መስከረም 12 1988 አ.ም.
ዛሬ በተማሪዎች ቴሌቪዥን መመልከቻ አዳራሽ ውስጥ “No Place to Hide”
የተሰኘው ፊልም ሲታይ እኔም ታደምኩ:: እጅግ የወደድኩት ፊልም ነው:: በልቤ ውስጥ ካለው ነገር ጋ የሚሄድ ጠንካራ ትርጉም
አገኘሁበት:: በፊልሙ ውስጥ ያለው ዋና ገፀ ባህሪ በኔ ሚዛን እጅግ መልካም እንዲሁም እውነተኛ: እውነትን ለመታደግ ብሎም
ሕግን ለማስከበር የቆመ ስለነበር ወደድኩት::
መስከረም 13 1988 አ.ም. - ራሴን ሳክም
አልፎ አልፎ እንደሚያደርገኝ ዛሬ ደብሮኝ ነበር:: ቀላል ድብርት አይደለም::
ትልቅ የሆነ ድብርት ከነጉዋዙ:: የመሰላቸት ስሜት የገነነበትና በራስ የመተማመን ስሜት ጥቂት የሆነበት:: “የፍልስፍና ሙድ”
ውስጥ ነበርኩ:: አለማችን እግዚአብሔር ቆንጆ አድርጎ ቢፈጥራትም በዘመንና በሰው ልጆች ትብብር ቆሽሻ ታየችኝ:: የራሴን
ምንነትና በዚህ የቆሸሸ ዓለም ላይ ያለኝን ቦታ ለራሴ ጠየቅሁ:: ራሴን የሆነ ቦታ መመደብ ፈለግሁ ግን ቦታ አጣሁ::
ያለማቁዋረጥ እንቶፈንቶ አሰብኩ:: ለቅፅበት ፍርሃት ውስጥ ገባሁና ወጣሁ:: የያዝኩት ሕክምና ትምህርት ዳግም ከመቸውም የበለጠ
ከብዶ ታየኝ:: ተስፋ መቁረጥ ጀምሬ ተስፋ መቁረጤ ራሱ አስፈራኝና ተውኩት::በመፅሐፍ ቅዱስና በታገል ሰይፉ ግጥም ላይ
ያነበኩትን የእምባቆምን ለቅሶ አስታውስኩ:: በእግዚአብሔር ታላቅ ተስፋን ለማድረግ ወሰንኩና መተንፈስ ቀጠልኩ........
መስከረም 14 ና 15 1988 አ.ም. - ቻዎ ሰርጀሪ
ዙሩን ለመጨረስ ሶስት ሳምንት ሲቀረኝ ቀዶ ጥገና (surgey) ትምህርት
በማያሻማ ሁኔታ ሰለቸኝ:: በቃ በግልፅ ለመናገር ከዚህ በሁዋላ
የተንዛዛ (ቦሪንግ) ነው:: ይህ አምና ስፔሻላይዝ አደርግበታለሁ እንዲሁም በቀዳሚነት እወደዋለሁ ያልኩት ፊልድ የኔ እንዳይደለ
ጥርት ብሎ ታየኝ....ቻዎ
መስከረም 17 1988 አ.ም. ሐሙስ ጠዋት - መስቀል
ከዛሬው ይልቅ ስለትናንት ማታ ልናገር:: ለኔና ለጉዋደኞቼ ጥሩ ምሽት ነበር::
እኔና እነመንጌ የመስቀል ዋዜማ በመሆኑ እንደተለመደው: ምሽቱን ወጣ ብለን ለማሰለፍ ሳንቲም አሰባሰብን:: ሳንቲም ካላቸው ጉዋደኞቻችን
ተበደርን: አሮጌ ልብሶችና ጫማዎች ገበያ ወደን ጆሮ ግንዳቸውን አልን: ከዚያም ወደ ጅማ ከተማ እምብርት ሄድን...ጠለቅን::
በቅርብ የተዋወቁት መሃንዲሱ ጉዋደኛዬ ጌታሁን አብሮን ስለነበር የኔ ደስታ እጥፍ ነበር:: ሌላው ምሽቱን ልዩ ያደረገው ግርማ
ሁንዴ ለመጀመሪያ ግዜ ምሽት ላይ እኛን መቀላቀሉ ነው:: እርሱ ደሞ ቀን ላይ አዲስ መጫሚያ ገዝቶ ስለነበር ተመችቶት ነበር::
ብዙ ግዜ እንዳደረግነው ወይን ጠጅ እየጠጣን ደነስን:: ዶርማችን ስንመለስ መንግስቱ ከሌሎቻችን በገዘፈ ሞቅታ ተኝተው
የነበሩትን ጉዋደኞቻችንን ቀሰቀሳቸው:: ነገርግን እነሱ መንም ቅር አልተሰኙበትም:: ምክንያቱም መስቀል በተለምዶ የጉራጌ በዓል
ነው ስለሚባል .............
No comments:
Post a Comment