኔ ግን ለመፈተን የመጨረሻው የዶርሙ አባል በመሆን አርብ የውስጥ ደዌ ትምህርቴን እፈተናለሁ:: በህክምና ትምህርት ውስጥ እንዲህ ያሉ የምጥና የመከራ ቀናት ለኔ አዲስ አይደሉም ነገር ግን የዶርም ተጋሪዎቼ በሙሉ ፈተናቸውን ጨርሰው እያየሁ እንዴት አዘልቀዋለሁ! ከባድ ነው የሚሆንብኝ:: ከኔና ከመንጌ በቀር ሌሎቹ ነገ የሚፈተኑት በሙሉ የማንበብ ፍጥነታቸውን ቀንሰው ለማይቀረው ፈተና ሃሳባቸውንና አእምሮአቸውን በማረጋጋጋት ላይ ናቸው:: የመጨረሻው ተፈታኝ በመሆኔ ከፋኝ:: ብቸኝነት ተሰማኝ:: ዛሬ ከሰዓት በሁዋላም የጎሰጎስኩት የጫት ምርት አላመረቀነኝም:: ፀጥ ግን አድርጎኛል:: የመኝታ ክፍል ተጋሪ የሆኑትና የቅርብ ጉዋደኞቼ በሙሉ በአካል አጠገቤ ቢሆኑም በውስጤ የተፈጠረውን የብቸኝነት ስሜት ሊያስታግሱት አልቻሉም:: ጭንቀትና የስሜት አዘቅት እየተፈራረቁብኝ ነው......
ሐሙስ ታህሳስ አራት ቀን 1988 ዓም
አሁን ከቀኑ ስድስት ሰዓት ነው:: መኝታ ቤታችን ውስጥ ካለው ግዙፍና ባዶ ጠረጴዛ ፊት ተቀምጫለሁ:: ቤተማርያም ትናንት ፈተናውን ያጠናቀቀ በመሆኑ ዛሬ ለሽ ብሎ አልጋው ላይ ተኝቷል ::በዚህ ሰዓት መንጌ ምናልባት የርሱን ፈተና ጨርሶ ይሆናል:: ገና አልመጣም:: ከዚህ መኝታ ክፍል እኔ ብቻ ነገ እፈተናለሁ:: ከጭ ንቀቱና ከስሜት አዘቅቱ ላይ ዛሬ ድካም ታክሎበታል-ጎሽ! ደ ብተርም ሆነ መፅሐፍ ማየት አስጠልቶኛል....
በነገራችን ላይ ዛሬ ጠዋት ከቤት በፖስታ የተላከልኝን ወርሓዊ ሃምሳ ብር ጅማ ፖስታ ቤት በመሄድ በጠዋት ከተቀበልኩ በሁዋላ የነበሩብኝን የሱቅ ዱቤዎች ከፍዬ ባሁኑ ሰዓት ከወጪ ቀሪ ምንም የለኝም:: ወደፖስታ ቤት ከመሄዴ በፊት በነበርኩበት አቁዋም ላይ ነኝ :: አሁን ያማረኝ አጭር የመኝታ ግዜ ውይንም ናፕ ነው፣ ከተቻለ :: ስህተት መሆኑን ባውቅም በተደጋጋሚ ፈተናዬ ከባድ ይሆናል ብዬ ማሰቤን መተው አልቻልኩም......
No comments:
Post a Comment